{$lang.login}{$lang.site_name}
Welcome
Login / Register

Most popular


 • ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? ክፍል አንድ

  ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? ክፍል አንድ አትም ኢሜይል

  ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? ምንስ እየሠራ ነው? የተዛባ አመለካከት የማይጋርደው ገሐድ እውነታ

  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ብራና ዳምጠው፤ ቀለም በጥብጠው፣ ብዕር ቀርጸው በየአብያተ ክርስቲያናቱ የመቃብር ቤቶች ውስጥ በማስተማር ትውልዱ የሀገር መሪ፣ የቤተክርስቲያን አለኝታ፣ የእግዚአብሔር ቅን አገልጋይ እንዲሆን ያበረከቱት አገልግሎት ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ ለትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚኖር ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገራችን ሥልጣኔ በር ከፋች ሆና የኖረች ከመሆኗም በላይ ዛሬ ላለው ዘመናዊ ሥልጣኔም መሠረት የጣለች ባለውለታ ናት፡፡ ቀደምት የቤተክርስቲያን አበው ደከመን፣ ሰለቸን ሳይሉ ዐረፍተ ዘመን እስከገታቸው ድረስ ሲያገለግሉ ኖረው ቤተክርስቲያኒቱ አሁን ከምትገኝበት የዕድገት ደረጃ አድርሰዋታል፡፡
  በዚህ ዘመንም የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ሁሉ ይህን ከአበው የተማሩትን ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀውና አስጠብቀው ለሚመጣው ትውልድ የማቆየት ሓላፊነት ያለባቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

  በመሆኑም ይሔንን አባቶች ወዛቸውን አንጠፍጥፈው፣ ዐይናቸውን አፍዘው፣ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው በሰማዕትነትና በተጋድሎ ያቆዩትን ሃይማኖት ለማስጠበቅና ለቀጣዩም ትውልድ በተመቻቸ ሁኔታ ለማስተላለፍ በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ድጋፍና ዕውቅና የተመሠረተው ማኅበረ ቅዱሳን በውጪ በአጽራረ ቤተክርስቲያንና በአሕዛብ፣ በውስጥ ዓላማውን ባልተረዱ፣ ዓላማውን ተረድተው የኑፋቄ ትምህርታቸውን እንደልብ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ለማስረግ ሌት ተቀን በሚተጉ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እየተከሰሰ እየተወቀሰና ያለ ስሙ ስም እየተሰጠው ይገኛል፡፡

  እነዚህ በውስጥና በውጭ የሚገኙት የቤተክርስቲያን ጠላቶች ቤተክርስቲያን ላይ በየዘመኑ በሚነሳው ፈተና እየተጠቀሙና በምክንያት እየተሳቡ ለቤተክርስቲያን ወዳጅ መስለው እየቀረቡና እያስቀረቡ ማኅበረ ቅዱሳንን ቢቻላቸው እንዲፈርስ፣ ባይቻላቸው ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓት ለማፍረስ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ የሚያስታጥቋቸው መናፍቃን ሴራና ዓላማ እንዳይጋለጥ እና በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እንደፈለጋቸው እንዲሆኑ ማኅበሩ አገልግሎቱ ተገድቦ እንዲዋቀር ለማስደረግና ለማድረግ የጥፋት ዘመቻዎችን በመክፈት ላይ ናቸው፡፡

  እነዚህ የቤተክርስቲያን ጠላት ወዳጆች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ጊዜ በሰጣቸው ጊዜ ሁሉ በመጠቀም ማኅበሩን ለማሳጣትና ለማጥላላት የሚጠቀሙባቸው ስልቶች በርካቶች ናቸው፡፡

  ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል «ማኅበረ ቅዱሳን ሲኖዶስ ከሰጠው ደንብና መመሪያ ውጪ እየሠራ የሚገኝ፣ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለውና ገቢና ወጪው የማይታወቅ ማኅብረ» እንደሆነ አድርገው» ሚያናፍሱት አሉባልታ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀስ ነው፡፡

  ማኅበረ ቅዱሳን ግን ባለፉት 17 ዓመታት እነዚህ የውስጥና የውጪ የቤተክርስቲያን ጠላቶች በየጊዜው ማኅበሩ ላይ የሚያናፍሱትን ወሬ ችላ በማለት ከወሬ ሥራ ይቀድማል በማለት ከቅዱስ ሲኖዶስ የተቀበለውን ዓላማ በዓይን በሚታይ፣ በእጅ በሚዳሰስ መልኩ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን «ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል» እንዲሉ ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ? ዓላማውስ ምንድን ነው? ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውን ሓላፊነት እንዴት እየተወጣ ነው? ለ17 ዓመታትስ ምን ሠራ? የሚሉትን ጥያቄዎት በስፋት ማቅረቡ አስፈላጊ መሆኑን ለምእመናን መግለጽ ግድ ብሎናል፡፡

   ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ?

  ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት አጽራረ ቤተክርስቲያንና ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱት ተላላኪዎቻቸው የውስጥ ዐርበኞች ማኅበረ ቅዱሳንን በሰው ውስጥ የጥላቻ መንፈስ እንዲያድር ከሚጣጣሩበት መንገድ አንዱ ማኅበሩ የሚጠራበትን ስያሜውን በማዛባት ነው የሚጀምሩት፡፡ ከዚህ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለውን ነገር ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ስያሜው ላይ አጭር ትንታኔ በመስጠት ወደ ማንነቱና አመሠራረቱ እንለፍ፡፡

   የማኅበሩ ስያሜ

  አንዳንድ ሰዎች ስያሜውም ግራ ያጋባቸዋል፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው አባላቱ ለራሳቸው ያወጡት አስመስለው የሚነግሯቸው ሰዎች አሉና የዋሀኑ ግራ ቢጋቡ አያስደንቅም፡፡ ነገር ግን የማኅበሩ ስያሜ እኩያኑ ማኅበሩን ለማጥላላት ከሚጠቀሙት ፕሮ­ጋንዳ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ማኅበረ ሚካኤል «የሚካኤሎች ስብስብ»፣ ማኅበረ ማርያምም «የማርያሞች ስብስብ» ካልሆነ /እንዳልሆነ/ ማኅበረ ቅዱሳንም «የቅዱሳን ሰብስብ» አይደለም፣ ሊሆን አይችልም፤ ወይም ማኅበረ ጊዮርጊስን የመሠረቱ ሰዎች ራሳቸውን «ጊዮርጊሶች»ነን እንደማይሉት፤ እንዳልሆኑትም፣ ማኅበረ ቅዱሳንም ቅዱሳን ነን የሚሉ ሰዎች ስብስብ አይደለም፡፡ ይልቁንም ማኅበረ ማካኤል የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት፣ ተራዳኢነት የሚታሰብበት ማኅበር እንደሆነው ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዐት ከመጠበቅና ከማስተማር በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርተ ሃይማኖት መሠረት የቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት እንዲሁም የቅዱሳን መላእክት ክብ ራቸው፤ ገድላቸውና ትሩፋታቸው፣ አማላጅነታቸውና በረከታቸው፤ በሰፊው እንዲታወቅና ትውልዱም የዚህ ተጠቃሚ እንዲሆን ትምህርት የሚሰጡበት ማኅበር ነው፡፡ ምእመናን በነዚህ ቅዱሳን አማላጅነትና ረድኤት እየታገዙ ለመንግሥተ ሰማያት እንዲበቁ ማድረግም ቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡

  ከዚህ የተነሣ የእነዚያ ብዙ ማኅበራት ኅብረት የሆነው ማኅበር የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ ጻድቃን ሰማዕታትና የቅዱሳን መላእከት ሁሉ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ተባለ፡፡

   ማኅበረ ቅዱሳን እንዴትስ ተመሠረተ?

  ዘመኑ የኮምዩኒዝም ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ የሰፈነበት፤ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት አስቸጋሪ የሆነበትና ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሔድ እንደ ኋላቀርነት የሚቆጠርበት ዘመን ነበር 1977 ዓ.ም፡፡

  በተለይም በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ /ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች/ በሚገኙ ተማሪዎች ዘንድ ቃለ እግዚአብሔርን በግልጽ መነጋገርም ሆነ መሰማት የማይታሰብበት ወቅት ነው፡፡

  ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይም በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች እንዲያስተምሩ ከምዕራባውያኑ ሀገሮች መጥተው የነበሩ ሚሲዮናውያን የኑፋቄ ትምህርታቸውን ያሠራጩ የነበረውም በእነዚሁ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነው፡፡

  በዚህ ሁኔታ ትውልዱ በየአቅጣጫው በሚሲዮናውያኑ የኑፋቄ ትምህርት እንዲሁም በኮምዩኒዝም ርዕተ ዓለምና አስተሳሰብ እየተነጠቀ ከኦርቶዶከሳዊት ተዋሕዶ እምነት የኮበለለበት ከቤተክርስቲያን የራቀበት ዘመን ነበር፡፡

  በዚህ ጊዜ ነው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ዋናው ግቢ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ አምስት ወጣቶች ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በቅዱስ ገብርኤል ስም ተሰባስበው ጽዋ መጠጣት የጀመሩት፡፡ ይህ መንፈሳዊ እንቅስቀሴ በዚሁ ተወስኖ አልቀረም፡፡ በየሳምንቱ እሑድ በመንበረ ­ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተክርስቲያን ግቢ በመጠለያ ሥር እየተሰባሰቡ በተደራጀ መልክ ባይሆንም መንፈሳዊ ትምህርት ይማሩ ጀመር፡፡ ከዚያም በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ትምህርት መማር ቀጠሉ፡፡

  እንዲህ የተጀመረው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገኙ የቤተክርስቲያን ልጆች ዘንድ የተዳረሰበት አጋጣሚና ሁኔታ የተፈጠረው ደግሞ በዚሁ በ1977 ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱ በነበረው የመንግሥት ሠፈራ ፕሮግራም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሙሉ በመንደር ምሥረታና መልሶ ማቋቋም ዘመቻ ወደ ጋምቤላ፣ መተከል እና ፓ­ዌ እንዲዘምቱ ተደረገ፡፡ በዘመቻው ወቅት ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየመጡ የተገናኙት የቤተክርስቲያን ልጆች ቃለ እግዚአብሔርን በመማር፣ በማኅበር ጸሎት በማድረግ እና ስለቤተክርስቲያን ጉዳይ በመወያየት ጊዜውን ተጠቀሙበት፡፡

  በዚህ ዓይነት የተጀመረው እንቅስቃሴ ከዘመቻው መልስ በ1978 ዓ.ም ተጠናከረ፡፡ ውስን የነበረው የተማሪዎች ቁጥርም ጨመረ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ ግቢዎች እስከ አርባ የሚደርሱ ተማሪዎች በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ማኅበር አዳራሽ እየተገኙ ትምህርተ ወንጌል ይማሩ ነበር፡፡ የተማሪዎቹን ዓላማና ጥረት የተገነዘቡ አባቶች መምህራነ ወንጌልም በቅርብ ሆነው እየተከታተሉ ሲያስተምሯቸው ቆይተዋል፡፡

  በቀጣዩ ዓመት ከ1979 ዓ.ም እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ ተማሪዎቹ በተምሮ ማስተማር ማኅበር አደራሽ ከሚከታተሉት መንፈሳዊ ትምህርት መርሐ ግብር ጋር ይህ መንፈሳዊ እን ቅስቃሴ ተጠናክሮ በስፋት የሚቀጥልበትን መንገድ ይወያዩ ነበር፡፡ በወቅቱ ትኩረት ተሰጥቶት ውይይት ይደረግበት የነበረው ዐቢይ ጉዳይ ከመካከላቸው ሰባኪ ወንጌል ማፍራት ነበር፡፡ ለዚህም በተለይ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት በቤተክርስቲያን አገልግሎት እየተሳተፉ በሰንበት ትምህርት ቤት ያደጉና በመጠኑም ቢሆን ልምድ ያላቸውን ተማሪዎች እንዲያስተምሩ ማድረግ አንድ መፍትሔ ነው፡፡ ለዘለቄታው ግን ከተማሪዎቹ መካከል በወቅቱ ሸዋ ሀገረ ስብከት ዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ገብተው እንዲሠለጥኑ ማድረግ የታመነበት መሠረታዊ ጉዳይ ሆነ፡፡

  ይህንኑ ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ፤ አስቀድመው በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው ስለስብከተ ወንጌል ሥልጠና የወሰዱ፤ በወቅቱ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እና የካህናት ማሠልጠኛው የበላይ ጠባቂ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጋር ይቀራረቡ በነበሩ ተማሪዎች አማካኝነት ግንኙነት ተደረገ፡፡

  እንዲሁም በ1980 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ግቢ ትምህርታቸውን ሊከታተሉ ከገቡት መካከል እስከ ሃምሣ የሚደርሱ ተማሪዎች በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብር ኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ተሰብስበው ይማሩ ጀመር፡፡ በዚሁ ዓመት በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሚማሩ ተማሪዎችም ተመሳሳይ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ጀምረው ነበር፡፡

  በዩኒቨርሲቲ መደበኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው በ1980 ዓ.ም ከተመረቁት ተማሪዎች ውስጥ በግቢ ቆይታቸው በቤተክርስቲያን ተሰባስበው መንፈሳዊ ትምህርት ሲማሩ የነበሩት የቤተክርስቲያን ልጆችም ለመጀመሪያ ጊዜ ተመረቁ፡፡ የምረቃው መርሐ ግብር የተካኼደው በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ማኅበር አዳራሽ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮሰ ካልዕ ጋር ሌሎችም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተው፤ ተመራቂዎቹ ተማሪዎች ለቤተክርስቲያን አገልግሎት እንዲተጉ አስተምረው ባርከው መርቀዋል፡፡

  ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጋር በተደረገው ግንኙነት መሠረት በዚሁ ዓመት ከተመረቁት መካከል ዐሥራ ሁለት ተመራቂ የቤተክርስቲያን ልጆች በዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው በክረምቱ ወራት፤ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ እምነት፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ትውፊት እንዲሁም የስብከት ዘዴ ሲማሩ ከረሙ፡፡ ሥልጠናውን የተከታተሉት ተማሪዎች ተመርቀው ከገዳሙ ሲሔዱ፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎር ዮሰ ካልዕ፤ «ከዚህ ስትወጡ ተበትናችሁ እንዳትቀሩ አደራ፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎታችሁ እየተገናኛችሁ መወያያ ይሆናችሁ ዘንድ መሰባሰቢያ አብጁ» በማለት፤ ተመራቂዎቹ በጽዋ ማኅበር ስም በመሰባሰብ፣ በሚሔዱበት ቦታ ሁሉ ስብከተ ወንጌልን እንዲያስፋፉ፣ በየዓመቱም በዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እየተገናኙ ስለ ዓመቱ የአገልግሎት ቆይታቸው ሪፖርት እንዲያቀርቡና እንዲወያዩ አሳስበው አሰናበቷቸው፡፡

  ተመራቂዎቹ የቤተክርስቲያን ልጆች የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕን አባታዊ ምክርና መመሪያ አልዘነጉም፡፡ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ «ማኅበረ ማርያም» በሚል ስያሜ የጽዋ ማኅበር መሠረቱ፡፡ በአዲስ አበባና በዙሪያው በሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በዓውደ ምሕረትና ሌሎች መርሐ ግብሮች ቃለ እግዚአብሔርን እያስተማሩ በየወሩ እየተገናኙ ስለአገልግሎታቸው ይወያዩ ነበር፡፡ በዓመቱ መጨረሻም በዝዋይ ተገኝተው ሪፖርት አድርገዋል፡፡ በ1981 ዓ.ም ክረምት ለሁለተኛ ዙር  ሥልጠና በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ተምሮ ማስተማር ማኅበር እና በግቢ ገብርኤል ዓምደ ሃይማኖት አዳራሾች ይማሩ ከነበሩት መካከል ዐሥራ ሁለት ተማሪዎች ተወክለው በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ በአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ አማካኝነት ሥልጠና ተሰጠቷቸዋል፡፡

  በዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች መንፈ ሳዊ እንቅስቃሴው እየተጠናከረ ቀጥሎ በተለይም በ1982 ዓ.ም በብዙ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ተዳረሰ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ፋኩልቲዎች፤ በጥቁር አንበሳ ሕክምና ፋኩልቲ፣ በልደታ ሕንፃ ኮሌጅ፣ በደ ብረ ዘይት እንስሳት ሕክምና ፋኩልቲ እንዲሁም በጅማ ጤና ሳይንስ፣ በዓለ ማያ ዩኒቨርሲቲ፣ በወቅቱ በአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ወዘተ ተስፋፋ፡፡ በዓመቱ የክረምት ወራት ከየዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆቹ የተውጣጡ አርባ አምስት ተማሪዎች ዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው ሥልጠና ወስደዋል፡፡ በሥል ጠናው በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ከሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ አርባ የሚደርሱ ተማሪዎችም ተሳትፈዋል፡፡ በዚህ ሥልጠና ወቅት ነበር ባልታሰበ ሁኔታ ታላቅ ኃዘን የደረሰው፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎር ዮስ ካልዕ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ነዐረፉ፡፡

  በ1983 ዓ.ም በወቅቱ በነበረው መንግሥት በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች በሙሉ ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ ሲታዘዝ፤ በሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮሌጆችና ተቋማት የሚማሩ አሥራ አንድ ሺሕ ያህል ተማሪዎች በብላቴ አየር ወለድ ማሠልጠኛ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በዩኒቨርሲቲና ኮሌጆቹ ግቢዎች ተጀምሮ ቀስ በቀስ የተስፋፋው መንፈሳዊ እንቅስቃሴም የበለጠ የሰፋበትና የተጠናከረበት ጊዜ ሆነ፡፡ ተማሪዎቹ ቀን ከሚሰጣቸው ወታደራዊ ሥልጠና መልስ ማታ ማታ እየተገናኙ መንፈሳዊ ትምህርት መማር በጋራ መጸለይ ጀመሩ፡፡ መንፈሳዊ ትምህርቱና ጸሎቱ በኅብረት የሚካኼደው በወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፑ በሚገኝ በሌላ አገልግሎት ያልተያዘ አዳራሽ /ኬስፖን/ ውስጥ ነበር፡፡ ትም ህርቱ ከዚህ ቀደም በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው በሠለጠኑ እና ሌሎችም በቤተክርስቲያን ትምህርትና አገልግሎት በቆዩ ተማሪዎች እየተሰጠ በየቀኑ ምሽት መርሐ ግብሩ ሳይታጎል ለሁለት ወራት ቀጥሏል፡፡ በዚህ ጉባኤ እስከ አምስት መቶ የሚደርሱ ተማሪዎች ያለማቋረጥ ይከታተሉ ነበር፡፡

  በወቅቱ በብላቴ አየር ወለድ ማሠልጠኛ ካምፕ ለወታደራዊ ሥልጠና የገቡት ተማሪዎች ማታ ማታ እየተ ሰበሰቡ በአንድነት ከሚያደርጉት ጸሎት እና ከሚማሩት የቤተክርስቲያን ትምህርት በተጨማሪ፤ በአካባቢው ወደሚገኘው ብላቴ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እየተደበቁም እያስፈቀዱም በመሔድ ምስጢራተ ቤተክርስቲያንን ይሳተፉ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሰባሰቡት ተማሪዎች ኅብ ረት እየጠነከረ መንፈሳዊ እንቅስቃሴው እየሰፋ መጣ፡፡ እነዚህ የቤተክርስቲያን ልጆች በወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ በነበሩበት ጊዜ የ1983 ዓ.ም የእመቤታችንን የልደት በዓል /ግንቦት ልደታ/ ለጸሎትና ለመንፈሳዊው ትምህርት በሚሰበሰቡበት አዳራሽ በደመቀ ሁኔታ አክብረዋል፡፡

  በብላቴ አየር ወለድ ማሠልጠኛ ካምፕ የነበረው የተማሪዎቹ ወታደራዊ ሥልጠና የሁለት ወር ቆይታ በመን ግሥት ለውጥ ምክንያት ሊበተን ግድ ሲሆን፤ ተማሪዎቹ በወታደራዊ ካምፑ ቆይታቸው የነበረው መንፈሳዊ እንቅስቃሴና ኅብረታቸው ዕጣ ፈንታ አሳሰባቸው፡፡ ይህ መንፈሳዊ አንድነት እንዴት መቀጠል እንዳለበት ተነጋገሩ፡፡ ከብዙ ውይይት በኋላም ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በየዩኒቨርሲቲና ኮሌጆቻቸው ሲመለሱ በቅዱስ ሚካኤል ስም ተሰባስበው ቤተክርስቲያንን ለማገልገል በመስማማት ቃል ገብተው ተለያዩ፡፡

  በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ዕረፍት ዓመታዊ መታሰቢያ ላይ የተገኙ ደቀመዛሙርትና መምህራን ነሐምሌ 22 ቀን 1983 ዓ.ም፤ በወቅቱ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ የገዳሙና የካህናት ማሠልጠኛው የበላይ ጠባቂ በነበሩበት በብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት ጉባኤ ተደርጎ ነበር፡፡ በጉባኤው ላይ «በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ተምራችሁ በማኅበረ ማርያም የታቀፋችሁ፣ በየቦታው ያላችሁ፣ በገዳሙም የምትኖሩ መነኮሳት እንዳትበታተኑ በአባታችን ስም ማኅበር አቋቁሙ» በማለት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሐሳብ አቀረቡ፡፡ በሐሳቡ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ለጊዜው «የዝዋይ ደቀመዛሙርትና መምህራን ማኅበር» በሚል ስያሜ እንዲጠራ ተወስኖ ማኅበር ተመሠረተ፡፡

  ከዚህ ቀደም በ1981 ዓ.ም በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም በተምሮ ማስተማር ማኅበር እና በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት የሚማሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ጉባኤ አንድነት በመፍጠር የተጠናከረ እንቅስቃሴ ባያደርግም «ማኅበረ እስጢፋኖስ» የሚባል ማኅበር መሥርተው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን እንቅስቃሴአቸው የተጠናከረ ባይሆንም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋኩልቲ ተማሪዎች «ማኅበረ ሥላሴ» በሚል ስያሜ፤ በሌሎችም ፋኩልቲዎችና ኮሌጆች ግቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች በተለያዩ ቅዱሳን ስም በሰየሟቸው ጽዋ ማኅበራት ተሰባስበው ነበር፡፡

  በጥር ወር 1984 ዓ.ም በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ የመጀመሪያውንም የመጨረሻውንም ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው «ማኅበረ ሚካኤል» የማኅበሩን መተዳደሪያ ደንብ አጽድቆ አመራሩንም መርጧል፡፡ ሆኖም በቅዱሳኑ ስም ማኅበር መሥርተው የተሰባሰቡት አባላት፤ «ዓላማቸው፣ አገልግሎታቸውም ሆነ ታሪካቸው አንድ ነው፡፡ ለምን አንድ ስያሜ ይዘው በአንድነት አይንቀሳቀሱም?» የሚል ሐሳብ በውስጣቸው እየተነሣ በተለያዩ አጋጣሚዎች በጉዳዩ ሲወያዩበት ቆይቷል፡፡

  በዝዋይ ለተመሠረተው ማኅበር ስያሜ ለመስጠት አዲስ አበባ በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ቤት በዚሁ ዓመት በየካቲትና መጋቢት ወራት በተካኼደው ስብሰባ ላይ ሐሳቡ ቀርቦ ውይይት ተደረገበት፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል «ሁላችሁም የያዛችሁት አገልግሎት የቅዱሳን ክብር የሚገለጽበት ነው፡፡ ስለዚህ የማኅበራችሁም ስም 'ማኅበረ ቅዱሳን' ይባል፡፡» በማለት ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት፤ የ«ማኅበረ ማርያም»፣ «ማኅበረ ሚካኤል» እና «የዝዋይ ደቀመዛሙርትና መምህራን ማኅበር» ተዋሕደው የሁሉም ማኅበራት የጋራ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ተመሠረተ፡፡

  አባላቱም መንፈሳዊ አገልግሎታቸው የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሥርዓትና መዋቅር ጠብቆ በቤተክርስቲያን አስተዳደር ዕውቅና ማግኘት እንዳለበት አምነው፤ «በጠቅላይ ቤትክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆነን እናገልግል» በማለት መተዳደሪያ ደንባቸውን ይዘው ወደ መምሪያው ጽ/ቤት ቀረቡ፡፡ በዚህ ዓይነት ማኅበረ ቅዱሳን ለመጀመሪያ ጊዜ በቤተክርስቲያኒቷ መዋቅር ዕውቅና አግኝቶ ግንቦት 2 ቀን 1982 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር መደራጀቱ ይፋ ሆነ፡፡
   
  ምንጭ፤ ማሕበረ ቅዱሳን ድሕረ ገፅ
   
  Read more »

 • ኩኑ ቅዱሳን እስመ ቅዱስ አነ” ዘሌ.19፡2

  የካቲት 12ቀን 2007 ዓ.ም.

   ፲ቱ ማዕረጋት

  ቅዱሳን ማለት የተቀደሱ፣ የከበሩ፣ የተመሰገኑ፣ የተለዩ፣ የተመረጡ፣ ንጹሐንየሆኑ፣ የጠሩ….. ወዘተ ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን በዚህ ስም የሚጠሩበት ከሰው ወይም ከምድራዊ ባለሥልጣን የተቸሩት አይደለም፡፡ በሃይማኖት ጸንተው በምግባር ጐልምሰው የሥጋ ምኞታቸውን ጥለው አፍርሰው ሲገኙ የቅድስና ባለቤት ቅዱስ እግዚአብሔር እነሱን /ቅዱሳንን/ መሣሪያ አድርጐ ኃይሉንና ሥልጣኑን ቢገልጽባቸው ማኅደረ እግዚአብሔር መሆናቸው ይገለጻል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡

  እሱ እግዚአብሐር ቅዱስ ተብሏልና የጌትነቱ መገለጫ የሆኑ ሁሉ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ጻድቃን እንደመላእክት ውሉደ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ /ኢዮ.1፡6/፣ ሮሜ.8፡14/ ቅዱሳን ጻድቃን በግብር መላእክትን መስለው ሆነው የፈጣሪአቸውን ፈቃድ ፈጽመው በመገኘታቸው ከዚህ ዓለም በመለየታቸው ቅዱሳን ሲባሉ የፈጣሪአቸውን ሕያው መንግሥት ወራሾች ናቸውና ውሉደ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ በሌላም ቃል ውሉደ ብርሃን ይባላሉ፡፡ /ሉቃ.16፡8/ በዓለማቸው ይራቀቃሉና ይህን ዓለም ይጠሉታል፡፡ ውሉደ ሕይወት ይባላሉ ሞትንና የሞት ከተማ ይህን ዓለም ይንቃሉና በክብር ተነሥተው ዳግመኛ ሲሞቱ የማይገባቸው ስለሆነ /ሉቃ.10፡30/ ውሉደ ጥምቀት ተብለዋል ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትናን ተጐናጽፈዋልና፡፡ ውሉደ መንግሥትም ተብለዋል የመንግሥተ ሰማያት ባለቤቶች ናቸውና፡፡ በጸጋ እግዚአብሔር የበለጸጉ በመሆናቸው የእግዚአብሔር አዕይንተ እግዚአብሔር ተብለዋል /መዝ.33፡15/

   የፈጣሪአቸው ፈቃድ በተግባራቸው ስለሚታይ የእግዚአብሔር አዝነ ፈቃድ ወደ ጻድቃን ነው፡፡ ልመናቸው ጾማቸው እንዲሁም ምጽዋታቸው ሁሉ የተወደደ መሥዋዕት ነው፡፡ ቅዱሳን በዓላማቸው ጾምን ግብዣ /ድግስ/፣ ለቅሶን ዘፈን፣ ደስታን ሐዘን አድርገው በመኖራቸው ይህ ተለዋዋጭ ዓለም በየጊዜው የሚአቀርብላቸው መርዶ በእነሱ ዘንድ ዋጋ የለውም ወይም ዋጋ አይሰጡትም፡፡ ዓለምም ለእነሱ የሚያቀርበው ዓለማዊ የምኞት ስጦታ እንደ ኢምንት የተቆጠረ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ገጸ መዓቱ ወደ ዓለማውያን ሰነፎች እንደሆነ ገጸ ምሕረቱ ወደ ቅዱሳን ነው፡፡ ስለዚህ አማላጅነታቸው ጸሎታቸው በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ “አፍቅርዎ ለእግዚአብሔር ኲልክሙ ጻድቃኑ” ቅዱሳን እውነትን ይዛችሁ ትሕትናን ተላብሳችሁ እግዚአብሔርን ውደዱት “እስመ ጻድቅ የሐስስ እግዚአብሔር” እግዚአብሔር እውነትን ትሕትናን ይወዳልና፡፡ /መዝ.30፡23/ የቅዱሳን ፍሬ ትሕትና ነው፡፡ በዓይነ ሕሊናቸው ፈጣሪአቸውን በዓይነ ሥጋቸው የእነሱን ምንነት እንዲሁም የዓለምን ከንቱነት ይመለከታሉ፡፡

   ፍሬ የያዘ ተክል ሁሉ ቁልቁል የተደፋ ነው፤ ትሕትናን ያስተምራል፣ የጻድቃን ምሳሌ ነው፡፡ በፈሪሃ እግዚአብሔር ልቡ የተሰበረ እሱነቱን /ምንነቱን/ የመረመረ ሰው በዓይነ ሕሊናው የፈጣሪውን ቸርነት በዓይነ ሥጋው የራሱን ውድቀት ይመለከታል፡፡ ይህ አመለካከት ለጸጋ እግዚአብሔርና ለፍሬ ክብር ያደርሱታል፡፡ በመቅረዝ ላይ ያለች መብራት መሰወር እንዳይቻላት የመቅረዙ ከፍታ የግድ እንደሚገልጻት በተራራ ላይ ያለች ቤትም በእይታ እንደማትሰወር የተራራው ከፍታ እንደሚገልጻት በጥበበ እግዚአብሔር ከብረው በጸጋ እግዚአብሔር ተውበው የሚኖሩ ቅዱሳን ጻድቃንም ደረጃ በደረጃ ማዕረጋትን አልፈው ከመለኮት ባሕርይ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ይሆናሉ፡፡

   “መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኑ” /መዝ.67፡35/ “እግዚአብሔር በቅዱሳኑ በወዳጆቹ አድሮ የሚሠራው ሥራ ድንቅ ነውን፡፡ /2ኛጴጥ.1፡3/ ቅዱሳን የጸጋ ተዋሕዶ ተዋሕደው ሲገኙ ሙት ሲሆኑ ሙታንን ማስነሳት እውር ሲሆነ እውርን ማብራት፣ በዓለም ላይ ድንቅ ሥራቸው ይሆናል፡፡ የጸጋና የክብር ተሸላሚዎች ሆነዋልና በዓለም ላይ ሳሉ የሚመጣባቸውን ፈተና ሁሉ ከምንም ባለመቁጠር ተቋቁመው የጸጋ መቅረዝ ተቋሞች ይሆናሉ፡፡ በዚህም በአላሰለሰው ሕይወታቸው የአንበሳ አፍ ዘጉ /ዳን.7፡1-28/ ውኃውን ወደ ኋላው መለሱ /ዘጸ.14፡22/ ሰማይን አዘዙ /1ኛ ነገ.17፡1፣ ያዕ.5፡17/ ነበለባለ እዥሰት አበረዱ /ዳን.3፡1-13/ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ወዳጅ እግዚአብሔር ከዘመድ ባዕድ ከሀገር የሚኖሩትን በረድኤት ይቀበላል፣ ሥጋዊ ሀገረ ተድላን ጥለው ሓላፊ ጠፊ ምድራዊ ምቾታቸውን ንቀው ጸጋውን የሚጠባበቁትን ሁሉ አብሮአቸው ይኖራል፡፡ ትዕግስትን የጥዋት ቁርስ የቀን ምሳ የማታ እራት አድርገው የሚመገቡትን ሁሉ ቤተ መቅደስ አድርጓቸው ይገኛል፡፡

   ቅዱሳን በዚህ ዓለም ይጠበቡበታል፣ ወጥተው ወርደው እነሱነታቸውን ከስስት ኃጢአት ጠብቀው ለወዲያኛው ዓለም ደግሞ በትዕግሥት ደጅ ይጠኑበታል፡፡ “አሪሃ እግዚአብሔር ትፍስህተ ልብ ውእቱ ወይሁብ ሐሴተ ወያስተፌስህ ወያነውሀ መዋዕለ ሕይወት፤ እግዚአብሔርን መፍራት የልብ ደስታ ነው፡፡ ፍጹም የሥጋና የነፍስን ደስታ ይሰጣል በሕይወትም ያኖራል፡፡” “ለፈሪሃ እግዚአብሔር ይሴኒ ድሐሪቱ ወይትባረክ አመ እለተ ሞቱ እግዚአብሐርን የሢፈራ ሰው ፍጻሜው ያምርለታል እንደ ኢዮብ ከደዌው ተፈውሶ ልጅ ልጅ አይቶ ይሞታል /ኢዮብ.31፡16/ ይህ ሁሉ በረከት የቅዱሳን የሁልጊዜ ፍሬ ነው፡፡

   ቅዱሳን ሁል ጊዜ የሚሠሩት ሰማያዊ ድርብ ድርብርብ /እንደ ሐመረ ኖኅ/ በጸጋ ላይ ጸጋ እየተጨመረላቸው ወደ 10ሩ መእረጋት ይወጣሉ፡፡ በያዙት ቀን መንገድም ኢዮባዊ ትዕግስት አብርሃማዊ ሂሩት ይስሐቃዊ ፈቃደኛነት ያዕቆባዊ ቅን አገልግሎት ጠሴፋዊ ሀዳጌ በቀልነት ሙሴአዊ ለወገን ተቆርቋሪነት እየጨመሩ በመኖራቸው ሳያውቁት የፈጣሪአቸውን ኃይል የጌትነቱ የመለኮትነቱን ድንቅ ሥራ መገለጫዎች ይሆናሉ፡፡

   ማዕረጋቸውን ከዚህ ይናገሩታል፡-

   የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት 3 ናቸ ው እነሱም፡-

  1. ጽማዌ
  2. ልባዌ
  3. ጣዕመ ዝማሬ ይባላሉ፡፡

   የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት 4 ናቸው

  1. አንብዕ
  2. ኲነኔ
  3. ፍቅር
  4. ሁለት ናቸው፡፡

   የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት ናቸው እነሱም

  1. ንጻሬ መላእክት
  2. ተሰጥሞ
  3. ከዊነ እሳት ናቸው፡፡

  የንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት

  1. ማዕረገ ጽማዌ፡- ይህ ማዕረግ የመጀመሪያው ነውና ማስተዋል ውስጣዊ ትዕግስትን ውስጣዊ ትህትና ውስጣዊ የራስ ሚዛንን ይዞ ማሰላሰል…… ወዘተ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ እግዚአብሔርን ብቻ መዘከር ይችሉ ዘንድ የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ከማውራት ይከለከላሉ፡፡ በዚህ ማዕረግ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያያሉ፡፡ ነገር ግን ለምን እንደሚወጡና እንደሚወርዱ አያውቁም፡፡ ዮሐንስ ሐጺር የሰፋውን ስፌት ገበያ ላይ ለመሸጥ ተቀምጦ እያለ እርሱ ግን በተመስጦ እነ ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን እንዲሁም ሌሎችን መላእክት በየማዕረጋቸው እያየ ሲያደንቅ ስፌቱን የሚገዛ ሰው ቁሞ እንቅቡ ዋጋው ስንት ነው ብሎ ሲጠይቀው እርሱ የሚያየውን የሚያይ መስሎት “ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ አኮ ገብርኤል ሚካኤል ይበልጣል ወይስ ገብርኤል” ብሎ በአንክሮ ጠየቀው፡፡ ይህን ሲለው ሰውየው ይሄስ እብድ ነው ብሎ ትቶት ሄዷል፡፡

   2. ማዕረገ ልባዌ፡- ደግሞ ማስተዋል ልብ ማድረግ አሰሙኝ እንጂ ስሙኝ አለማለት ልማር እንጂ ላስተምር አለማለት የተነገረው ትንቢትና ተግጻጽ ምዕዳን ሁሉ የራሱ እንደሆኑ መገመት መመርመር ዓይነ ሥጋን ከመጽሐፍ ከስነ ፍጥረት ዓይነ ነፍስን ከምስጢር….. ወዘተ ማዋል ነው፡፡ ወይም የእግዚአብሔርን ቸርነት ማድነቅ ስለሰው ያደረገውን ውለታ ማሰላሰል ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከሰው መወለዱን በገዳም መጾሙን መገረፉን ሥጋውን መቁረሱን ደሙን ማፍሰሱን መሰቀሉን መሞቱን መቀበር መነሳቱን እያሰቡ ልብን በፍቅረ እግዚአበሔር መሰበር አንደበትን በመንፈሳዊ ሕይወት መስበር ዓላማን በገጸ መስቀል/ትዕግሥት/ ማስተካከል የመሳሰሉት ናቸው፡፡

   3. ማዕረገ ጣዕመ ዝማሬ፡- ከዚህ ደረጃ ሲደርስ አንደበትን ከንባብ ልቡናን ከምስጢር ማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ አንደበታቸው ምንም ዝም ቢል በልባቸው ውስጥ ዝም አይሉም፡፡ ከአፍ እስትንፋስ ከአፋፍ ላይ ነፋስ እንደማይለይ ሁሉ ከአንደበታቸው ትዕግስት ከእጃዋው ምጽዋት ከልቡናቸው ትሕትና ከሰውነታቸው ንጽሕና አይለይም፡፡

   4. የሚጸልዩትና የሚይነቡት ምስጢሩ እየገባቸው ስለሚያደርጉት አይሰለቻቸውም፡፡ ከዚህ ማዕረግ የደረሰ አንደ ባሕታዊ ለብዙ ዘመናት አቡነ ዘበሰማያት /አባታችን ሆይ/ እያለ ብቻ ሲኖር መልአክ መጥቶ ይትቀደስ ስምከ በል እንጁ ቢለው ኧረ ጌታዬ እኔስ አቡነ የሚለው ኃይለ ቃል ምስጢሩና ጣዕሙ በአፌ እንደ ጨሙ እየሟሟ አልጠገበኝ ብሏል እንዴት አድርጌ ወደፊት ልሂድ ብሎታል፡፡

   የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት

   1. ማዕረገ አንብዕ፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ቅዱሳን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ያደረገውን ፍቅር እስከ ሞትና መቃብር የተጓዘውን የመከራ ጉዞ እያሰቡ በአንጻሩም ምረረ ገሃነመ እሳትን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን እያሰላሰሉ ውሉደ አዳም ይህን ሁሉ መከራ ባለ መገንዘብ ወደ ሰፊው የፈቃደ ሥጋ ሲጓዝ በማየታቸው ሲአለቅሱ ይታያል፡፡ ያለምንም መሰቀቅ ሲአለቅሱ እንባቸው እንደ ምንጭ ይፈሳል፡፡ እንደ ሰን ውኃ ይወርዳል ይኸውም ለዚህ ዓለም ብለው የሚአለቅሱት ልቅሶ ፊትን ያንጣጣል ዓይንን ይመልጣል የቅዱሳን ልቅሶ ግን ፊትን ያበራል ኃጢአትን ያስወግዳል እርጥብ እንጨት ከእሳት ጋር በተያያዘ ጊዜ እንጨቱ ከነበልባለ እሳት ሲዋሐድ እንጨቱ እርጥብነቱን ትቶ ውኃውን በአረፋ መልክ እያስወገደ ይነዳል፡፡ ቅዱሳንም በግብር/በሥራ/ ከመለኮት ጋር ሲዋሐዱ የዚህ ዓለም ምስቅልቅል ሥራ በሰማያዊ የረጋ ሕይወት ተለውጦ አሠራራቸው አካሄዳቸው ፍጹም ሕይወታቸው መልአካዊ ይሆናል፡፡

   2. ማዕረገ ኲነኔ፡- ከዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ሥጋዊ ፈቃድ ሁሉ ለነፍስ ፈቃድ ይገዛል ነፍስ በሥጋ ባሕርያት ላይ ትሰለጥናለች ምድራዊ /ሥጋዊ/ ምኞት ሁሉ ይጠፋና መንፈሳዊ /ነፍሳዊ/ ተግባር ሁሉ ቦታውን ይወርሳል ያለምንም ማወላወል መንፈሳዊ ተግባር ሁሉ ይከናወናል፡፡

  3. ማዕረገ ፍቅር፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ውሉደ እግዚአብሔር ቅዱሳን እንደ ፈጣሪአቸው ሁሉን አስተካክለው በመውደድ ይመሳሰላሉ አማኒ መናፍቅ ኃጥእ ጻድቅ ዘመድ ባእድ ታላቅ ታናሽ መሃይም መምህር ሳይሉ አስተካክለው በመውደድ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

  4. ማዕረገ ሁለት፡- ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ ባሉበት ሆነው ሁሉን ማየት መረዳት ይችላሉ፡፡ ጠፈር ደፈር ሳይከለክላቸው ርቀት ሳያግዳቸው ሁሉን በሁሉ ይመለከታሉ፡፡

   የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት

  1. ንጻሬ መላእክት
  2. ተሰጥሞ
  3. ከዊነ እሳት ናቸው፡፡

   ማዕረገ ንጻሬ መላእክት፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ የመላእክት መውጣት መውረድ ማየት ተልእኮአቸውን ያለምንም አስተርጓሚ መረዳት ማነጋገርና ማማከር የመሳሰሉትን መፈጸም፤ ለምሳሌ እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ መልአኩን 10 ዓመት ማቆም ነው፡፡

   ማዕረገ ተሰጥሞ፡- ከዚህ ማዕረግ ሲደረስ በባህረ ብርሃን መዋኘት ባሉበት ሆኖ ወደ ላይም ወደታችም መመልከት መቻል….. ወዘተ ናቸው፡፡
   ማዕረገ ከዊነ እሳት /ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ/፡- የፈጣሪ ቤተ መቅደስ ሆኖ ጸጋ በተዋሕዶ ከመላእክት ጋር ሆኖ ረቆ ማመስገን ያሉበትን ሥጋ በብቻው ማየት በአካለ ነፍስ ሰማየ ሰማያትን መጐብኘት ገነት ውስጥ መግባት ናቸው፡፡

   እነዚህም የቅዱሳን ማዕረጋት 10 ናቸው፡፡ /2ኛ ጴጥ.1፡4-10፣ ዮሐ.1፡40/ የአስሩ ማዕረጋት ምሳሌዎች የአስሩ ቃላት፡፡ /ዘጸ.20፡3-12፣ ዮሐ.13፡17/ በመጨረሻም ቅዱሳን የቅዱስ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ናቸው ኑሮአቸውም ቅዱስ ነው፡፡

        የቅዱሳን በረከታቸው አይለየን፡፡ አሜን፡፡


  • ምንጭ፡- ዝክረ ቅዱሳን ኅዳር ፮ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓ.ም.

   

   
  Read more »

 • ቅዱስ ፓትርያርኩ የትንሣኤን በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

                                                               

   

   "ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሰዶም ግብረ ኃጢአትን በጽናት መመከት አለበት" ብፁፅ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2006 ዓ.ም. የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓልን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡

   ቅዱስነታቸው በልዩ ጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ “በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ያጣናት ሕይወት፤ በክርስቶስ መታዘዝ አገኘናት፡፡ . . . የእርሱ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ዋዜማ ነውና የቀደመችው ሕይወት እንደተመለሰችልን አየናት፤ አወቅናትም” /ኤፌ.4፤ 5-7/ በማለት ገልጸዋል፡፡

   ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በማናቸውም ጊዜ ከነውረ ኃጢአትና ከርኩሰት ሁሉ ርቀው፤ ሕገ ተፈጥሮንና ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው መኖራቸውን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው የሰዶም ግብረ ኃጢአትን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጽናት መመከት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

  ምንጭ፤ ማሕበረ ቅዱሳን

   

  Read more »

 • በሰሙነ ሕማማት የሚነሡ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓዋጅ ከሚጾሙት አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም፤ ጾመ ኢየሱስ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ አሁን በጾሙ መጨረሻ ሳምንት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማምና ሥቃይ እንዲሁም እንግልት በምናስብበትና የጨለማውን ዘመን በምናስታውስበት ጊዜ /ሰሙነ ሕማማት/ ላይ እንገኛለን፡፡ስለ ሰሙነ ሕማማት ስናነሣ በምእመናን ዘንድ የሚነሡ አንዳንድ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እኛም እነዚህን ጥያቄዎች ለሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በማቅረብ የሰጡንን ምላሽ ይዘን ቀርበናል፡፡

  የግዝት በዓላት በሰሙነ ሕማማት ቢውሉ ስግደት መስገድ ይገባልን?

  ጥያቄው በርካታ ምእመናን በየዓመቱ የሚያነሡት ጥያቄ ነው፡፡ የግዝት በዓል በሰሙነ ሕማማት ላይ ሲውል በአንዳንድ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሲያሰግዱ በአንዳንዶቹ ደግሞ ቀኑ የግዝት በመሆኑ ስግደት አይገባም ብለው ሲከለክሉ ይስተዋላል፡፡

  የሰሙነ ሕማማት ቀናት የጌታችንን መከራና ሥቃይ የምናስብበት፣ የኃዘን የመከራ ጊዜያት ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ ስቅለት ከጌታችን ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ በመሆኑ በዓሉ ራሱ የሚከበረው በስግደት፣ በጾምና በጸሎት ነው፡፡

  በዓሉ የጌታን መከራና ሥቃይ፣ መንገላታቱን የምናስታውስበት በመሆኑ በዓሉ የሚከበረው በስግደት፣ በጾምና፣ በጸሎት፣ በንባብና በትምህርት ነው፡፡ በመሆኑም ይህን በዓል የሚሸር ምንም ዓይነት የግዝት በዓል የለም፡፡ የግዝት በዓላት በየወሩ በውዳሴና በቅዳሴ የምናከብራቸው ወርኃዊ በዓላት ይኼንን በዓመት አንድ ቀን የሚመጣን ልዩና ዐቢይ በዓል ይሽሩታል የሚል ትምህርት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አላስተማሩም፡፡

  በቤተ ክርስቲያናችን ንኡሳን በዓላትና ዐበይት በዓላት ተለይተው ይቀመጣሉ፡፡ ከጌታ በዓላት እንኳን ዐበይትና ንኡሳን ተብለው ተለይተው የሚቀመጡ በዓላት አሉ፡፡ ዘጠኙ የጌታ በዓላት ዐበይት ናቸው፡፡ በነዚህ በዓላት አይሰገድም፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ተለይቶ የስቅለት በዓል የበዓሉ ጠባይ በራሱ የሚከበረው በስግደት ስለሆነ በዚህ በዓል ስግደት ይገባል፡፡ በሰሙነ ሕማማት ክርስትና ማንሣት፣ ክህነት መስጠት፣ ለሞቱ ሰዎች መጸለይም አይገባም፡፡ ይላል ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 600፡፡

  የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ሕማማቱ በኃዘን፣ አብዝቶ በመጾም፤ ስለ መከራው በማሰብ፤ በስግደት እንዲከበሩ የሚያሳስብ መመሪያ የተላለፈበትን በዓል በወር የሚከበሩ የግዝት በዓላት አይሽሩትም፡፡ የሰሙነ ሕማማት በዓል ልዩና የስቅለቱን፣ የመከራውን፣ የሕማሙን ነገር የምናስብበት በመሆኑ መከበር የሚገባው በስግደት ነው፡፡ የሊቃውንቱም ትምህርት ይኸው ነው፡፡

  ታችን በከርሰ መቃብር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ቆይቶአልን?

  ጌታችን በከርሰ መቃብር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት መቆየቱ እውነት ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ቅዱሳት መጻሕፍት ያረጋግጣሉ /ዘፍ.22፤4፣ ዕብ.11፡17-19/፡፡ ለብዙዎች ጥያቄ የሆነው ጉዳይ አቆጣጠሩ በመሆኑ በዚህ ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡

  የጌታችን ትንሣኤ ትንቢተ ነቢያት የተፈጸመበት ነው፡፡ እርሱ ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል በሦስተኛውም ቀን ያነሣናል /ትን.ሆሴ. 6፤21/፡፡ የነቢዩ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ሌሊት ሦስት መዓልት መቆየቱ የትንሣኤ እግዚእ ምሳሌ ነው፡፡ /ማቴ.12፡40-42፣ዮና.2፤1/፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንጽሖተ ቤተ መቅደስን በፈጸመበት ዕለት እንዲህ ለማድረጉ ምን ምልክት ታሳየናለህ? በማለት ለጠየቁት አይሁድ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አስነሣዋለሁ አላቸው፡፡ አይሁድ ለጊዜው አይረዱት እንጂ እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር፡፡/ዮሐ.2፡18-21/

  ሀ. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ አንድ ቀን በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነው አቆጣጠር የመጻሕፍትን ምስጢር ለመረዳት ከሚያግዙን ነገሮች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የዕብራውያንን ባህል ማወቅ አንዱ ነው፡፡ የዕብራውያን አንድ ሙሉ ቀን መቆጠር የሚጀምረው ማታውን ስቦ ነው፡፡ በመሆኑም ጌታችን ከተሰቀለባት ዕለተ ዓርብ ጀምረን እስከ ትንሣኤው ያለውን ማታና ጠዋት ስንቆጥር፣ የዕለተ ዓርብን መዓልት /ቀን/፣ የቅዳሜን ሌሊትና መዓልት እንዲሁም የእሑድን ሌሊት ስንቆጥር ዓርብ ሌሊቱን አምጥቶ እሑድ መዓልቱን ስቦ አንድ ቀን የሚባሉ ናቸውና ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ቆይቷል፡፡

  ለ. ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ የሚለው የኦሪት ዘፍጥረት ቃል የሚያስታውሰንም የብርሃንና ጨለማ መፈራረቅ አገልግሎታቸው ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታ እንደሆኑ ነው፡፡

  ሐ. ዓርብ ከነግህ እስከ ቀትር የነበረው ብርሃን አንድ መዓልት፣ በቀትር ከነበረው ጨለማ ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ /ማቴ.27፤45/፡፡ እንዲል አንድ ሌሊት በመሆን የመጀመሪያውን መዓልትና ሌሊት ያስቆጥራሉ፡፡

  መ. ከዘጠኝ ሰዓት እስከ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ያለው ብርሃን አንድ መዓልት፣ ቀጣዩ ጨለማ የቅዳሜ ሌሊት አንድ መዓልትና ሌሊት ሆነው ሁለተኛ ቀንን ይቆጥሩልናል፡፡

  ሠ. የቅዳሜው መዓልትና /ቀን/ የእሑድ ሌሊት እስከ ትንሣኤው ጊዜ ድረስ ተቆጥሮ መዓልትና ሌሊት ሦስተኛን ቀን ያረጋግጡልናል፡፡


  ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ፤ ሚያዝያ 1-5 ቀን 2004 ዓ.ም.

  Read more »

 • ሰሙነ ሕማማትና ምስጢሩ

  ሰሙነ ሕማማትና ምስጢሩ

   

  ከትንሣኤ በፊት ያለው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ይኸውም በነቢዩ ኢሳይያስ ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማምነ፣ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንም ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡ /ኢሳ. 5፤34-36/ ተብሎ በመንፈስ ቅዱስ ትንቢት የተነገረው ቃል ተፈጸመ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ሳምንት ውስጥ ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ ለማስታወስ የወጣ ስያሜ ነው፡፡

   

  በሰሙነ ሕማማት መስቀል መሳለምና እርስ በእርስ መሳሳም የለም፡፡ ይህም ይሁዳ ጌታን በመሳም አሳልፎ እንደሰጠው ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ሣምንት ውስጥ ያሉት ዕለታት ስያሜያቸውና በየአንዳንዳቸው ዕለታት የተፈጸሙትን ድርጊቶች እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

   

  ሰኞ፡-

   

  አንጽሖተ ቤተ መቅደስና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ ያድራል፡፡ በማግስቱም ከቢታንያ ሲመጣ ተራበ ወበሳኒታ ወፂኦ እምቢታንያ ርኅበ ወርእየ በለሰ እምርኁቅ ወባቲ ቈጽለ ወሖረ ይርአይ እመቦ ዘይረክብ ፍሬ በውስቴታ ወበጺሖ ኀቤሃ አልቦ ዘረከበ ዘእንበለ ቈጽል ባሕቲቱ እስመ ኢኮነ ጊዜሁ ለበለስ፣ ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ ዓይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳችም ፍሬ አላገኘባትም፤ ወአውሥአ ወይቤላ ለዓለም አልቦ ዘይበልዕ ፍሬ እምኔኪ እንከ፣ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት፡፡ /ማር. 11፤11-12/

   

  በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፡፡ ፍሬ የተባለች ሃይማት ምግባር ናት፡፡ ከእስራኤል ፍቅርን ሃይማኖትን ምግባርን ፈለገ አላገኘም፡፡ እስራኤል ሕዝበ እስራኤል መባል እንጂ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገም ምክንያት እርሱ ከላያቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋባት፡፡

   

  አንድም በለስ ኦሪት ናት፡፡ በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፡፡ እጸ በለስን ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት፡፡

   

  አንድም በለስ ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሠፊ እንደሆነች ኃጢአትም በዚህ ዓለም ሥፍራ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፡፡ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ያሰኛል፡፡ ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ ወደ እርሷ ሄደ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፣ ኃጥእ ከመባል በቀር በመዋዕሉ ኃጢአት አለመሥራቱን ለመመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ፡፡ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚውሉም በኃጢአት በፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፡፡ ስትረገም ፈጥና መድረቋም በአዳም በደል ያገኛትን እዳ በደል በእርሱ እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

   

  በመቀጠልም ወደ ቤተ መቅደሰ ሄደ፡፡ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ /የንግድ ቤት/ ሁኖ ቢያገኘው ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ትሰመይ፣ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፡፡ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፡፡ /ማር. 11፤17-19/ ይህም የሚያሳየው ማደሪያ ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡

   

  በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስት ሰዓትና በተሰዓቱ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፡፡ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፡፡ ምክንያቱም የደረሰበትን መከራ ኀዘኑንና 5500 ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ሕይወት ይኖር እንደነበር ለማዘከር ነው፡፡

  ማክሰኞ፡-

  የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት በዚህ ዕለት ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና፡፡

   

  ጥያቄውም ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታት በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? የሚል ነበር ይህንስ ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ወይስ ከሰው? አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ነው ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም? ይለናል፡፡ ከሰው ነው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፤ እንደ መምህርነቱም ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን ተባብለው ወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ እኔም አልነግራችሁም አላቸው፡፡ ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፡፡ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነው እንጂ፡፡ ከዚህ የምንማረው የእነሱን ክፉ ጠባይና ግብር መከተል እንደማይገባን ነው፡፡

   

  በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስም ረጅም ትምህርት ስላስተማረ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን፣ ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብ፣ መክሮ መመለስ እንደሚገባ ሲያስተምር ነው፡፡

   

  ረቡዕ፡-

   

  ይህ ዕለት የምክር ቀን ይባላል፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሓፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር የጀመሩበት ወይም የያዙበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት በመሆኑ ብዙውን ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱን የሚያደንቁ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጥር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ /ማቴ. 26፤1-5፣ ማር. 14፤1-2/

   

  የሐዲስ ኪዳን ካህናት ምእመናን በዚህ ዕለት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ከእህልና ውኃ ተለይተው፣ መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው፣ የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ስለዚህ ታሪክ የሚያወሳውንም በማንበብ እስከ ኮከብ መውጫ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

   

  ይሁዳ ማለት ታማኝ ማለት ቢሆንም እንደ ስሙ ግብሩ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ስምና ግብሩ አልተባበረለትም፡፡ እኛ እንደ ስማችን ይሆን ግብራችን?

   

  መልካም መዓዛ ያለው ቀንም ይባላል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት ከእንግዲህ በኃጢአት ተጎድቶ የኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚሁ መልካም ሽቶ ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የሞላ ሽቱ ይዛ በመሄድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስላቀረበች ነው፡፡

   

  የእንባ ቀንም ይባላል፡፡ ይህም ይህችው ሴት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፡፡ /ማቴ. 26፤6-13፣ ማር. 14፤3-9፣ ዮሐ. 12፤1/ ከዚህም እያንዳንዳችን ልንማር የሚገባን ነገር አለ፡፡ ይኸውም የራሱን ኃጢአት በማሰብ ማልቀስና የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ነው፡፡

   

  ሐሙስ፡-

   

  ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት ያለው ሐሙስ በቤተ ክርስቲያናችን የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፡፡

   

  1.ሕጽበተ እግር ይባላል፡፡

   

  ይህ ስያሜ የተሰጠው ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ለማስታወስ ዛሬ ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝቡን ኃጢአት እጠብ ሲሉ በቤተ ክርስቲያናችን የተገኙትን ምእመናን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ሲያጥቡ ያረፍዳሉ፡፡ /ዮሐ. 13፤4-15/

   

  2.የጸሎት ሐሙስ ይባላል፡፡

   

  የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚደክም ሥጋን የተዋሐደ አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ለመግለጽና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ በጌቴ ሴማኒ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ነው፡፡ /ማቴ. 26፤36፣ ዮሐ. 17፤1/

   

  3.የምስጢር ቀንም ይባላል፡፡

   

  ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷል፡፡ ይኸውም ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፤ እንካችሁ ብሉ፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ አመሰገነ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ፡፡በማለት እኛ ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን መንገድ ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡

   

  በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ የሚቀደሰውም በለሆሳስ ሲሆን እንደ ቃጭል በመሆን የሚያገለግለውም ጽናጽል ነው፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ሲመጡ ድምፃቸውን ዝግ አድርገው በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው፡፡ በቅዳሴውም ኑዛዜ አይደረግም፡፡ ሥርዓተ ቁርባን ግን ይፈጸምበታል፡፡ ይህም ጌታችን የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ተዘጋጅቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርበታል፡፡

   

  4.የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡

   

  ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳ ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ /ሉቃ. 22፤18-20/ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚሆን የአዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ በማለቱ ይታወቃል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓማዊ ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት መሆኑን በማሰብ የቃል ኪዳኑ ፈጻሚዎች ጠባቂዎች መሆን እንደሚገባን እንማራለን፡፡

   

  5.የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡፡

   

  ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ራሱም ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆቼ ግን ብያችኋለሁ በማለቱ /ዮሐ.15፤15/ ከባርነት ነጻ የወጣንበት ቀን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከኃጢአት ባርነት በመራቅ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን በቅድስና መምራት ይኖርበታል፡፡ እርሱ ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጆቹ አድርጎናል፡፡ /ማቴ 26፤17-19/

   

  6.አረንጓዴው ሐሙስ ይባላል፡፡

  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአትክልት ቦታ ስለ ጸለየ፡፡

   

  ዕለተ ዓርብ፡-

   

  የስቅለት; ቀን ስቅለት፣ መስቀል፣ መሰቀል፣ አሰቃቀል ማለት ነው፡፡ መስቀል በቁሙ መስቀያ፣ መመዘኛ፣ መሰቀያ፣ መንጠልጠያ፣ ለሞት የሚያበቃ መከራ በማር 8፤34 ወጸውዖሙ ለሕዝብ ምስለ አርዳኢሁ ወይቤሎሙ ዘይፈቅድ ይፀመደኒ ይጽልአ ለነፍሱ ወያጥብዕ ወይፁር መስቀል ሞቱ ወይትልወኒ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ሕዝቡን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፡፡ ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ ይላል፡፡

   

  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በ1ኛ ቆሮ. 1፤17 ላይ ወኢኮነ በጥበበ ነገር ከመ ኢንስዐር መስቀሎ ለክርስቶስ የክርስቶስን መስቀሉን ከንቱ እንዳናደርግ ነገርን በማራቀቅ አይደለም ይላል፡፡

   

  ጌታችን በተሰቀለ ዕለት ከሰድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፡፡ /ፀሐይ ጨለመ/፣ እነሆም የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተውም ከነበሩት ቅዱሳን ብዙዎች ተነሱ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ለብዙዎች ታዩ፡፡ /ማቴ. 27፤51/

   

  ጌታችን ለዓለሙ ያሰበውን ቤዛነት ሊፈጽም በመስቀል ላይ መሰቀሉ የሚታሰብበት ነውና ለስቀለቱ መታሰቢያ የሚሆን አጎበር ተዘጋጅቶ ከርቤ እየታጠነ ስቅለቱ የሚመለከቱ ምንባባት ሲነበብና ሲሰገድ ይዋላል፡፡ የሰው ልጅ በሙሉ በእግረ አጋንንት ረግጦ ከፈጣሪው ተጣልቶ ለ5500 ዘመን በጨለማ መኖሩን ለማስታወስም መንበሩ ታቦቱ በዚህ ቀን በጥቁር ልብስ ይሸፈናሉ፡፡ ዲያቆኑም በቤተ ክርስቲያን በመዞር የሚያሰማው የቃጭል ድምፅ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅሶ አንድም ዋይ ዋይ እያሉ የተከተሉት የኢየሩሳሌም ሴቶችን ሙሾም ምሳሌ ነው፡፡ /ሉቃ. 23፤31/

   

  በዕለተ ዓርብ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ፡፡ አንቀጸ ገነት ተከፈተልን፣ ርስተ መንግስተ ሰማያት ተመለሰችልን፤ አባታችን አዳምም ከፈጣሪው ጋር ታረቀልን በማለት ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃዶ እያልን የተድላ፣ የደስታ ምልክት ወይም መገለጫ የሆነ ልምላሜ ያለውን ቆጽለ ሆሣዕና ወይም ቄጤማ ግጫ ይዘን የምሥራች እንባባላለን፡፡ /ኤፌ. 2፤14-15/ ወዘእንበለ ምሳሌሰ ኢተናግሮሙ፣ ያለ ምሳሌ አልተናገረምና እንዳለ /ማቴ 13፤34-35/ በኖኅ ጊዜም ርግብ ሐጸ ማየ አይኅ፣ ነትገ ማየ አይኅ፣ የጥፋት ውኃ ጎደለ፣ አለቀ እያለች ቈጽለ ዕፀ ዘይት ይዛ ለኖኅ አብስራዋለች፡፡ /ዘፍ. 8፤8-11/

   

  ርግብ የካህናት፣ ኖኅ የምእመናን፣ ኖኅ እጁን ዘርግቶ ርግብን እንደተቀበላት ካህናትም በየመንደሩ እየዞሩ ክርስቶስ ተመረመረ ዲያብሎስ ታሰረ በማለት ቄጤማ ሲያድሉ ምእመናንም እጃቸውን ዘርግተው መቀበላቸው የዚህ ምሳሌ ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢገኝ የወይራ ልምላሜ ቢታጣ ግጫን እየታደልን የምሥራች መባባላችን ነፍሳት ከሲኦል ለመውጣቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ይህን ቈጽለ ልምላሜ ይዞ ተድላ፣ ደስታ መግለጽ ከጥንት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ለዚህ በመጀመሪያዪቱ ቀን ከበጎ እንጨት ፍሬን የሰሌንና የተምር ዛፍ ልምላሜ ይዛችሁ በየዓመቱ ሰባት ቀን ተድላ፣ ደስታ ታደርጋላችሁ ብሏል፡፡ /ዘሌ. 23፤40-44/

   

  በሰሙነ ሕማማት ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችን የምታደርገው ትውፊት የሐዋ. ሥራ 1፤3

   

  ከሆሣዕና እስከ ቀዳም ሥዑር ያሉት ዕለታት የዓመተ ፍዳ መታሰቢያ ናቸው፡፡ ፡፡ ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ በዚህ ሣምንት ውስጥ ለሚሞቱ ምእመናን እግዚኦ ሕያዋን ይደገማልና፡፡ በሰሙነ ሕማማት መስቀል የለም፡፡ ሣምንቱ የዘመነ ኦሪት ምሳሌ ስለሆነ እርስ በእርስ መሳሳም፣ ሰላም መባባልና መልክዐ መልክዕ መድገም የለም፡፡ ይኸውም ይሁዳ ክርስቶስን በሰላምታ ስላስያዘው እርሱን ላለመምሰል፡፡ /ማቴ. 26/

   

  በዚህ ሳምንት ብሉያትና ሐዲሳት መጻሕፍት ከጠዋት እስከ ማታ ይነበባሉ፡፡ የአምልኮ ስግደት ይሰገዳል፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል መስቀልን ተሸክሞ ሲወድቅ ሲነሣ የዋለበትን፣ ይልቁንም ሥርዓተ ስግደትን ራሱ ሰግዶ እኛን ያስተማረንን በማሰብ ነው፡፡ /ሉቃ. 22፤41-45፣ ዮሐ. 4፤22-24/

   

  ስለዚህም በዚህ ሳምንት ወርኃዊ፣ ዓመታዊ በዓል ቢሆን እንኳ ስግደት አይቋረጥም፡፡ የአምልኮ ስግደት ሳምንት ስለሆነ፡፡ ዲያቆኑ ጥቁር ለብሶ መስቀል ይዞ ቃጭል እያቃጨለ ቤተ ክርስቲያንን ሦስት ጊዜ መዞሩ ዲያቆኑ የዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፣ ቃጭል የእመቤታችን ምሳሌ ሲሆኑ፤ ዮሐንስና እመቤታችን ጌታችን የተሰቀለበትን እግረ መስቀሉን እየዞሩ አልቅሰው ነበርና፡፡

   

  በዕለተ ዓርብ ሠርክ ሲሆን ምእመናን ወደ ቄሱ እየቀረቡ ስግደት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ ቄሱም በወይራ ቅጠል እየጠበጠበ ተጨማሪ ቀን ሲሰግዱ ከዋሉት ሌላ ስግደት ይሰጣቸዋል፡፡ ጥብጠባ የጌታችን ግርፋት ምሳሌ ነው፡፡ አንድም የተግሣፅ ምሳሌ ነው፡፡ /ማቴ. 26፤27/

   

  አክፍሎት

   

  አክፍሎት ማለት ማካፈል፣ ማጠፍ፣ መደረብ፣ ሁለቱን ቀን አንድ አድርጎ መጾም፣ ጌታ ከተያዘበት እስከተነሣበት ድረስ ይህ ሥርዓት የመጣው በቤተ ክርስቲያናችን ልማድ እመቤታችን፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የጌታን ትንሣኤ ሳናይ እህልና ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሣኤ በመቆየታቸው ምክንያት ነው፡፡ በሀገራችን ብዙ ሰዎች ሐሙስ ማታ የቀመሱ እሑድ የትንሣኤ ዕለት ብቻ እህልና ውኃ የሚቀምሱት፤ ያልተቻላቸው ግን ዓርብ ማታ የቀመሱ እስከ ትንሣኤ ይሰነብታሉ፡፡ የሁለት ቀን ማክፈሉ እንኳ ቢከብድ ቅዳሜን ማክፈል ሥርዓት ነው፡፡ ቅዳሴው በመንፈቀ ሌሊት ስለሆነ በልቶ ማስቀደስና መቁረብ እንዳይሆን፡፡

  Source:Mahbere Kidusan

   

  Read more »

RSS