{$lang.login}{$lang.site_name}
Welcome
Login / Register

ትምህርተ ሃይማኖት


 • “ኦ ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ” ማቴ. ፳፭፥፳፫

  አንተ በጎ እና ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሀልና በብዙ እሾምሀለሁ፡፡

  የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብር ኄር ይባላል፡፡ ገብር ኄር ማለት ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ስለ ታማኝ አገልጋይ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ስንኖር ለፈጣሪያችን ያለንን ታማኝነትና የምናገኘውን ዋጋ በመዋዕለ ሥጋዌው አስተምሯል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዜማ መክፈያነት የዐቢይ ጾምን ሳምንታትን ሲከፍል ገብር ኄርን ተጠቅሟልና እኛም ስለ ገብር ኄር ጥቂት እንበል፡፡


  ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ አንደበት አድሮ፤ “እከሥት በምሳሌ አፉየ፤ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት፤ አንደበቴን /ነገሬን/ በምሳሌ እገልጣለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ ታሪክና ምሳሌ እናገራለሁ” አለ፡፡ ይህም ማለት ወንጌልን በምሳሌ አስተምራለሁ፤ በመልከ ጼዴቅ ዘመን አስቀድማ የተሠራችና ታይታ የጠፋችውን ወንጌልን እናገራለሁ፡፡ ይህን ታላቅ ምሥጢር ሐዋርያው ሲያብራራ “. . . ከመ በአሚን ያጸድቆሙ እግዚአብሔር ለአሕዛብ አቅደመ አሰፍዎቶ ለአብርሃም ከመ ቦቱ ይትባረኩ ኲሎሙ አሕዛብ፤ . . . በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ” ብሏል፡፡ /ገላ. ፫፥፰፣ መዝ. ፸፯፥፪


  በዚሁ መሠረት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ለልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ ምሳሌ አስተምሯል፤ ከላይ በተገለጠው ኃይለ ቃል መነሻነት ሁለት ምሳሌያትና አንድ ቃለ ትንቢት ቀርበዋል፡፡ ከምሳሌያቱ የመጀመሪያው በዐሥሩ ደናግል አንጻር የቀረበው ምሥጢር ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ወጥተው ወርደው ነግደው ያተርፉበት ዘንድ ገንዘቡን ስለሰጠ አንድ ነጋዴ የሚናገረው ነው፡፡


  የትንቢቱ ምሥጢራዊ ይዘት የሚያስረዳውም ስለ ኅልቀተ ዓለም አይቀሬነት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ዕትማችን ወጥተው ወርደው ነግደው እንዲያተርፉበት ከጌታቸው የተሰጣቸውን መክሊት ስለተቀበሉት አገልጋዮች ሕይወት እንመለከታለን፡፡ ፈጣሪያችን አእምሮውን ለብዎውን /ማስተዋሉን/ ያድለን፡፡


  ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ያስተማራቸው ምሳሌያዊ ትምህርቶች በቅዱስ መጽሐፋችን በሰፊው ተጽፈው እናገኛለን፡፡ የእነዚህ ትምህርታዊ ምሳሌዎች መሠረታዊ አሳብና ዓላማም የእግዚአብሔርን መንግሥት የምናገኝበትን የታማኝነትን ሥራ እንዴት መሥራት እንደሚገባንና መሥራትም እንደምንችል ማስተማር ነው፡፡


  ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመንግሥተ ሰማያት ምሥጢር ያስተማራቸው ብዙ ምሳሌዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ብዙ ምሳሌያዊ ትምህርቶች መካከልም እንዲያተርፉበት መክሊት ስለተሰጣቸውና ስለተመሰገኑት መልካም አገልጋዮች፣ እንዲሁም መክሊቱን በመቅበሩ ምክንያት በጌታው ስለተወቀሰውና ፍርድን ስለተቀበለው ሰነፍ ሰው ታሪክ፣ የታሪኩም ምሥጢር ምን እንደሚመስል የተጻፈው ትምህርት ነው፡


  ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ምሳሌ የተናገረው /ያስተማረው/ በሚከተለው መልኩ ነበር፤ ‹‹ወደ ሌላ ሀገር የሚሔድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ ሀገር ወዲያውኑ ሔደ፡፡ አምስት መክሊትም የተቀበለው ሔዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፣ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፣ አንድ የተቀበለው ግን ሔዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ፡፡


  ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፡- ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፡፡ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡


  አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሔጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ መክሊትህ አለልህ አለው፡፡ ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፡- አንተ ክፉና ሐኬተኛ ባሪያ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁበትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር:: እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር፡፡ ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት ዐሥር መክሊትም ላለው ስጡት:: ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል:: ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል የሚል ነው፡፡


  መክሊት ጥንት የክብደት መለኪያ ነበር:: አንድ መክሊት 30 ኪሎ ግራም ያህል ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸውም መክሊት የሚለው ቃል ገንዘብን ያመለክታል፡፡


  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ እርሱን የምናገለግል ሁላችን እንደየዓቅማችን ማድረግ የሚገባንን መንፈሳዊ የአገልግሎት ሥራንና በአገልግሎታችን ውጤታማ በመሆናችንም ከእርሱ የምናገኘውን ዘለዓለማዊ ክብርና ዋጋን እንዲሁም መሥራት የሚገባንን ባለማድረጋችንም ምክንያት የሚገጥመንን መለኮታዊ ቅጣትን አመልክቶናል፡፡


  በዚህ ምሳሌ ውስጥ ባለ አምስት የተባለው በቂና ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ የተካ ያወጣ ነው፡፡ በተመሳሳይም ባለ ሁለት የተባለው እንደ መጀመሪያው ሁሉ ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣ ሲሆን ባለ አንድ የተባለው ደግሞ ተምሮ ሳያስተምር የቀረ በስንፍና በቸልተኝነት በማን አለብኝነት ሕይወት ተገድቦ የቀረ ሰው ነው፡፡


  በመሆኑም የባለ አምስትና የባለ ሁለት መክሊት ባለቤቶች የሆኑት ወጥተው ወርደው ደክመው፣ መከራ መስቀልን ሳይሰቀቁና ሳይፈሩ፤ ወድደው ፈቅደው የጀመሩትን አገልግሎት በማክበር ሕይወታቸውን ለታመነው አምላክ አደራ በመስጠት የተማሩትን ፍጹም ትምህርት ለሌላው አስተምረው፣ ሠርተው ያገኙትን ለሌላው አካፍለው ወገናቸውን እንደራሳቸው አድርገው ሲመለከቱ ባለ አንድ መክሊት የተባለው ግን ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ሃይማኖቴን ሲያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡኝ ብሎ ፈርቶ ሃይማኖቱን በልቡ ከመደበቅና ከመሠወር በቀር የተማረውን ትምህርት ሠርቶ ያገኘውን ሀብት ንብረት ለሌላው ሊያካፍልና የተሰጠውን አደራም ሊወጣ አልወደደም፡፡


  በምሳሌው ውስጥ እንደተገለጠው ሁለቱ ወገኖች በተሰጣቸው መክሊት ባለሁለቱ አራት ባለአምስቱ ዐሥር ማትረፋቸውን ለጌታቸው በገለጡ ጊዜ የመክሊቱ ባለቤት እጅግ አድርጎ እንዳመሰገናቸው ከላይ አንብበናል፡፡


  ይህ የመክሊቱ ባለቤት የተባለው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የተሰጣቸውን ሓላፊነት በአግባቡና በጽንአት ለተወጡት ሁሉ እርሱ ፍጹም ዋጋን የሚሰጣቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህም ሁኔታ “አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” በሚል ታላቅ የምስጋና ቃል ተገልጧል፡፡ ይህ ቃል በሃይማኖትና በበጎ ምግባር ለእግዚአብሔር የታመኑ ሁሉ ዘለዓለማዊና ፍጹም ደስታ ወደሚገኝበት መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ለሚያደርጉት የእምነት ጉዞ እጅግ ተስፋ የሆነ ቃል ነው፡፡


  በዚህ ምንባብ ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም እርሱን የምናገለግልበትንና ለእርሱ በመታመን ዘለዓለማዊ ክብርን የምናገኝበትን ዕውቀትን፣ ማስተዋልን፣ እምነትን፣ ተስፋን፣ የሥነ ምግባር ሀብትን፣ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን እንጠቀምባቸው ዘንድ ለእኛ ለሰው ልጆች እንደየዓቅማችን መጠን ሰጥቶናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሥጋችንን ምኞት ለማስፈጸም የተሰጡ ሳይሆኑ ነፍሳችን የምትከብርበትን መልካም ሥራን የምንሠራባቸው መሣሪያዎቻችን ናቸው፡፡


  በመሆኑም እርሱ በሰጠን የአገልግሎት በር ጸጋ በታማኝነት በማገልገል በሕይወት ዘመናችን ሁሉ መንፈሳዊውን ሀብት የምናተርፍ እንሆን ዘንድ የተላለፈልን አምላካዊ ምክር ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ የተጠራነው ፍሬ ልናፈራና ሌላውንም ልናተርፍ መልካም ሥራን ልንሠራ እንጂ የሥጋችንን ፈቃድ በመከተል የኃጢአት ባሮች ልንሆን አይደለም፡፡ መጽሐፍ እንዲህ አለ “ወኲሉ ዘከመ ተጸውአ ከማሁ ለየሀሉ፤ ሁሉ እንደተጠራ እንዲሁ ይኑር” /፩ኛ ቆሮ. ፯፥፳/


  ከላይ እንደተመለከትነው በልዑል አምላክ በእግዚአብሔር አንደበት አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ መባልን የመሰለ አስደሳችና አስደናቂ ነገር የለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚገኘው ሃይማኖትን በሥራ በመግለጥ እንጂ ሃይማኖትን በልቡና በመያዝ ብቻ /ሙያ በልብ ነው/ በማለት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ከእነዚህ እንደአቅማቸው መጠን መክሊት ተሰጥቷቸው በትጋታቸውና በቅንነታቸው ሌላ መክሊት ካተረፉት በጎና ታማኝ አገልጋዮች የምንማረው እውነታም ይህ ነው፡፡ በብዙ ለመሾም ለማደግ ለመጽደቅ በጥቂቱ መታመን መፈተን መጋደል ግድ ነው፡፡


  አንድ መክሊት የተሰጠውን ሰው ስንመለከተው ጌታውን ጨካኝና ፈራጅ አድርጎ ከመቁጠር ውጪ በተሰጠው መክሊት ወጥቶ ወርዶ ሊያተርፍ አልወደደም፡፡ መክሊቱንም ባስረከበ ጊዜ በጌታው ላይ የተናገራቸው ቃላት የእርሱን አለመታዘዝና አመጸኝነት ይገልጡ ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ ሰው በጥቂቱ መታመን ያቃተውና በአስተሳሰቡ ደካማነት እጅግ የተጎሳቆለ ሰው ነው፡፡


  በዚህ ምሳሌ መሠረት ይህ ባለ አንድ መክሊት የተባለው ሰው ዓላውያን ነገሥታት እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ በማለት ሃይማኖቱን በልቡ ሸሽጎና ቀብሮ በተቀደሰ ተግባር ሳይገልጠው ከመያዙ ባሻገር በጌታ ፊት በድፍረት ቆሞ አንተ ሕግ ሳትሠራ በአእምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ፤ መምህራንንም ሳትመድብ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ በሠራችሁ ብለህ የምትፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆንክን አውቃለሁና ፈርቼ ሃይማኖቴን በልቡናዬ ይዠዋለው በአዕምሮዬ ጠብቄዋለሁ የሚል ሃይማኖቱን ግን በሥራ የማይገልጥ ሰነፍ ሰውን ያመለክታል፡፡


  ለዚህ ዓይነት ሰው የጌታ መልስ ደግሞ በምሳሌው መሠረት የሚከተለው ነው፡፡ እኔ ሕግ ሳልሠራ በአእምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ፤ መምህር ሳልሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ አውቃችሁ በሠራችሁት ብዬ የምፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆኔን ታውቃለህን? እንዲህስ ካወቅህ ሹመትክን ልትመልስልኝ ይገባኝ ነበር፡፡ ወጥቶ ወርዶ ለሚያስተምር በሰጠሁት ነበር፡፡ አሁንም የእርሱን መምህርነት ሹመት ነሥታችሁ (ወስዳችሁ) ለዚያ ለባለ ዐራቱና ለባለ ዐሥሩ ደርቡለት! እርሱን ግን አውጡት የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ከበጎ ምግባር የተለየች እምነት የሞተች እንደሆነ ተጽፏልና፡፡


  ዛሬም እያንዳንዳችን በዓቅማችን መጠን መክሊት ተሰጥቶናል፡፡ ነገር ግን መክሊቱን እንደቀበረው እንደዚያ ሰው የተሰጠንን ቀብረን ለወቀሳና ለፍርድ እንዳንሰጥ በአገልግሎታችን ልንተጋ ይገባናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ ሲገልጥ “ወዘሂ ይትለአክ በመልእክቱ፤ ወዘሂ ይሜህር በትምህርቱ. . .፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚሰጥም በልግሥና ይስጥ›› (ሮሜ. ፲፪፥፯) በማለት ተናግሯል፡፡


  ለመሆኑ አሁን ባለንበት የስግብግብነት ወቅት ዛሬ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ…›› ተብሎ በእግዚአብሔር ሊመሰገን የሚችል ሰው ማን ይሆን? በእውነት እንዲህ ተብሎ የሚመሰገን በጎና ታማኝ ካህን በጎና ታማኝ መምህር በጎና ታማኝ ምእመን ታማኝ ሰባኪና ታማኝ ዘማሪ ማግኘት ይቻል ይሆንን? ትልቅ መሠረታዊ ሊሆን የሚገባው ጥያቄ ቢኖር ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ስለታማኝነት የሁላችንንም ሕይወት የሚዳስስና ሁላችንንም የሚመለከት ነውና፡፡ ነገር ግን መቼም አምላካችን ቸር ነውና በየዘመናቱ አንዳንድ ታማኝ አባቶችን እንደማያሳጣን ተስፋ አለን፡፡


  ምክንያቱም ዛሬም ቢሆን እንደአባቶቻችን እንደቅዱሳን ሐዋርያት በእምነት፣ በትዕግሥት በፍቅር በተጋድሎ በየውሐት በትሕርምት በጸሊዓ ንዋይ በትሕትናና በትጋት በማገልገል የተሰጣቸውን መክሊት የሚያበዙ አገልጋዮች አሉ፡፡ የእነዚህ ክብራቸው በምድርም በሰማይም እጅግ የበዛና ራሳቸውን አስመስለው በትምህርት የወለዷቸው ልጆቻቸውም ለቤተ ክርስቲያን የተወደዱ የተከበሩ ልጆች ናቸው፡፡


  ለምሳሌ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ነቢየ እግዚአብሔር ኢያሱን፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ቀሌምንጦስን፣ ቅዱስ ጳውሎስም ቅዱስ ጢሞቴዎስን ለቤተ ክርስቲያን አበርክተዋል፡፡ ሌሎችም አበው ቅዱሳን በወንጌል ቃል መንፈሳውያንና ትጉሃን የሆኑ ምእመናንን በሚገባ አፍርተዋል፡፡ ያላመኑትንም አሳምነው ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመመለስ ለዘለዓለማዊ ክብር የበቁ እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል፡፡ በተሰጣቸው ጸጋም አትርፈው አትረፍርፈው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሀብተ መንፈስ ቅዱስ እንድትጎበኝ አድርገዋል፡፡ የእነርሱም በረከታቸው ረድኤታቸው ቃል ኪዳናቸው ለሌሎች እንዲተርፍ ሆኖላቸዋል፡፡


  በመሆኑም ክርስቶስ በደሙ የከፈለውን ወደር የሌለውን ዋጋ ዓለም አምኖና አውቆ ተቀብሎ በክርስትና ሃይማኖት እንዲድንበትና እንዲጠቀምበት በማድረግ እንዲሁም በታማኝነትና በበጎነት አገልግሎታቸው ጥንትም ዛሬም ላለችዋና ወደፊትም ለምትኖረዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ድምቀትም ውበትም የሆኑት ቅዱሳን አበው ሊገኙ የቻሉት ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን ደስ ለማሰኘት በመድከማቸው ሳይሆን የተጠሩበትን ዓላማና የጠራቸውን እርሱን በሚገባ አውቀውና ከልብ ተረድተው ለዘለዓለማዊ ሕይወት ተግተው በመሥራታቸው ነው፡፡ (ገላ. ፩፥፲)


  “ወይእዜሰ ለሰብእኑ ነአምን ወአኮ ለእግዚአብሔር ወእምሰኬ እፈቅድ ለሰብእ አድሉ ኢኮንኩ ገብሮ ለክርስቶስ፤ አሁንስ ለእግዚአብሔር ያይደለ ለሰው ብለን እናመናለን፤ ለሰው የማደላ ከሆንኩስ፣ የክርስቶስ ባሪያ /አገልጋይ/ አይደለሁም” /ገላ. ፩፥፲/ በማለት ያስተማረው ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ ቃል በመነሣት በተለይ ደግሞ በክህነት አገልግሎት ውስጥ ያለ ሰው ከምንም በላይ በከፍተኛ መንፈሳዊ ሓላፊነት ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን በሃይማኖትም በሥነ ምግባርም ለሌላው አርአያ በመሆን እንደ እርሱ ሃይማኖትን ከምግባር ጋር አስተባብረው የያዙ ምእመናንን ማፍራት ማብዛት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ልንባል የምንችለው፡፡


  አሁን ባለንበት ወቅት በጎና ታማኝ አገልጋይ መሆን እንዳንችል ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ የችግሮቹም መሠረታዊ ምንጭ በተጠሩበት ጸንቶ መቆም ፈጽሞ አለመቻልና ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ በማድላት ሓላፊነትን መዘንጋት ናቸው፡፡ በሥጋዊ አምሮት ፍላጎትና ምርጫ ውስጥ ደግሞ መንፈሳዊ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት የሚያስችለንን የታማኝነት ሥራን መሥራት አይቻልምና በታማኝነት ከምናድነው ሰው ይልቅ መክሊታችንን በመቅበር ባለመታመን መሰናክል የምንሆንበት ሰው ሊበዛ እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡


  በመሆኑም ከእርሱ ዘንድ እንደ ዓቅማችን የተሰጠንን መንፈሳዊ ዕውቀት ሀብትና አገልግሎት ለሌላው በማድረስ መክሊታችንን ልናበዛ የምንችለውና አገልግሎታችን ወይም ክርስትናችን ውጤታማ የሚሆነው ምርጫችንን አውቀን እንደቃሉ ሆነንና ጸንተን ስንገኝ ብቻ ነው፡፡ ይህ ባለመሆኑ ነው ዛሬ ብዙዎቻችን በሕይወታችን ሌላውን ማትረፍ አቅቶን በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ በሚያስወቅስ የስንፍና መንገድ ላይ ቆመን የምንገኘው፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ‹‹ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ›› (ማቴ. ፳፬፥፵፪) ብሎናል፡፡


  ቃሉን የሰማንና የምናውቅ ሁላችን በሞቱ ላዳነን፣ በልጅነት ጸጋም ላከበረን፣ በትንሣኤውም ላረጋጋን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ከራሱ ጋር ላስታረቀን፣ በውኂዘ ደሙም ሕይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በረከትንና ዘለዓለማዊ ደስታን ለሰጠን አምላካችን በመታዘዝ አቅማችን በሚፈቅደው አገልግሎት ጸንቶ መገኘት ተገቢ ነው፡፡ በአገልግሎት የመጽናት ምልክቱ ደግሞ አትራፊነት ነው፡፡ ቅዱሳን ነቢያት፣ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ በአትራፊነት ይታወቃሉ፡፡ ለማትረፍ ግን ራሳቸውን ለእውነት ለአገልግሎት ለመከራ አሳልፈው በመስጠት ነው፤ በትንሹ መታመን ሲባል የእኛ አገልግሎት ከፈጣሪ ቸርነት ጋር ስለማይመጣጠን ነው፤ በብዙ እሾምሃለሁ ማለቱም በመንግሥተ ሰማያት ለዘለዓለም ከብሮ መኖርን ነው፡፡


  ከቅዱሳን ነቢያትም ሐዋርያትም ሰብአ አርድእትም ሊቃውንትም የሰማነውና ያየነው እውነት ምንጊዜም ትጉህ ሠራተኛ የሚሠራው መልካም ሥራ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዘመን ልዑል እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን፤ ምእመናንን፤ ሀገርንና ሕዝብን ለመምራት የጠራንና የመረጠን፤ በአገልግሎት ዐደባባይ ያስቀመጠን ሰዎች እጅግ ዕድለኞች ነን፤ ምክንያቱም የሕዝብን ችግርና አቤቱታ ሰምቶ ተቀብሎ መፍትሔ መስጠት ትርፋማነት ነውና፤ ትርፋማነት ደግሞ ወደ ትልቁ የሹመት መሰላል መውጣት ነው፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አገልግሎታችን ተደናቅፎ የሕዝባችን ችግር ሳይፈታ ቀርቶ የአገልግሎታችን ተቆጣጣሪ አምላካችን ቢጎበኘን “አንተ ሰነፍ አገልጋይ” ተብለን ወደ ውርደት አዘቅት እንዳንላክ መጠንቀቁ አይከፋም፡፡ የመሾም የመሻር የማሳደግና የማውረድ ሥልጣን የእግዚአብሔር ነውና፡፡ “ከእናንተ መካከል አንዱን እንኳ እንዳናስቸግር ቀንም ሌሊትም እንሠራ ነበር” /፩ኛ ተሰ. ፪፥፱/ በጎና ታማኝ አገልጋዮች ሆነን እንድንገኝ ጠንክረን ልንሠራ ይገባናል፡፡


  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  Read more »

 • ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ማቴ 24÷44

  መጋቢት 05 ቀን 2007ዓ.ም


  ዲ/ን ተመስገን ዘገየ

  ይህ ቃል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ለደቀመዛሙርቱ ስለ ዳግመኛ ምጽአቱና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምልክቶች ሲጠይቁት የተናገረው ኃይለ ቃል ነው፡፡ “ወእንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ቀርቡ ኀቤሁ አርዳኢሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ ቀረቡና እንዲህ አሉት፤ ንግረነ ማእዜ ይከውን ዝንቱ ወምንትኑ ተአምሪሁ ለምጽአትከ፣ ንገረን ይህ መቼ ይሆናል የዓለም ፍጻሜ ምልክቱስ ምንድን ነው?” አሉት፡፡

  ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግሮ የሚገኝ ታላቅ ተራራ ነው፡፡ 800 ሜትር ያህል ከባሕር ጠለል በላይ ከፍታ አለው፡፡ ቤተፋጌና ቢታንያም ከግርጌው የሚገኙ መንደሮች ናቸው፡፡ ደብረ ዘይት ስያሜውም የተሰጠው በላዩ ከሚበቅሉት (ተራራውን ከሸፈኑት) የወይራ ዛፎች የተነሳ ነው፡፡ ደብረዘይት ማለት የወይራ ዛፍ የመላበት (በብዛት የሚገኝበት) ተራራ ማለት ነውና፡፡

  የደብረ ዘይት ተራራ ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደ ተራራ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመንም ዳዊት ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት እንደወጣ በ2ኛ ሳሙ 5 “ዳዊትም ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ” ይላል፡፡ ይህ ተራራ በሕዝቅኤል ትንቢት ስብሐተ እግዚአብሔር እንደሚያርፍበት ተነግሮአል፡፡ የእግዚአብሔር ክብርም ከከተማይቱ መካከል ተነሥቶ በከተማይቱ ምሥራቅ በኩል በአለው ተራራ ላይ ቆመ፡፡ ት.ሕ11፤23

  ዘሩባቤል ከሠራው ቤተ መቅደስ ዐደባባይ ደብረ ዘይት 75 ሜትር ገደማ ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡ ቤተ ፋጌና ቢታንያም የሚበሉት ታሪካውያን ቦታዎች ከደብ ረዘይት ግርጌ ይገኛሉ፡፡

  ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሳዕና ዕለት ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም እንደገባ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 11፡1 ላይ “ወአልጺቆሙ ኢየሩሳሌም ኀበ ቤተ ፋጌ ወቢታንያ በኀበ በደብረ ዘይት ፈነወ ክልኤተ እምአርዳኢሁ ፤ወደ ኢየሩሳሌም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወደ አሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ ከደቀ መዘሙርቱ ሁለቱን ላከ” ይላል፡፡ አይሁድም ጌታን የያዙት በደብረ ዘይት ተራራ ግርጌ በምትገኘው ጌቴሴማኒ ነው፡፡

  “አንቢቦሙ ወሰቢሖሙ ወጽኡ ወሖሩ ውስተ ደብረ ዘይት ወእምዝ ይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ኵልክሙ ትክሕዱኒ በዛቲ ሌሊት፣ መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ” አላቸው፡፡ (ማቴ. 26፡30)

  ጌታችንም ሲያስተምር ውሎ ማታ ሔዶ የሚያድረው በደብረዘይት ተራራ ውስጥ ባለችው ኤሌዎን ዋሻ ውስጥ ነበር፡፡ በዕለተ ሆሳዕናም ከኢየሩሳሌም ሲወጡ የገባውም ወደ ደብረ ዘይት ነው፡፡ ማር 11፤1 በዚህ ዓለም የፈጸመውን አገልግሎት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሰማይ ያረገውም በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ ወደፊትም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል ተብሎ የተነገረው ትንቢት ላይ መገለጫው ደብረ ዘይት እንደሆነች ተገልጿል፡፡ እነሆ እግዚአብሔር ቀን ይመጣል ብዝበዛሽንም በውስጥ ይከፍላሉ፡፡ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምን ይወጉአት ዘንድ እሰበስባለሁ ከተማይቱም ትያዛለች፡፡ (ት. ዘካ. 14፤1)

  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ምጽአቱ (ዳግም ምጽአቱ በደብረ ዘይት ተራራ) ላይ በሰፊው አስተምሯል፡፡በቤተመቅደስ ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስና እንድርያስም ለብቻ ጠየቁት፡፡ እንዲህም አሉት ንገረን ይህ መቼ ይሆናል(ማር 13፤3፣ ማቴ 24፤1-51) ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቡነ ዘበሰማያት የሚለውን ጸሎት ያስተማረውም በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡

  ከ62 ሀገሮች በላይ ልሳን(ቋንቋ) በሞዛይክ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ግእዝ ነው፡፡ በመሆኑም 5ኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት የክርስቶስ ነገረ ምጽአት የሚዘመርበት የሚሰበክበት ዕለት ስለሆነ በደብረ ዘይት ተሰይሟል፡፡ ሰያሚውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በዕለቱ የሚነበበው የወንጌል ክፍልም ማቴ 24፤1-36 ነው፡፡

  ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት በሄደበት ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ አጠገቡ ቀርበው ዘሩባቤል ያሳነፀውን የመቅደስ ግንቦች እያሳዩት ቀረቡ፡፡

  “አማን እብለክሙ ኢይትኀደግ ዝየ እብን ዲበ እብን ዘኢይትነሠት፣ እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የኢየሩሳሌምን መፍረስና ዳግም መምጣትን አስፍቶ አምልቶ ከነምልክቱ ለደቀ መዛሙርቱ አስተማራቸው፡፡ ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆንባቸው በሰማያዊ ንጉሥ ፊት ያለ ምክንያት ለፍርድ እንዲቆሙ የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ወንጌል በአህዛብ ቤት ሳይቀር ለሁሉም ይሰበካል፡፡ በዚህ ጊዜ መጨረሻው እየቀረበ ይመጣል፡፡ (ማቴ.24፤14) በማለት በስፋት አስተምሮአቸዋል፡፡” እምበለስ አእምሩ አምሳሊሁ፣ ነገሩን በበለስ እወቁ፡፡

  የበለስ ቅጠል መለምለም ማለት የጠፋችው እስራኤል መንግሥት መመሥረት የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት 11ኛ ምልክት ነው፡፡ ማቴ 24፤32

  ከዚህ በኋላ በማናውቀው ጊዜና ሰዓት እግዚአብሔር ወልድ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት (በአካላዊ መጠን) ከቅዱሳን መላእክት ጋር በደመና ይመጣል፡፡ “ናሁ ይመጽእ በደመና ሰማይ ወትሬእዮ ኩላ ዐይን ወእልክቱሂ እለ ወግእዎ ይበክዩ በእንቲአሁ ኩሎሙ አሕዛበ ምድር እወ አማን፣ እነሆ በሰማይ ደመና ይመጣል ዐይን ሁሉ ታየዋለች የወጉትም ሁሉ ያለቅሳሉ የምድር ወገኖች ሁሉ የኀዘን ድምፅ ያሰማሉ፡፡ አሕዛብ ሁሉ ስለ እርሱ ያለቅሳሉ፡፡ (ራእይ 1፤7)

  ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዳግም ምጽአቱ በተናገረበት አንቀጹ ቅዱሳን ሐዋርያትን ካስጠነቀቀበት ዐቢይ ኃይለ ቃል መካከል ስለ ሐሰተኞች መምህራን መምጣት ነበር፡፡ “እስመ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወያስሕትዎሙ ለብዙኃን” የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ በማለት (በማቴ 24፤5) አስጠንቅቋል፡፡

  ክርስቲያኖች አሁንም በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች ከሆኑት ከሐሰተኞች መምህራን ተጠበቁ፡፡ ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማል? በማለት እውነተኛ የወንጌል መምህራንን በመምሰል ብዙዎችን እንደሚያሳስቱ ጌታችን አስተምሮናል (ማቴ 7፤15) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ 16፤17 “ነገር ግን ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትና ማሰናከያ የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምንቹሃለሁ፡፡ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግር ተንኰል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉና››ይላል፡፡

  የእስክንድርያው ሊቀጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረ “እኛስ ያለማወላወል የደጋግ አባቶችን ሃይማኖት እንይዛለን” (ሃይማኖተ አበው) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያውን እምነታችን እስከመጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተከፋዮች ሆነናልና፡፡ (ዕብ 3፤14) ይላል፡፡ ስለዚህ በጊዜው ያለ ጊዜውም መጽናት ይገባል (2ኛ ጢሞ4.2)

  የዓለም መጨረሻውና የኢየሱስ ክርስቶስ መምጫ ምልክቶች በማቴ 24፤1 በስፋት ተዘርዝረዋል፡፡

  ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ታላላቅ ምጽአቶችእንዳሉት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “….በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሥዋት ኃጢአት ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል… አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ ያድናቸውም ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታዩላቸዋል (ዕብ 9፤26-28 ) በማለት ተናግሮአል፡፡

  የመጀመሪያው ምጽአቱ ሥጋ በመልበስ ለሰው መሥዋዕት ሁኖ ሊያድን ለካሳ በፍጹም ትህትና የእኛን ውርደት ተቀብሎ በበረት በመወለድ በሥጋ ማርያም መጣ፡፡ በሚሞት በሚሰደድ በሚዳከም ፤በሚበረታ፤ በሚራብ፤ በሚጠማ ፤ በሚዝል በሚወድቅ በሕርየ ሰብእ (የሰው ባሕርይ) እንደ አንድ ኃጥእ ሞት፣ እስኪፈረድበት ድረስ ራሱን ዝቅ አድርጐ መጣ፡፡

  ወንጌለ መንግሥቱን ሊሰብክልን ከሞት ወደ ሕይወት ሊያሸጋግረን በሥጋ ማርያም መጣ፡፡ ከአይሁድ ስድብን ታገሠ ኃጥአንን በሽተኞችን ሊያድን በምድር ላይ ተመላለሰ፡፡ ስለ እኛ ተገረፈ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ያውም መራራ ለሆነ የመሰቀልሞት ታዘዘ፡፡ ሞቶ በሦስተኛው ቀን ተነሳ ወደ ሰማይም በዐርባኛው ቀን አረገ በየማነ አብ ተቀመጠ፡፡ይህ ነው የመጀመሪያው ምጽአቱ መከራን ለመቀበል እኛን ለማዳንና ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ለመግለጥ ነው፡፡


  ዳግማዊ ምጽአቱ፡- በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በፍጹም ጌትነት በኃጥአን (የመጀመሪያ ምጽአቱን) ባልተቀበሉት ላይ ሊፈርድ ዐይን ሁሉ እየተመለከተው በገሃድ ይመጣል፡፡ ‹‹እግዚአብሔርስ ገሀደ ይመጽእ ወአምላክነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፣ እግዚአብሔር ግልጥ ሁኖ ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል (መዝ 49፡3)

  መጥቶም ዝም አይልም (ኤሌ ለክሙ ጸሐፍት ወፈሪሳውያን መደልዋን፤ ግብዞች ጸሐፍት ፈሪሳውያን ወዮላቸሁ) እያለ ይወቅሳል ወንጌልንም ያስተምራል፡፡ ጻድቃንን “እናንተ የአባቴ ብሩካን ወደ እኔ ኑ ብሎ ይጠራል ኃጥአንንም እናንተ ርጉማን ሐሩ እምኔየ፤ ከእኔ ወግዱ” ብሎ ያሰናብታቸዋል፡፡ በፊቱ እሳት ይነዳል ማለት ጻድቃን የሚድኑበት ሕይወት ኃጥአን የሚጠፉበት መዓት በባህርዩ አለ ማለት ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሆይ! የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛ መገለጥ ለእኛስ ለምን ይሆን? ለዘለዓለማዊ ሕይወት ወይስ ለዘለዓለም ሞት?

  ጌታችን በደብረ ዘይት ያስተማራቸው ትምህርቶች በመሠረታዊነት በ3 ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡

  1. ምልክት (በዚያ ዘመን እንዲህ ይሆናል እያለ በፍጻሜ ዘመን የሚከሰቱትን ድርጊቶች

  2. ትእዛዝ (በዚያ ዘመን ከጥፋት እንድን ዘንድ የሰጠን አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ እያለ ፡፡

  3. ማስጠንቀቂያ በፍጻሜ ዘመን እንዲህ ሁናችሁ የተገኛችሁ ‹‹ወዬላችሁ›› እያለ የተናገራቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ምሳሌ “ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው” የሚለው እርጉዝ ማለት የኃጢአት ዐሳብ የጸነሱት ሲሆኑ የሚያጠቡ ያላቸው ኃጢአትን ጸንሰው በንግግር የወለዱትን ነው፡፡


  በይሁዳ ያሉት ወደተራሮች ይሽሹ (ማቴ 24፤16) በዚህ ቃል መሠረት በይሁዳ በዓለም ያሉ ወደ ተራራ ይሽሹ ተብሏል፡፡ በሃይማኖት ጸንተው ምግባር ትሩፋት እየሠሩ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ወደ ተራራ ይሽሹ ነው፡፡


  ተራራ ምንድን ነው?


  1. ተራራ የተባለው ረድኤተ እግዚአብሔር ነው፡፡ “ተራሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው” መዝ. 124፤2 ይላል በዚህ ቃል የእግዚአብሔር ረድኤት በተራራ ተመስሎ ቀርቧል፡፡ ምክንያቱም ተራራ እንደሚከልል እግዚአብሔርም በረድኤቱ ይከልላልና፡፡ ስለዚህ ወደ ተራራ ሽሹ ማለት ረድኤተ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጉ ማለት ነው፡፡


  2. ተራራ የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ድንግል ማርያም የጽዮን ተራራ ትባላለች “አንሰ ተሠየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ፣ በጽዮን በደብረ መቅደሱ ፤እኔ ግን በእነርሱ ላይ ንጉሥ ሆኜ ተሾምሁ በተቀደሰው ተራራ ላይ በጽዮን ላይ” መዝ.2፤6 ስለዚህ ትውልድ ድንግል ማርያምን ዓምባ መጠጊያ ያደርግ ማለት ነው፡፡

  3. ተራራ የተባሉት ቅዱሳን አባቶቻችን ናቸው፡፡ መዝ.86፤1 መሠረታቲሃ ውስተ አድባረ ቅዱሳን ፤መሠረቶቿ በቅዱሱ ተራሮች ናቸው” ስለዚህ ወደ ተራራ ሽሹ ማለት ወደ ቅዱሳን አባቶቻችን ቅረቡ በአማላጅነት ስልጣናቸው አምናችሁ ተማጸኗቸው ሲል ነው፡፡

  በሰገነት ያለውም በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ ይላል (ማቴ 24፤17) ሰገነት ከፍ ያለ ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቃል በሠገነት የተመሠለ በምግባር በሃይማኖት የበረታ የወጣትነት ዘመን አልፎ ከማዕከላዊነት የደረሰ ማለት ሲሆን በዝቅታ የተመሠለ ደግሞ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ የነፍስ ተዋርዶ ነው፡፡

  ዴማስና ይሁዳ በሰገነት ነበሩ በኋላ ግን በዝቅታ ሥፍራ ተገኙ፡፡ መዋል በማይገባቸው ቦታ ውለው ተገኙ፡፡ በክርስትና ከፍ ከፍ ብለው በመንፈሳዊነት መጽናት አቃታቸው፡፡ እኛስ ከየትኛው ስፍራ እንሆን?

  በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላ አይመለስ (ማቴ 24፤18 ) በእርሻ የተመሰለ የመነነ ወይም በምንኩስና ሕይወት ያለ ማለት ነው፡፡ በእርሻ ያለ አይመለስ ማለት በምነና በምንኩስና ያለ ይህንን ሕይወት የጀመረ አይመለስ፡፡ ስለዚህ ስደታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ተግታችሁ ጸልዩ አለ (ማቴ 24፤20) ክረምት የፍሬ የአጨዳ ሳይሆን የሥራ የመዝሪያ ወቅት ነው፡፡ ሰንበትም የዕረፍት ቀን ናት በሠንበት ሥጋዊ ሥራ አይሠራም፡፡ አንድም በክረምት ቅጠል ካልሆነ ፍሬ አይገኝም እናንተም ሃይማኖት ይዛችሁ ምግባር ከሌላችሁ ዋጋ የላችሁም ማለቱ ነው፡፡

  ሽሽት የተባለ ዕለተ ምጽአት ሲሆን በሽሽት የተመሰለው ሞት ድንገት እንደሚመጣ ዕለተ ምጽአትም በድንገት ስለሚሆን ነው፡፡ ትርጉሙ ንስሓችሁን ሳትጨርሱ የንስሐ ፍሬ ሳታፈሩ በድንገት ዕለተ ምጽአት እንዳይደርስባችሁ ጸልዩ የሚል ይሆናል፡፡ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ሲኖር “ድልዋኒክሙ ንበሩ ፤ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” ማቴ 24፤24 በተባለው አማናዊ ቃል መሠረት ራሱን በንስሓ አዘጋጅቶ የጌታውን መምጣት ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡

  ምንጭ፤ ማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ

  Read more »

 • መፃጉዕ ( የዐቢይ ጾም ዐራተኛ ሳምንት)

  የካቲት 29 ቀን 2007 ዓ.ም.

  ምንባባት

  የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

  አምላኩሰ ለአዳም ለዕረፍት ሰንበተ ሠርዓ፤ ወይቤልዎ አይሁድ በዓይ ሥልጣን ትገብር ዘንተ ወይቤሎሙ ኢየሱስ አነኒ እገብር አንትሙኒ፤ እመኑ ለግብርየ ወይቤሎሙ አነ ውእቱ እግዚኦ ለሰንበት እግዚኦ ውእቱ ለሰንበት ወልድ ዋሕድ ወይቤሎሙ ብውህ ሊተ፤ እኅድግ ኃጢአተ በዲበ ምድር እስበክ ግዕዛነ ወእክሥት አዕይንተ ዕውራን አቡየ ፈነወኒ፡፡


  ትርጉም: “የአዳም ፈጣሪ ለዕረፍት ሰንበትን ሠራ፤ አይሁድም በማን ሥልጣን ይህን ታደርጋለህ አሉት፤ እርሱም እኔ እሠራለሁ እናንተም ሥራዬን እመኑ አላቸው፡፡ የሰንበት ጌታው እኔ ነኝ፤ የሰንበት ጌታው/የአብ/ አንድያ ልጁ ነው፡፡ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር እል ዘንድ ፣ ነፃነትን እሰብክ ዘንድ ተሰጥቶኛል ፣ የዕውራንን ዓይን አበራ ዘንድ አባቴ ልኮኛል አላቸው፡፡” ማለት ነው፡፡


  መልእክታት

  (ገላ. 5÷1-ፍጻሜ ምዕ.)፡- እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ፡፡ እነሆ÷እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፤ “ብትገዘሩም በክርስቶስ ዘንድ ምንም አይጠቅማችሁም፡፡” ደግሞም ለተገዘረ ሰው ሁሉ የኦሪትን ሕግ መፈጸም አንደሚገባው እመሰክራለሁ፡፡ በኦሪት ልትጸድቁ የምትፈልጉ እናንተ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋዉ ወድቃችኋል፡፡ እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ÷ በእምነትም ልንጸድቅ ተስፋ አናደርጋለን፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በፍቅር የምትሠራ እምነት እንጂ መገዘር አይጠቅምምና፤ አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምምና፡፡ ቀድሞስ በመልካም ተፋጠናችሁ ነበር፤ በእውነት እንዳታምኑ ማን አሰናከላችሁ? ይህ መፋጠናችሁ ከሚጠራችሁ አይደለምና፡፡ ጥቂት እርሾ ብዙውን ዱቄት መጻጻ ያደርገው የለምን? እኔ ሌላ እንዳታስቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኛችሁ ነበር፤ የሚያውካችሁ ግን የሆነው ቢሆን ፍዳውን ይሸከማል፡፡ ወንድሞቼ ሆይ÷ እኔ ግዝረትን ገና የምስብክ ከሆነ÷ እንግዲህ ለምን ያሳድዱኛል? እንግዲህ የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት እንዲያው ቀርቶአል፡፡ የሚያውኩአችሁም ሊለዩ ይገባል፡፡

  ወንድሞቼ ሆይ÷ እናንተስ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን በሥጋችሁ ፈቃድ ለነጻነታችሁ ምክንያት አታድርጉላት፤ ለወንድሞቻችሁም በፍቅር ተገዙ፡፡ “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈጽማልና፡፡ እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትንካከሱ ከሆነ ግን÷ እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ፡፡ እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ኑሩ እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ፡፡ ሥጋ መንፈስ የማይሻውን ይሻልና÷ መንፈስም ሥጋ የማይሻውን ይሻልና የምትሹትንም እንዳታደርጉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፡፡ የመንፈስን ፈቃድ የምትከተሉ ከሆናችሁ÷ ከኦሪት ወጥታችኋል፡፡ የሥጋም ሥራው ይታወቃል፤ እርሱም ዝሙት÷ ርኲሰት÷ መዳራት÷ ጣዖት ማምለክ÷ ሥራይ ማድረግ÷ መጣላት÷ ኲራት÷ የምንዝር ጌጥ÷ ቅናት÷ቊጣ÷ ጥርጥር÷ ፉክክር ÷ምቀኝነት መጋደል÷ ስካር ይህንም የመሰለ ሁሉ ነው፡፡ አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር÷ ደስታ ÷ሰላም÷ ትዕግሥት÷ ምጽዋት÷ ቸርነት÷ እምነት÷ ገርነት÷ ንጽሕና ነው፡ ከዚህ ሕግ የሚበልጥ የለም፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ግን ሰውነታቸውን ከምኞትና ከኀጢአት ለዩ፡፡ አሁንም በመንፈስ እንኑር፤ በመንፈስም እንመላለስ፡፡ ኩሩዎች አንሁን፤ እርስ በርሳችን አንተማማ፤ እርስ በርሳችንም አንቀናና፡፡ 

  (ያዕ.5÷14- ፍጻሜ ምዕ.)፡- ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቅቡት፡፡ የሃይማኖት ጸሎትም ድውዩን ይፈውሰዋል፤ እግዚአብሔርም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል፡፡ እርስ በርሳችሁ ኀጢአታችሁን ተናዘዙ፤ እንድትድኑም ለወንድሞቻችሁ ጸልዩ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎቱ ብዙ ትረዳለች፤ ግዳጅም ትፈጽማለች፡፡ ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበር፤ እንደምንታመምም ይታመም ነበር፤ ዝናም እንዳይዘንም ጸሎትን ጸለየ፤ ሦስት ዓመት ከስድስት ወርም በምድር ላይ አልዘነመም፡፡ ዳግመኛም ጸለየ፤ ሰማይም ዝናሙን ሰጠ፤ ምድርም ፍሬዋን አበቀለች፡፡ ወንድሞቻችን ሆይ÷ ከእናንተ ከጽድቅ የሳተ ቢኖር÷ ከኀጢአቱ የመለሰውም ቢኖር÷ ኀጢአተኛውን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ራሱን ከሞት እንደ አዳነ÷ ብዙ ኀጢአቱንም እንዳስተሰረየ ይወቅ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድም የሐዋርያው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት ተፈጸመች፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡

  ግብረ ሐዋርያት

  (የሐዋ.3÷1-11)፡- ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ነበር፤ ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁል ጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋት በመቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር፡፡ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም ወደ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡ ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ተመለከተውና “ወደ እኛ ተመልከት” አለው፤ ወደ እነርሱም ተመለከተ፤ ምጽዋት እንደሚሰጡትም ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ጴጥሮስም÷ “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ÷ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ በቀኝ አጁም ይዞ አስነሣው፤ ያን ጊዜም እግሩና ቊርጭምጭምቱ ጸና፡፡ ዘሎም ቆመ፤ እየሮጠና እየተራመደም ሄደ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ሕዝቡም ሁሉ እግዝአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፡፡ እርሱም መልካም በምትባለው በመቅደስ ደጃፍ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እንደ ሆነ ዐወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መገረምና መደነቅ ሞላባቸው፡፡

  ምስባክ

  መዝ.40÷3 “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፡፡ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቢ /ቤ/ሁ እምደዌሁ አንሰ እቤ እግዝኦ ተሣሃለኒ

  ትርጉም፦ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል፡፡

  ወንጌል

  (ዮሐ. 5÷1-24)፡- ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት፡፡ በዚያም ዕውሮችና አንካሶች÷ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃዉን በሚያናውጠው ጊዜ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና፡፡ በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ይህን ሰው በአልጋዉ ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደ ቆየ ዐውቆ÷ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ ድውዩም መልሶ÷ “አዎን ጌታዬ ሆይ÷ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያዉ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው፡፡ ጌታችን ኢየስስም÷ “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያውኑም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያች ቀንም ሰንበት ነበረች፡፡ አይሁድም የዳነውን ሰው÷ “ዛሬ ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አይገባህም” አሉት፡፡ እርሱም መልሶ÷ “ያዳነኝ እርሱ፡- አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው፡፡ አይሁድም÷ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና÷ “እነሆ÷ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ” አላቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው” በማለት ብቻ አይደለም፤ ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል” በማለት ነው እንጂ፡፡

  ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል፡፡ አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል፡፡ አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸው÷

  ምንጭ፤ ማኅበረ ቅዱሳን ድህረ ገጽ

  ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም፡፡

  Read more »

 • ዐቢይ ጾም

  ይህ ጾም የተለያዩ ስሞች አሉት፡፡
  1. ዓቢይ ጾም ይባላል፡- ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የዓርባ ቀን ጾም በመሆኑ እንዲሁም ዓቢይ እግዚአብሔር ወብዙኃ አኮቴቱ ዓቢይ እግዚአብሔር ወዓቢይ ኃይሉ የተባለ ጌታ የጾመው ስለሆነ መዝ. 47፡1፣ መዝ. 146፡5 ፡፡

  2. ሁዳዴ ጾም ይባላል፡- ሁዳድ ማለት ሰፊ የመንግሥት እርሻ ወይም ማንኛውም የሕዝብ ብዛት ያለበት ሥራ ሁሉ ሁዳዴ የሚባል ሲሆን፤ የሁዳዴ ጾም የተባለውም በጾም ቀናት 55 ቀናት ስለሚጾምና ጾሙንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጾመው ነው፡፡አሞ. 7፡1

  3. በዓተ ጾም ይባላል፡- ይህም ማለት የጾም መግቢያ፣ መባቻ ወይም ጾሙ የሚሰፍርበት በዓት ማለት ነው፡፡

  4. ጾመ አርባ ይባላል፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓርባ ቀን ስለ ጾመው ነው፡፡ ማቴ. 4፤1

  5. ጾመ ኢየሱስ ይባላል፡- ይህም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ ጹሙ ብሎ ስላዘዘን

  6. ጾመ ሙሴ ይባላል፡- ይህ ደግሞ ቅዱስ ያሬድ በዘወረደ ሰኞ ዕዝል ከመዝ ይቤ ሙሴ . . . ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት . . . እያለ በጾመ ድጓው ስለ ዘመረ ነው፡፡

  ዓቢይ ጾም መሠረቱ ጌታችን የጾመው 40 ቀን ሆኖ ከመነሻው በፊት አንድ ሳምንትና ከመጨረሻው በኋላ ደግሞ አንድ ሣምንት ታክሎበት /ተጨምሮበት/ 55 ቀኖች የምንጾመው ጾም ዓቢይ ጾም ይባላል፡፡ የመጀመሪያው አንድ ሳምንት የዝግጅትና የመለማመጃ ጊዜ ሲሆን፣ የመጨረሻው አንድ ሳምንት ደግሞ የጌታችን ሕማማት ሳምንት ለማስታወስ ነው፡፡ በሌላ በኩል የመጀመሪያው ሳምንት ሕርቃል ከተባለ ንጉሥ ጋር በማያያዝ ጾመ ሕርቃል የሚባል ስም መሰጠቱ የተለመደ ነው፡፡

  ጾም፡- ጾመ፤ ጦመ፤ እህል ውሃ ሳይቀምስ ዋለ፤ ከሥጋ ከቅቤ ተከለከለ ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ጾም ከፍተኛ ቦታ ያለው ሲሆን፤ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህልና ውኃ በአፋቸው አይገባም ነበር፡፡ /ዘጸ. 34፤28/ በኃጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር፡፡ ዮናስ 2፤7-10

  በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥራው መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው፡፡ /ማቴ. 4፤2፣ ሉቃ. 4፤2/ ይህም ብቻ ሳይሆን በቁራኝነት አብሮ የሚኖር መንፈስ ርኩስ ሰይጣን፤ በጾም የሚወገድ መሆኑን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል፡፡ /ማቴ.17፡21፣ ማር. 9፡2 ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም በየጊዜው ከመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ የሚቀበሉት በጾም እና በጸሎት ላይ እንዳሉ ነበር፡፡ /ሐዋ.ሥራ 13፤2/ ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስትም የሚሾሙት በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ /የሐዋ. ሥራ 13፤3፣ 14፤23/ እነ ቆርኔሌዎስ ያላሰቡትን ያዩና ያገኙ የነበረው በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ለምነው ነው፡፡

  በጾም ወራት ላምሮት፣ ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የሆኑ፤ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ ሥጋና የሚያሰክሩ መጠጦችን /ዳን. 10፤2-3/ ቅቤና ወተት /መዝ. 108፤24/ ማራቅ እንዳለብን ታዝዟል፡፡ ባልና ሚስት በጦም ወራት በአልጋ አይገናኙም፡፡ /1ኛ ቆሮ. 7፤5፣ 2ኛ ቆሮ. 6፤6/ በጾም ወራት ከመባልዕት መከልከል ብቻ ሳይሆን ዓይን ክፉ ከማየት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር፤ ጆሮ ክፉ ከመስማት መቆጠብ እንደሚገባ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው፤ ይጹም ዓይን፣ ይጹም ልሳን፣ እዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ሕሡም በተፋቅሮ ሲል ይገልጽልናል /ያስረዳናል፡፡/

  ዐቢይ ጾምን በተመለከተ ቀደም ሲል ወንጌላውያን የጻፉትን የጌታችን ጾም እንደሚከተለው እናያለን፡፡ /ማቴ. 4፡1-11፣ ሉቃ. 4፡1-13/ ኪዘያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፡፡ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ፡፡ ከተጠመቀ በኋላ መሄዱ እናንተም ተጠምቃችሁ ሳትውሉ ሳታድሩ ዕለቱን ጽኑ ሥራ ሥሩ፣ ለገድል ለትሩፋት ተዘጋጁ በማለት ለአብነት ለማስተማር ዕለቱን ሂዷል፡፡ ወደ ገዳም መሄዱም በብቸኝነት ባለበት በገነት አዳም ድል ተነስቶ ነበርና እርሱም በብቸኝነት ገዳም ውስጥ ተገኝቶ ዲያብሎስን ድልን ለመንሳት ነው፡፡ /ማቴ. 12፤29/

  ዘወረደ፡- 
  የዓቢይ ጾም መግቢያ የሆነው የሰኞ ዋዜማ እሁድና ከእርሱ ጋር ተያይዞ ያለው የሚቀጥለው ሳምንት “ዘወረደ” ይባላል፡፡ ዘወረደ የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ መውረዱን የሚያመለክተው የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበት ስለሆነ ነው፡፡

  ያ በሰማያት የሚኖረው በእሳትና መብረቅ፣ በከባድ ደመናና ነጎድጓድ፣ በበረታ የቀንደ መለከትም ድምፅ ወደ ምድር የወረደውና በሙሴ መሪነት በምድረ በዳ ለሚጓዙት ለእስራኤል ልጆች በሲና ተራራ የተገለጠው እግዚአብሔር ብለን የምንጠራው ፈጣሪና የማይታየው አምላክ በመጨረሻ ዘመን በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ሰው ሆኖና በበረት ተወልዶ፣ የመስቀል መከራን ተቀብሎና ሞቶ ተቀብሮና ተነስቶ ፍጥረተ ዓለሙን ከዲያብሎስ አገዛዝ ከኃጢአት ቀንበርና ከሞት ፍዳ ሊያድን ከሰማየ ሰማያት ወረደ ማለት ነው፡፡

  እንዲሁም ሙሴ በኢየሱስ ክርስቶስና በድንግል ማርያም ምሳሌ ከእግዚአብሔር የተሰጡትን ቃላት፣ ትእዛዛትና / ጽላት/ ይዞ ከሲና ተራራ ወደ እስራኤል ሕዝብ የመውረዱን ዝክረ ነገር ለማስታወስ ዘወረደ ተባለ፡፡

  አምላክ አዳምን ለማዳን ከሰማይ መውረዱን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱንና በመስቀል መስቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡ /ዘፀ. 3፤9፣ ዮሐ. 3፤11/ ሙሴኒም ይሉታል፡፡ ስለ ሙሴ ሕግና ጾም ሙሴን እየደጋገመ ስለሚያነሳ ነው፡፡ 
  በዚህም መሠረት የዓቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ተባለ፡፡

  ጾመ ሕርቃል፡-
  ይህ ሳምንት በሕርቃል ስም የተጠራበት ምክንያት በ714 ዓ.ም ሕርቃል የኤራቅሊዮስ/ የቤዛይንታን ንጉሥ በነበረበት ዘመን፤ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታችንን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ እርሱ ወደ ፋርስ ዘምቶ መስቀሉን ከእነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡

   ከመዋጋቱ በፊት ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ነፍስ የገደለ ሰው እስከ እድሜ ልኩ ይጹም ብለው ሥርዓት ሠርተው ነበርና እርሱም ጾሙን ፈርቶ ነበርና በኢየሩሳሌም የነበሩ ምዕመናን ይህን ሀሳብ ደግፈው የአንድ ሰው እድሜ ቢበዛ ሰባ ሰማንያ ነው፡፡ ጠላታችንን አጥፋልን እንጂ ጾሙን እኛ ተከፋፍለን እንጾማለን ባሉት መሠረት አምስት አምስት ቀን ተከፋፍለው ጹመውለታል፡፡ ያላወቁት አንድ ጊዜ ጹመው ትተውታል፡፡ ያወቁት ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጹመውታል ብለው ሥርዓት አድርግው በዓመት በዓብይ ጾም መጀመሪያ ላይ የሚጾሙት ሆነዋል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል በሚል ስያሜ ሰይማ እንዲጾም አድርጋዋለች፡፡

  Read more »

 • ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፤ ከሴትም ተወለደ /ገላ. 4፣4/

  እግዚአብሔር አምላክ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ፈጠረ ዘፍ 1፡1 ሌሎች ፍጥረታት ለአንክሮ ለተዘክሮ ሲፈጠሩ ሰውና መላእክት ግን መንግሥቱንና ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ተፈጠሩ፡፡

   የሰው ልጅን /አዳምን/ ፈጥሮ የሚያስፈልገውን አዘጋጅቶ፣ ዕውቀትንና ሥልጣን ሰጥቶ፣ በጸጋ አምላክነትን ሾሞ፣ መመሪያ ሰጥቶ፣ በክብር እንዲኖር ፈቀደለት፡፡ በመጀመሪያው ዕለትና ሰዓት ከተፈጠሩት መላእክት መካከል በክብር ይልቅ የነበረው ሳጥናኤል /የኋላ ስሙ ዲያብሎስ / አምላከነት በመሻቱ ተዋርዶ ሳለ አዳምንም በተዋረደበት ምኞትና ፍላጎት እንዲወድቅ ክብሩን እንዲያጣ ከአምላኩም እንዲለይ አደረገው፡፡ እግዚአብሔርን፤ ጸጋውን፣ ሹመቱን፣ ወዘተ አጣ /ኃጥአ/፡፡ ኃጢአት የሚለው ከዚህ ጽንሰ ሐሳብ የተወሰደ ነው፡፡

   አዳም ከእግዚአብሔር በመለየቱና ክብሩን በማጣቱ ተጸጽቶ ንሰሐ በመግባቱ ለሥርየተ ኃጢአት የሚሆን መሥዋዕትም በማቅረቡ፤ እግዚአብሔር አምላክ ልመናውንና መሥዋዕቱን ተቀብሎ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ቃል ኪዳን ገባለት “መዓልትና ዓመታትን በዚህ ምድር ላይ ሠራሁልህ፡፡ ይኸውም እነርሱ እስኪፈጸሙ ድረስ በምድር ላይ ትኖርና ትመላለስ ዘንድ ነው፡፡ የፈጠረችህና የተላለፍካት ከገነት ያወጣችህና በወደቅህም ጊዜ ያነሳችህ ዳግመኛም አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም የምታድንህ ቃሌን እልክልሃለሁ” እንዲል ገድለ አዳም እግዚአብሔር ለአዳም ነገረው፤ አዳምም አምስት ቀን ተኩል የሚለውን ቃል ከእግዚአብሔር በሰማ ጊዜ የእነዚህን ታላላቅ ነገሮች ትርጓሜ ሊያስተውል አልቻለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምስት ቀን ተኩል ማለት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት መሆናቸውን ገልጾ አርያውና አምሳያው ለሆነው ለአዳም በቸርነቱ ተረጎመለት ያን ጊዜ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ተስፋ ሰጠው፡፡

   አዳምም ይህንን ተስፋ ለልጆቹ አስተማራቸው፤ ልጆቹም ተስፋው የሚፈጸምበትን ጊዜ ለማወቅ በፀሐይ፣ በጨረቃና በክዋክብት /ዛሬም ቤተክርስቲያናችን ይህንን አቆጣጠር ትጠቀምበታለች/ ዘመናትን እየቆጠሩ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ ያለውን አዳኝ ጌታ መወለድ በትንቢታቸው ይናገሩ ይጠብቁም ነበር፡፡ ከእነርሱም ውስጥ:-

   1.ሱባኤ ሔኖክ፡- ሔኖክ ሱባኤውን ሲቆጥር የነበረው በአበው ትውልድ ሲሆን ሰባቱን መቶ ዓመት አንድ እያለ ቆጥሯል። በስምንተኛው ሱባኤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድ ትንቢት ተናግሯል። አቆጣጠሩም ከአዳም ጀምሮ ነው። 8x700=5600 ዓመት ይሆናል። 5500 ዓመተ ዓለም ሲፈጸም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደ ያጠይቃል።

   ትንቢቱም እንዲህ ይላል። “ስምንተኛይቱ ሰንበት ጽድቅና ኩነኔ የሚታወቅባት ሱባኤ ናት፡፡ ሰይፍም ለርሰዋ ይሰጣታል ታላቁ ንጉሥ የሚመሰገንበት ቤትም በርሰዋ ይሰራል፡፡ ምሥጋናውም ዘላለማዊ ነው፡፡” ሔኖክ 35፡ 1-2 ክፍል 91 በማለት ሲተነብይ መተርጉማን እንዲህ ይመልሱታል፡፡ ለርሰዋ ሰይፍ ይሰጣታል ማለቱ ጽድቅና ኩነኔ የሚታወቅበት ወንጌል ያን ጊዜ በዓለም ሁሉ ትሰበካለች ማለት ነው፡፡ የታላቁን ንጉሥ ቤት ይሠራል ማለቱ የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመሰገንበት ቤተ ክርስቲያን ትሰራለች ማለት ነው፡፡ ምስጋናውም ዘላለማዊ ነው ማለቱ ደግሞ ሰውና መላእክት በአንድነት ሆነው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር” እያሉ ዘወትር ያመሰግናሉ ማለት ሲሆን ስምንተኛይቱ ሰንበት ለክርስቲያኖች የተሰጠችበትን ዕለት ልደተ ክርስቶስ ናት ይሏታል፡፡

   2.ሱባኤ ዳንኤል፡- ስለ ጌታችን ሰው መሆን ጊዜ ወስኖ ሱባኤ ቆጥሮ የተናገረው ዳንኤል ነው፡፡ የዳንኤል ሱባኤ የሚቆጠረው በዓመት ነው ፡፡ ዳንኤል ሰባው ዘመን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ ተብሎ በኤርምያስ የተነገረውን ትንቢት እያስታዋሰ ሲጸልይ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጾ እንዲህ ብሎታል፡፡ “እግዚአብሔር ልምናህን ሰምቶሃልና እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፡፡ አሁንም ነገሩን መርምር ራእዩንም አስተዋሉ ኅጢአት የሚሰረይበትን ቅዱሰ ቅዱሳን ጌታም የባህርይ ክብሩን ገንዘብ የሚያደርግበት ባለው ሰባው ሊደርስ ሊፈጸም ነው ብለህ ወገኖችህን ቅጠራቸው” ብሎታል፡፡ /ዳን 9፡22- 25፤ኤር29፡1ዐ/

   ሰባ ሱባኤ አራት መቶ ዘጠና ዓመት ነው /7ዐX7= 490/ ይህ ጊዜ ከሚጠት እስከ ክርስቶስ መምጣት ያለው ጊዜ ነው /ትርጓሜ ሕዝ፡4፡6/

   3.ሱባኤ ኤርምያስ፡- ኤርምያስ ከባቢሎን እንደተመለሰ በፈረሰው ቤተ መቅደስ ውሰጥ ሆኖ ሲጸልይ ሳለ ራእይ አየ በሦስተኛው ቀንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ “ፈጣሪያችንን በአንድ ቃሉ አመስግኑ፤ የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን አመስግኑ፤ ከዚህ በኋላ ሰው ሊሆን ሥጋ ሊለብስ ወደዚህ ዓለም ሊመጣ የቀረው 333 ሱባኤ ዕለት ነውና እርሱ ወደዚህ ዓለም ይመጣል ዐሥራ ሁለት ሐዋርያትንም ይመርጣል…፡፡” ተረፈ ኤር 11፤37 ፣38፣42-48 ኤርምያስ ሱባኤውን የጀመረበትን ትንቢቱን የተናገረበት ራእዩን ያየበት ዘመን ዓለም በተፈጠረ በ5 ሺህ እና 54 ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ ትንቢቱ ከተነገረበት እስከ ክርስቶስ ልደት ያለው ጊዜ 446 ዓመት ነው፡፡

   ይኸውም በኤርምያስ ሱባኤ አንዱ 49ዐ ዕለት ነው መላው ሱባኤ 49ዐX333 = 163,170 ዕለት ሲሆን፤ ወደ ዓመት ሲለወጥ 163, 170÷365=446 ዓመት
  ኤርምያስ ሱባኤውን መቁጥር የጀመረበት ዘመን፤ …….. 5ዐ54 ዓመተ ዓለም ትንቢቱ ከተነገረበት ዓመት እስከ ክርስቶስ ልደት ……. 446 ዓመት በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት 55ዐዐ ዓመት ሲፈጸም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱ በዚህ ይታወቃል፡፡

   4.ዓመተ ዓለም:- የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምረው ሱባኤያትንና ሰንበታትን አውቀው ከአዳም እስከ ክርስቶስ ያለውን ዘመን ቁጥር 55ዐዐ ዓመት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

  ይኸውም፡- ከአዳም እስከ ኖኅ 2256 ዓመት፤ ከኖኅ እስከ ሙሴ 1588 ዓመት፤ ከሙሴ እስከ ሰሎሞን 593 ዓመት፤ ከሰሎሞን እስከ ክርስቶስ 1063 ዓመት፤በአጠቃላይ 55ዐዐ ዓመት ነው፡፡

   ከልደቱ በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የስብከትና የብርሃንን ሱባኤዎች አልፈን ኖላዊ ከገሃድ/ ጾመ ድራረ በፊት ያለ ሳምንት ነው፡፡
  እነዚህ ሳምንታት ነቢያት አምላክ ይህንን ዓለም እንዲያድን ያላቸውን ናፍቆት የገለጡባቸው እና ይህንን አስመልክተው ያስተማሩባቸው ሦስት የተለያዩ መንገዶች እና ጌታችንም ለእነዚህ መልስ የሰጠባቸው ሁኔታዎች ይታሰቡባቸዋል፡፡

   የመጨረሻው ሳምንት ኖላዊ የቃሉ ፍች እረኛ ማለት ነው፡፡ እረኞች ለበጎቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ሣር ውኃ ሳያጓድሉ እንዲጠብቁ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በነፍስ በሥጋ የሚጠብቅ ቸር እረኛ ነው፡፡ ይኽንን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሲያብራሩ ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው 14 ትውልድ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ዘመን እሥራኤላውያን ከሀገራቸው ተሰደው በባቢሎን 70 ዘመን ከኖሩ በኋላ ዘሩባቤልን አንግሦላቸው ይዟቸው እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ከዚያ በፊት እስራኤል ጠባቂ እንደሌለው መንጋ ተበታትነው ሲኖሩ ነቢያት ከኪሩቤል ላይ የሚገለጥ እረኛቸው እንዲገለጥ የእሥራኤል ጠባቂያቸው ሆይ፣ አድምጥ እያሉ የጠየቁበት መታሰቢያ ነው፡፡ መዝ.79-1-3፡፡

   መዝሙሩም “ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃሉ እግዚአብሔር ዘወረደ እምላዕሉ፤ የእግዚአብሔር ልጅና ቃሉ የሆነ ክርስቶስ ከላይ የወረደ ወደ ዓለም የመጣ እረኛ” የሚል ሲሆን የሚነበበው ደግሞ አንቀጸ አባግዕ የተባለው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ ዮሐ.10-1-22፡፡

   እረኛ የሌለው በግ ተኩላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ከትጉኅ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም በሲኦል አጋንንት በርትተውበት ሲጠቀጠቅ ኖሯል፡፡ እንዲሁም ከመንጋውና ከእረኛው የተለየ በግ እንዲቅበዘበዝ አምላኩን ዐውቆ አምልኮቱን ከመግለጽ የወጣው ሕዝብ በየተራራው መስገጃዎችን እየሠራ የሚታደገውን አምላክ በመፈለግ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር” እንዳለ፡፡ 1ኛ ጴጥ.2-25፡፡

   ነቢያት በዓለም ተበትነው የሚቅበዘበዙትን ሕዝቡን በቤቱ ሰብስቦ የሚጠብቃቸው እውነተኛ ቸር እረኛ እንዲወለድ ስለተናገሩ ያን ለማስታወስ ሳምንቱ ኖላዊ ተባለ፡፡ ለዚህም ነው የልደትን በዓል ስናከብር “ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ”
  “ዛሬ በክርስቶስ ልደት ደስታ ሃሴት ሆነ” የምንለው፡፡
  “ዮም፣ ዛሬ” ማለታችን በልደቱ ቀን ከእረኞችና ከመላእክት ጋር ሆነን እንደምናከብር የሚያመለክት ነው፡፡

   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት /ዓመተ ዓለም ፣ዓመተ ኩነኔ ፣ዓመተ ፍዳ/ አምስት ቀን ተኩል /55ዐዐ ዓመት/ ሲፈጸም /በእግዚአሔር ዘንድ 1ዐዐዐ ቀን እንደ አንድ ቀን ናት፡፡ 2ኛ ጴጥ 3፤8 / በ5501 ዓመት ማክሰኞ ታኀሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡

   “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ሥምረቱ ለሰብእ” አምላካችን እየሱስ ክርስቶስ የዘመኑ ፍጻሜ /የገባው ቃል ኪዳን፣ የተነገረው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባዔ/ ሲደርስ ከእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተወለደው ያጣነውን ልጅነት ሊመልስልን፣ ከተቀማነው ርስት ሊያስገባን፣ የገባንበትን እዳ ሊከፍልልን እንደሆነ ሁሉ በየዓመቱ የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር በልደቱ ያገኘናቸውን ሀብታት በመጠበቅ፣ የተማርናቸውን ትምህርቶች በመፈጸም እውነተኛ የልደት በዓል ተካፋዮች መሆን ይገባናል፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ሰማያውያን መላእክት ከምድራውያን እረኞች ጋር በአንድ ላይ እንዳመሰገኑ እኛም በዝማሬና በምስጋና በፍፁም ደስታ ልናመሰግን ይገባል፡፡ፍቅሩን እያሰብን በኃጢአታችን ምክንያት ከልባችን ያወጣነውን የሁላችንንም አምላክ ዛሬም በልባችን እንዲወለድ ያስፈልጋል፡፡
  “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት አለ?” ማቴ. 2÷1

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  Read more »

RSS