{$lang.login}{$lang.site_name}
Welcome
Login / Register

Most popular


 • መፃጉዕ ( የዐቢይ ጾም ዐራተኛ ሳምንት)

  የካቲት 29 ቀን 2007 ዓ.ም.

  ምንባባት

  የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

  አምላኩሰ ለአዳም ለዕረፍት ሰንበተ ሠርዓ፤ ወይቤልዎ አይሁድ በዓይ ሥልጣን ትገብር ዘንተ ወይቤሎሙ ኢየሱስ አነኒ እገብር አንትሙኒ፤ እመኑ ለግብርየ ወይቤሎሙ አነ ውእቱ እግዚኦ ለሰንበት እግዚኦ ውእቱ ለሰንበት ወልድ ዋሕድ ወይቤሎሙ ብውህ ሊተ፤ እኅድግ ኃጢአተ በዲበ ምድር እስበክ ግዕዛነ ወእክሥት አዕይንተ ዕውራን አቡየ ፈነወኒ፡፡


  ትርጉም: “የአዳም ፈጣሪ ለዕረፍት ሰንበትን ሠራ፤ አይሁድም በማን ሥልጣን ይህን ታደርጋለህ አሉት፤ እርሱም እኔ እሠራለሁ እናንተም ሥራዬን እመኑ አላቸው፡፡ የሰንበት ጌታው እኔ ነኝ፤ የሰንበት ጌታው/የአብ/ አንድያ ልጁ ነው፡፡ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር እል ዘንድ ፣ ነፃነትን እሰብክ ዘንድ ተሰጥቶኛል ፣ የዕውራንን ዓይን አበራ ዘንድ አባቴ ልኮኛል አላቸው፡፡” ማለት ነው፡፡


  መልእክታት

  (ገላ. 5÷1-ፍጻሜ ምዕ.)፡- እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ፡፡ እነሆ÷እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፤ “ብትገዘሩም በክርስቶስ ዘንድ ምንም አይጠቅማችሁም፡፡” ደግሞም ለተገዘረ ሰው ሁሉ የኦሪትን ሕግ መፈጸም አንደሚገባው እመሰክራለሁ፡፡ በኦሪት ልትጸድቁ የምትፈልጉ እናንተ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋዉ ወድቃችኋል፡፡ እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ÷ በእምነትም ልንጸድቅ ተስፋ አናደርጋለን፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በፍቅር የምትሠራ እምነት እንጂ መገዘር አይጠቅምምና፤ አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምምና፡፡ ቀድሞስ በመልካም ተፋጠናችሁ ነበር፤ በእውነት እንዳታምኑ ማን አሰናከላችሁ? ይህ መፋጠናችሁ ከሚጠራችሁ አይደለምና፡፡ ጥቂት እርሾ ብዙውን ዱቄት መጻጻ ያደርገው የለምን? እኔ ሌላ እንዳታስቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኛችሁ ነበር፤ የሚያውካችሁ ግን የሆነው ቢሆን ፍዳውን ይሸከማል፡፡ ወንድሞቼ ሆይ÷ እኔ ግዝረትን ገና የምስብክ ከሆነ÷ እንግዲህ ለምን ያሳድዱኛል? እንግዲህ የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት እንዲያው ቀርቶአል፡፡ የሚያውኩአችሁም ሊለዩ ይገባል፡፡

  ወንድሞቼ ሆይ÷ እናንተስ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን በሥጋችሁ ፈቃድ ለነጻነታችሁ ምክንያት አታድርጉላት፤ ለወንድሞቻችሁም በፍቅር ተገዙ፡፡ “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈጽማልና፡፡ እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትንካከሱ ከሆነ ግን÷ እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ፡፡ እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ኑሩ እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ፡፡ ሥጋ መንፈስ የማይሻውን ይሻልና÷ መንፈስም ሥጋ የማይሻውን ይሻልና የምትሹትንም እንዳታደርጉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፡፡ የመንፈስን ፈቃድ የምትከተሉ ከሆናችሁ÷ ከኦሪት ወጥታችኋል፡፡ የሥጋም ሥራው ይታወቃል፤ እርሱም ዝሙት÷ ርኲሰት÷ መዳራት÷ ጣዖት ማምለክ÷ ሥራይ ማድረግ÷ መጣላት÷ ኲራት÷ የምንዝር ጌጥ÷ ቅናት÷ቊጣ÷ ጥርጥር÷ ፉክክር ÷ምቀኝነት መጋደል÷ ስካር ይህንም የመሰለ ሁሉ ነው፡፡ አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር÷ ደስታ ÷ሰላም÷ ትዕግሥት÷ ምጽዋት÷ ቸርነት÷ እምነት÷ ገርነት÷ ንጽሕና ነው፡ ከዚህ ሕግ የሚበልጥ የለም፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ግን ሰውነታቸውን ከምኞትና ከኀጢአት ለዩ፡፡ አሁንም በመንፈስ እንኑር፤ በመንፈስም እንመላለስ፡፡ ኩሩዎች አንሁን፤ እርስ በርሳችን አንተማማ፤ እርስ በርሳችንም አንቀናና፡፡ 

  (ያዕ.5÷14- ፍጻሜ ምዕ.)፡- ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቅቡት፡፡ የሃይማኖት ጸሎትም ድውዩን ይፈውሰዋል፤ እግዚአብሔርም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል፡፡ እርስ በርሳችሁ ኀጢአታችሁን ተናዘዙ፤ እንድትድኑም ለወንድሞቻችሁ ጸልዩ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎቱ ብዙ ትረዳለች፤ ግዳጅም ትፈጽማለች፡፡ ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበር፤ እንደምንታመምም ይታመም ነበር፤ ዝናም እንዳይዘንም ጸሎትን ጸለየ፤ ሦስት ዓመት ከስድስት ወርም በምድር ላይ አልዘነመም፡፡ ዳግመኛም ጸለየ፤ ሰማይም ዝናሙን ሰጠ፤ ምድርም ፍሬዋን አበቀለች፡፡ ወንድሞቻችን ሆይ÷ ከእናንተ ከጽድቅ የሳተ ቢኖር÷ ከኀጢአቱ የመለሰውም ቢኖር÷ ኀጢአተኛውን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ራሱን ከሞት እንደ አዳነ÷ ብዙ ኀጢአቱንም እንዳስተሰረየ ይወቅ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድም የሐዋርያው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት ተፈጸመች፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡

  ግብረ ሐዋርያት

  (የሐዋ.3÷1-11)፡- ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ነበር፤ ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁል ጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋት በመቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር፡፡ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም ወደ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡ ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ተመለከተውና “ወደ እኛ ተመልከት” አለው፤ ወደ እነርሱም ተመለከተ፤ ምጽዋት እንደሚሰጡትም ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ጴጥሮስም÷ “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ÷ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ በቀኝ አጁም ይዞ አስነሣው፤ ያን ጊዜም እግሩና ቊርጭምጭምቱ ጸና፡፡ ዘሎም ቆመ፤ እየሮጠና እየተራመደም ሄደ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ሕዝቡም ሁሉ እግዝአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፡፡ እርሱም መልካም በምትባለው በመቅደስ ደጃፍ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እንደ ሆነ ዐወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መገረምና መደነቅ ሞላባቸው፡፡

  ምስባክ

  መዝ.40÷3 “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፡፡ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቢ /ቤ/ሁ እምደዌሁ አንሰ እቤ እግዝኦ ተሣሃለኒ

  ትርጉም፦ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል፡፡

  ወንጌል

  (ዮሐ. 5÷1-24)፡- ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት፡፡ በዚያም ዕውሮችና አንካሶች÷ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃዉን በሚያናውጠው ጊዜ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና፡፡ በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ይህን ሰው በአልጋዉ ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደ ቆየ ዐውቆ÷ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ ድውዩም መልሶ÷ “አዎን ጌታዬ ሆይ÷ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያዉ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው፡፡ ጌታችን ኢየስስም÷ “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያውኑም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያች ቀንም ሰንበት ነበረች፡፡ አይሁድም የዳነውን ሰው÷ “ዛሬ ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አይገባህም” አሉት፡፡ እርሱም መልሶ÷ “ያዳነኝ እርሱ፡- አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው፡፡ አይሁድም÷ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና÷ “እነሆ÷ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ” አላቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው” በማለት ብቻ አይደለም፤ ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል” በማለት ነው እንጂ፡፡

  ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል፡፡ አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል፡፡ አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸው÷

  ምንጭ፤ ማኅበረ ቅዱሳን ድህረ ገጽ

  ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም፡፡

  Read more »

 • ኒቆዲሞስና አዲሱ ልደት

  ኒቆዲሞስና አዲሱ ልደት

   

  በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ ሦስት ብዙ አሕዛብ ወደ ክርስትና እምነት የተቀላቀሉበት ምዕራፍ ነው፡፡ድኅነትን በትጋት ለመፈጸም የሚታገሉ ክርስቲያኖች ይሄንን ምዕራፍ ሲያነቡ ከኒቆዲሞስ ጎን መቆማቸው የሚያጠራጥር አይሆንም፤ ከጌታ ጋር ምስጢራዊ የሆነ ውይይትን መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ በሕይወታቸው የተከፈተ የአዲስ ኪዳን መንገድን እንዳለ ሲገነዘቡም ጌታን ይከተላሉ፡፡ ከእርሱ ጋር ከቅዱስ መንፈሱም ጋር አንድ ይሆናሉ፡፡ አዲስ ልደትን ያገኛሉ ፤ይህም በጥምቀት የሚገኝ ልጅነት ነው፡፡


  ይህ ምዕራፍ መልካም ሥነ ምግባር በነበረው ፈሪሳዊ ሕያውና መንፈሳዊ በሆነው ምንጭ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የነበረውን ውይይት ይዟል፡፡


  ኒቆዲሞስ እንደ ፈሪሳዊ በአይሁድ ትውፊትና በብሉይ ኪዳን ትምህርት የታጠቀ ነው፡፡ ጠንካራ ሞራል እንደገነባ ሰው ወደ ጽድቅ የሚወስደውን ትውፊት የሚያውቅ ሰው በፈቃዱ መታዘዝ እንዳለበት የሚያምን ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ሰው በሚያደርገው ጠንካራ ትግል እንደሆነ ያምናል፡፡ይህ ትግል በሰው በጎ ፈቃድና ሕጉን በደረቁ በመተርጎም እንደሚገኝ ያምናል፡፡ ኒቆዲሞስ ጌታን ያገኘው ሕጉን የሚቃወም ሆኖ ሳይሆን ሕጉን በጥልቀት የሚተረጉም አይሁዳዊ ሆኖ ነው፡፡


  ስለዚህም ነው ወደ መድኀኒታችን ከተሳቡ ወገኖች መካከል ወንጌላዊው የኒቆዲሞስን ጉዳይ በትኩረት የጻፈው፡፡ በዚህ ዐውድ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ይላል፡-በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ /ዮሐ.2፡23/፡፡ ኒቆዲሞስ ጌታ ከእግዚአብሔር እንደመጣ አወቀ፤ አመነም /ዮሐ.3፡2/፡፡ ነገር ግን ምናልባት ኒቆዲሞስ ጌታ ትምህርቱን ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያስተምር ሊያስብ ይችላል፡፡ የሕጉን ጥሬ ትርጉም እንጂ ፍካሬያዊ ትርጉም አልተገነዘበም፡፡ የአይሁድን ኑሮ ሊያሻሽል የመጣ ነው ብሎም ሊያስብ ይችላል፡፡


  የኒቆዲሞስ አመለካከቱና ልምዱ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን አዲስ ሕይወት ለመቀበል አያበቃውም፡፡ በአዲሱ ልደት የሚገኘው የጸጋ ልጅነት አይገነዘበውም፡፡ የመንፈሳዊው ሕግ ጥቅም ግን ይህ ነበር፡፡ ሥጋዊውን ከመንፈሳዊ ምድራዊውን ከሰማያዊ መለየት ያስችላል፡፡ ጌታ የኒቆዲሞስን አሳቡን፣ ልቡን፣ ስሜቱን፣ ዕውቀቱን ሁሉ ወደ ሰማያዊ ነገር እንዲያሸጋግረው ፈቀደ፡፡ ይህን በማድረግ ከሰማይ የወረደው እርሱም የሰው ልጅ በሰማይ የነበረው€ እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ ወደ ሰማይ መውጣትም የሚቻለው እርሱ ነው፡፡ በእርሱ የሚያምኑ ወገኖችን ከፍ ከፍ የሚያደርጋቸው ከፍ ያለውንም ነገር እንዲመለከቱ የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፡፡


  የኒቆዲሞስና የጌታ ግንኙነት ትኩረታችንን ወደ ክርስቶስ እንድናደርግ ያደርገናል፡፡ ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ነፍስ መዳን ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጥ ከእያንዳንዱም ወገን ጋር ሲነጋገር ያለውን ትህትናም እንገነዘባለን፡፡ ከኒቆዲሞስ ጋር ሲወያይ የአዲሱን ልደት ጠባይ ዘርዝሯል፡፡ ኒቆዲሞስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ማወቅ ፈልጓል፤ ይሄንን መንግሥት ለማወቅ በውኃና በመንፈስ ይጠመቅ ዘንድ ግድ መሆኑን ያስረዳል፡፡


  ይህ ሁኔታ አስፈላጊ ነው፤ ክርስቲያን ዘወትር የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ እንዲኖር ያስችለዋልና ይጠመቅ ዘንድ የግድ ነው፤ በመንፈሱም እንዲኖር ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ጌታ ከምድራዊ ነገሮች ያወጣና አሳባችን ሰማያዊ በሆነው ጉዳይ እንዲያዝ ያደርጋል፡፡ ይህንን ማድረግ የምንችለው ከሰማያዊው ጋር ሕብረት ስንፈጥር መሆኑን ይነግረናል፡፡


  ጌታ ጥምቀቱን ከመስቀሉ ጋር አያይዞታል ፡፡ እግዚአብሔር አብ ለሰው ልጆች ሁሉ ያለውን እውነተኛ ፍቅር የገለጠበት፣ የባሕርይ ልጁን ወደ ዓለም በመላክ ዓለሙ ዘላለማዊ ሕይወትን ያገኝ ዘንድ ልጁ ከፍ ከፍ ያለበትም የነገሠበትም ዙፋኑ ነውና፡፡ አዲሱን ልደትን በማንሣት ጌታ ከፍርሃት ባርነት አውጥቶ መለኮታዊ የሆነውን ብርሃን እንድንመለከት ያደርገናል፡፡


  ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ጌታ ሲጠመቅ የነበረውን ሁኔታ ሲነግረን ለሚያምኑ ወገኖች ያለውን አንድምታም ሲገልጽ ደስታው ፍጹም ነበር፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ

  1.ስለ አዲሱ ልደት ገለጻ /1፡13/


  2.አዲሱ ልደትና የመስቀሉ ሥጦታ /14-17/


  3.አብርሆትና እምነት /18-21/


  4.በጌታ ጥምቀት ጊዜ የዮሐንስ ሁኔታ /22-36/ ተዘርዝሯል፡፡


  ስለ አዲሱ ልደት ገለጻ

  ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንደ ሰው ነበረ /ቁ.1/€ ኒቆዲሞስ የአይሁድ ስም ሲሆን ትርጓሜው ሕዝብን ያሸነፈ€ ማለት ነው፡፡ የአይሁድ አካል የሰንሃድሪን አይሁድ ሸንጎም አባል ነው፡፡ መለኮታዊው ጥሪው መላውን የሰው ልጆች ያካተተ ነው፡፡ የመደብ ልዩነት አልተደረገበትም፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ሓላፊነት ከነበሩ የመንግሥትና የሃይማኖት መሪዎች መካከል ለዚህ ጥሪ መልስ የሰጡ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ከፈሪሳውያን መካከል እጅግ ጥቂቶች፤ ከጥቂቶቹ አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡


  ጌታን ሊያነጋግር የመጣው ብቻውን ነው፡፡ ምናልባት አንድ ወይም ሁለት አጃቢዎች ሳይኖሩት አይቀሩም፡፡ በአይሁድ ሸንጎ የተከበረ ሰው ነበረ፡፡ ጌታ ግን ይህችን አንዲት ለመዳን የወሰነች ነፍስ ዝቅ አላደረጋትም፤ ሞትን የተቀበለው ስለ እያንዳንዱ ነፍስ ነውና፡፡ ፈሪሳውያን ለመለኮታዊው እውነት የሰጡት መልስ ጥላቻና የዓመጽ መንፈስን የተመላ ነው፡፡ ነገር ግን ከተማሩ አይሁድ መካከል ጌታን ለማግኘት የቸኮሉ በሩም ተከፍቶ የጠበቃቸው ጥቂቶች ነበሩ፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ በተማሩም ባልተማሩም ወገኖች ላይ ይሠራል፡፡ በተራውም ሕዝብ፣ በአለቃውም፣ በየዋኁም፣ በዓመጸኛውም ላይ ይሠራል፡፡


  ኒቆዲሞስ ደረጃው ከአመጸኞቹ ቢሆንም ወደ ጌታ መጣ፤ ጊዜው ሲደርስ የቻለውን ያህል ይጠይቅና ያውቅ ዘንድ ሞከረ፡፡ በጥያቄ ላይ እንደነበረ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ጊዜው ሲደርስ ለደቀ መዛሙርቱ ያልተቻለው ለዚህ ሰው ተቻለ፡፡ ከጲላጦስ አስፈቀዶ አዲስ ባሳነጸው መቃብር ላይ እንዲቀበር አደረገ፡፡


  ቤን ረጊን በአይሁድ ታሪክ መጽሐፍ ስለ ኒቆዲሞስ ሲናገር ይህ ሰው በጣም ሀብታም ከመሆኑ የተነሣ በኢየሩሳሌም የነበሩ ብዙዎችን ለብዙ ዓመታት ይረዳ ነበር ይላል፡፡


  እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን /ቁ.2/አለው፡፡


  ቅዱስ ዮሐንስ ኒቆዲሞስን በብዙ ቦታዎች ጠርቶታል፡፡ ጌታን ማታ ማታ ይጎበኝ እንደነበረ ተገልጧል፤ ይህ ሁኔታ ሦስት ጊዜ ያህል ተጠቅሷል /ዮሐ.ዮሐ.3፡2፣ 7፡50፣ 19፡39/


  ስለምን ወደ ጌታ በምሽት መጣ

  1.የመጀመሪያው ምክንያት ጌታችን በአደባባይ የሚያስተምረውን ትምህርት ከሰዎች መስማቱ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ጌታ በአደባባይ የሚያደርገውን ምልክት በሕዝብ መካከል በግልጽ መጥቶ ማየት አልወደደም፡፡ ድኅነትና ነፍስን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በጥሞና ከጌታ ሥር ቁጭ ብሎ መነጋገር ልቡ ፈቅዷል፡፡ቃሌስ በቅንነት ለሚሄድ በጎ አያደርግምን /ሚክ.2፡7/ ተብሎ እንደተጻፈ የቅንነትን መንገድ መርጦ ወደ ጌታ ቀርቧል፡፡


  ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ይነጋገር ዘንድ ወደደ፡፡ ጌታ እንኳን ከሕዝቡና ከደቀመዛሙርቱ ተለይቶ ከአብ ጋር ሲነጋገር የሚያድርበት ጊዜ ነበር፡፡ እኛማ ሌሊቱን በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር እንደምን መነጋገር ይገባን ይሆን፡፡ በተለይ በሌሊት ሁሉንም ነገር ትተን ከጌታ ጋር የግል ጭውውት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ አዲሱን ሕይወትና የዚህን ሕይወት ባህርይ፣ በዚህ ሕይወትም ውስጥ ካለች ከመንፈስ ሕብረት ተካፋዮች እንሆን ዘንድ ይገባናል፡፡


  2.ሁለተኛው ምክንያት ምናልባት ጥበብን ለመማር የማታው ጊዜ የተሻለ እንደሆነ በመረዳቱ ነው፡፡ ጌታ ቀን ቀን ሕዝቡን በማስተማር ተይዞ እንደሚውል ያውቃል፡፡ ስለዚህ ኒቆዲሞስ ምሽት እስከሚመጣ ድረስ ጠበቀ፡፡ ጌታን ለማግኘትና የድኅነት ጨዋታን ይጨዋወቱ ዘንድ ወደደ፡፡


  3.ሦስተኛው ምክንያት አንዳንድ ምልክቶችን ከተመለከተ በኋላ ጌታን ለማግኘት የመጀመሪያውን ዕድል በምሽት አግኝቶ ይሆናል፡፡ ሁሉም ሰው ሲተኛ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መንፈሳዊ የሆነች ምሽትን ማሳለፍ ፈልጎ ይሆናል፡፡ ምናልባትም እንዲህ አይነት ዕድል ወደፊት ሊገጥመው እንደማይችል ሥጋት አድሮበት ሊሆን ይችላል፡፡


  4.አራተኛው እንደ ነቢዩ ዳዊት ምሳሌውን ሊከተል ፈልጎ ::ዳዊት ሌሊቱን ለምስጋና ይጠቀምበት ነበርና /መዝ.36፡6፤119፡148/


  5.አምስተኛው ምናልባትም ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ ዘንድ እየሄደ መማሩ ለካህናት አለቆች ወሬው ሊደርስ ይችላል ብሎ ከፍርሃት የተነሣ ሊሆን ይችላል፡፡


  6.ስድስተኛው ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ ዘንድ መድረሱን አይሁድ ቢያውቁ ጌታችንን ለመዋጋት ቁጣቸውን ይጨምርላቸዋል፡፡ ኒቆዲሞስን ራሱን ለመጉዳት አይሁድ ፈሪሳውያን ሊነሳሡበት ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን በጌታ ትምህርት የተሳበ ቢሆንም በቀን እንዳይሄድ እምነት አንሶት ሊሆን ይችላል፡፡


  7.ሰባተኛው ምክንያት ከምንም በላይ ጌታ የዓለም ብርሃን መሆኑን በእርግጠኝነት አለመረዳቱ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ ነው፤ የእስራኤል መምህር ነው፡፡ ሰማያዊውን ደስታ ገንዘብ ያደርግ ዘንድ አዲስ ልደት የሚያስፈልገው ሰው ነው፡፡ በምሽት ሲመጣ ደካማ የሆነ እምነትን ይዞ ነበር የመጣው፤ ነገር ግን የጌታ በር ተከፍቶ አገኘው፡፡ ጌታ ስሜቱን ሊጎዳው አልወደደም፡፡


  ሁሉ ነገር የሚቆጠረው እምነት እንደሰናፍጭ ቅንጣት ቀስ በቀስ በልቡ ውስጥ እንደሚያድግ ነበር፡፡ ጌታ የፈለገው ያች ቅንጣት አብባ፣ አፍርታ፣ ጌታ በሚሰቀልበት ጊዜ ትልቅ ዛፍ ትሆን ዘንድ ነበረ፡፡ እንደዚያ ሲሆን ነው በዚያ እምነት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው በድፍረት የጌታን ሥጋ የቀበረው፡፡


  ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በተገናኘ ጊዜ የአይሁድ ድካም በእርሱም ላይ ይንጸባረቅ ነበር፡፡ አስቀድመን እንዳልነው በብርሃን ሳይሆን በጨለማ የመምጣቱም ምክንያት ይህ ነበር፡፡ ነገር ግን መኃሪው አምላክ አልጠላውም፤ ትምህርቱንም አልከለከለውም፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ጌታ በጉጉት ከእርሱ ጋር ተነጋገረ፤ ከፍ ያለውንም ምስጢር ገለጠለት፡፡ በርግጥ ለኒቆዲሞስ የተሰወረ ነበረ፡፡ ጌታ ግን አብራራለት፤ ክፉ አሳብ ከነበራቸው ወገኖች አንጻር ሲመዘን ይህ ሰው ይቅርታን ያገኝ ዘንድ እንደሚገባው ጌታ ቆጥሯልና፡፡ ክፉ ሰዎች ይቅርታ የላቸውም፡፡


  ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ ከአይሁድ የተለየ ቢሆንም ጌታን የቆጠረው ሰው አድርጎ ነው፡፡ ይናገረው የነበረው እንደ ነቢይ ነው፡፡ ያደረገውን ምልክት እያደነቀ ነበር የጠየቀው፡፡


  መምህር ሆይ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን /ቁ.2/ አለው፡፡


  ታዲያ ኒቆዲሞስ ሆይ ስለምን በምስጢር በምሽት መጣህ? ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣ የእግዚአብሔር የሆነውንም ነገር እንደሚናገር እያወቅህ፡፡ ስለምን ከእርሱ ጋር ነገሮችን በግልጽ አልተወያየህም? ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስን እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን አልጠየቀውም፡፡ አልወቀሰውምም፡፡ ነቢዩ እንዲህ ይላል €œአይጮኸም፤ ቃሉንም አያነሣም፣ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም፡፡ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፣ የሚጨስንም ክር አያጠፋም€ /ኢሳ.42፡3/ ጌታ ራሱ እንዲህ ብሏል፡፡ ዓለሙን ላድን እንጂ በዓለሙ ልፈርድ አልመጣሁም፡፡ /ዮሐ.12፡47/


  €œእግዚአብሔር ከርሱ ጋር ከሆነ በስተቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና /ቁ.2/


  የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትሕትና ተመልከቱ! እንዲህ አላለም €œእኔ ሁሉን በራሴ ማድረግ ይቻለኛልና የማንም እርዳታ አያስፈልገኝም፡፡ እኔ ራሴ እግዚአብሔር ነኝ፡፡ የያዝኩት ኀይል የአባቴን ኀይል ነው፤ ይህንን ቢል ለሚያዳምጡት ወገኖች ከባድ በሆነ ነበር፡፡


  ነገር ግን ድርጊቱን ሲፈጽም በተመሳሳይ መንገድ አልነበረም፤ ምልክትን ሲያደርግ በኀይል ነው፤ ስለዚህም እንዲህ አለ €œልትነጻ እወዳለሁ /ማቴ.8፡3/ ጣቢታ ተነሽ /ማር.5፡4/ እጅህን ዘርጋ /ማር.3፡5/ ኀጢአትህ ተሠረየችልህ /ማቴ.9፡2/ ፀጥ በል /ማር.4፡39/ አልጋህን ተሸከምና ሂድ /ማቴ.9፡6/፤ አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ /ማር.5፡8/፤ ማንም ስለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት ማር.11፡3/፤ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ /ማር.23፡43/፡፡ ለቀደሙት አትግደል እንደተባለ ሰምታችኋል የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል እኔ ግን እላችኋለሁ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፡፡ /ማቴ.5፡21-22/ ተከተለኝ ሰውን አጥማጅ አደርግሃለሁ /ማቴ.1፡17/፡፡


  በማንኛውም ሁኔታ ታላቅ ሥልጣኑን እንመለከተዋለን፡፡ ስለዚህ ሲሠራ ማንም ወገን በርሱ ላይ ስህተትን ማግኘት አይቻለውም፡፡ ነገር ግን ሊያጠምዱበት የሚቻላቸው በአንድ መንገድ ብቻ ነው እርሱም በንግግሩ ብቻ ነው፤ ማለት ንግግሩን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም፡፡


  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡-

  ስለዚህ ነው ጌታ ኒቆዲሞስን በግልጥ ያናገረው፤ ነገር ግን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን በመግለጽ አልጀመረም፤ ምልክት የሚያደርገው በተመሳሳይ ሥልጣን መሆኑን አልገለጠለትም፡፡


  ኒቆዲሞስ በሥሙ ከሚያምኑ ከጌታ ጋር ግን ግንኙነት ከሌላቸው ወገኖች አንዱ ነበረ፡፡ ስለዚህ በምሽት ወደ ጌታ ዘንድ መጣ፡፡ የመጣው ወደ ብርሃን ቢሆንም በጨለማ መጣ፡፡


  ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ የመጣው ወደ ጌታ ቢሆንም የመጣው በምሽትና የሚናገረው በጨለማ ነፍሱ ነበር፡፡ ስለዚህ በሰው ሁሉ ላይ የሚያበራውን ብርሃን የሚናገረውን መልእክት ሊረዳው አልተቻለውም፡፡


  ኒቆዲሞስ መምህር ነበረ ወደ እውነተኛው ብርሃን በጨለማ የመምጣቱ ምስጢርም ምናልባት ለክብሩ ተጠንቅቆ ነው፡፡ የሚናገረውን ማንነት ገና አላወቀምና፤ መማሩ እንዲያፍር አደረገው፤ በግሌ እኔ መምህርን ማዳመጥ እንጂ ሰዎች እንደመምህር ሲያዳምጡኝ አይደለም የምጠቀመው፡፡ የመጀመሪያ በመሆን ፍላጎትና ዝንባሌ ያላቸውን ወገኖች ጌታ እንዲህ ብሎ ሲገሥጻቸው አውቃለሁ፡፡ እናንተ ግን መምህር ተብላችሁ አትጠሩ መምህራችሁ አንድ ነውና /ማቴ.23፡8/


  በማንኛውም ሁኔታ ኒቆዲሞስ በምሽት ወደ ጌታ የመጣው ለመጠመቅ አልነበረም ለመማርና የጌታ ደቀመዝሙርም ለመሆን አይደለም፡፡


  በአይሁድ ትውፊት መሠረት ማንም ወገን በምሽት ወደ አይሁድ እምነት፣ ለመገረዝ ወይም ለመጠመቅ አይመጣም፡፡ ይህ ሕግን መተላለፍ ነው፡፡ እንደ ተማሪ ከጌታ ሥር ቁጭ ብሎ ለመማር ሳይሆን የጌታን አሳብ ለማወቅና በጎዳናውም ይጓዝ ዘንድ ነው፡፡


  ለአንድ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጠንቅቄ አውቃለሁ ለሚል የአይሁድ መምህር ረቢ ብሎ ጌታን መጥራት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የሕዝብ አለቃ ነኝ ብሎ የሚያስብ ሰው በትህትና ረቢ ብሎ ሲናገር መመልከት በርግጥም ያስደንቃል፡፡€œመምህር ሆይ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን/ቁ.2/ ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ቢሆንም የተናገረው ፖለቲካ ወይም የአገር ጉዳይ አይደለም፡፡ ነፍሱ ስለምትድንበት ሁኔታ ብቻ ነው የጠየቀው፡፡


  ኒቆዲሞስ ስለ ጌታ አንድ ነገር ያውቃል፤ ጌታ በአይሁድ ምሁራን ወይም በታወቀ የአይሁድ ትምህርት ቤት ገብቶ የተማረ አይደለም፡፡ ትምህርቱ ከሰማይ ነው፡፡ ጌታ የያዘው የእውነትን ኀይል እንጂ የሰይፍን ኀይል አለመሆኑን ተገነዘበ፡፡ የሰውን ጥበብ ባለፈ ፍጹም መለኮታዊ ጥበብ እንደሚናገር ተገንዝቧል፡፡ የሚያደርገው ምልክት በመለኮታዊ ኀይል መሆኑን ተገንዝቧል፡፡


  በጣም አስደናቂው ንግግሩ €œእናውቃለን€ የሚለው ነው፡፡ ምናልባት ከርሱ ጋር ሌሎች ሰዎች እንዳሉ ያመለክታል፤ ወይም ፈሪሳውያንን ወክሎ እየተናገረ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ምግባቸውም መጠጣቸውም ወሬአቸውም ክርስቶስ ሆኗልና፡፡ ከእነርሱ መካከል ኒቆዲሞስ የሚያምነውን እምነት የሚያምኑ ፈሪሳውያን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ መካከል ጌታን በግልጥ ወይም በስውር ሊያገኘው የፈለገ ወገን የለም፡፡


  ኢየሱስም መልሶ እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው /ቁ.3/€


  ኒቆዲሞስ ምልክትን ማድረግ ለክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ ለማመኑ ማሣያ አድርጎ ቆጥሮ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ረበናት እምነትን ምልክት ከመሥራት ጋር አያይዘውታልና፡፡ ስለ ክርስቶስ ማንነት ለመመስከር ከዚህ ወንዝ ባሻገር ያቋረጠው የለም፡፡ ስለዚህ ጌታን ዕሤተ በጎነት ያለው መምህር፣ የእግዚአብሔር ሰው አድርጎታል፡፡ እግዚአብሔር ይስሐቅን €œአትፍራ እኔ ከአንት ጋራ ነኝና /ዘፍ.26፡24/ እንዳለው ሰው ዓይነት አድርጎ ገምቶት ነበር፡፡ ወይም እንደ መበለቲቱ ልጅ ኢያሱ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ከአንተም ጋር እሆናለሁ /ኢያ.1፡5/ ያለው ዓይነት ነቢይ ነበር ጌታ ለኒቆዲሞስ፡፡


  ሌሎች ብዙ አለቆችና ነቢያት ተመሳሳይ ልምድ ነበራቸው፤ ነገር ግን ኒቆዲሞስ ምንም እምነትን ይዞ ቢመጣም ከፈሪሳውያን ጠባብ አስተሳሰብ ልጓም እንዳይወጣ የሚያደርግ አዕምሮ ነበረው፡፡ የተማረውም ይኼንን እውነታ ነው፡፡ በጌታና በኒቆዲሞስ መካከል የነበረው ውይይት የሚከተሉት ነጥቦች የትኩረት አቅጣጫዎቹ ነበሩ፡፡


  1.የዳግም ልደት አስፈላጊነት እርሱም ውስጣዊው ዓለም የተሻለ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፤ እርሱም የእግዚአብሔር መንግሥት ነው፡፡ ይህ አባባል በቅብጥ፣ በሶርያ፣ በላቲን በመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጽሑፍ የተካተተ ነው፡፡ ዮስጢኖስ፣ ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ፣ ጠርጡለስ፣ አውግስጢኖስና፣ ዠሮም ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ጌታችን ኒቆዲሞስን እንደገና እንዲወለድ እንደጋበዘው ተረድቷል፡፡ ይህ አስደነቀው፡፡ አሳቡ በልቡ ውስጥ መዳህ ጀምሯል፡፡ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል አለ፡፡


  2.አዲሱ ልደት ከላይ ነው ሰማያዊ ነው /3/ ይህ ድርጊት በቅዱሱና በሰማያዊው የእግዚአብሔር መንፈስ ብቻ የሚፈጸም ነው፡፡ የሰውን አሳብ ሁሉ ያለፈ ስጦታ ነው፡፡


  3.አዲሱ ልደት የሚፈጸመው በውኃና በመንፈስ ነው /5/


  4.ይህ ልደት በኀይል ያለ በነፍስ የተመሰለ ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ምስጢሩን ሊገነዘበው አይችለም፡፡


  በአይሁድ ጽሑፍ እውነት የሚለው ቃል መደገሙ በእውነት ቅዱስ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ጌታችን የሚናገረው ነገር በጣም ጠቃሚና ትኩረት የሚያሻው መሆኑን ለመናገር ይጠቀምበታል፡፡


  ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ በርጋታ ለኒቆዲሞስ የገለጸለት ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዘንድ መምህር መሆኑን ማመን ብቻውን በቂ አለመሆኑን፣ ተአምራቱንም ማድነቅና የተለዩ መሆናቸውን ማወቅ በራሱ ግብ አለመሆኑን ነው፡፡ በርግጥም የሚያስፈልገው እንደገና መወለድ ነው፡፡ እርሱም ሰማያዊ የሆነ ልደት ነው፡፡ ሰማያዊ መንፈሳዊ የሆኑ ጉዳዮችን ለማየት ያስችላልና፡፡ በእናቱ ማኅፀን ያለ ፅንስ በዚህ ዓለም እየሆነ ስላለው ነገር የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት መመልከት አይቻለውም፡፡ እንደገና ከተወለደ ብቻ ነው የአዲሱን ዓለም ብርሃን መመልከት የሚችለው፡፡


  ሊያይ የሚለው ጌታችን አጽንዖት ሰጥቶ የተናገረው ግሥ ለእውነተኛ ክርስቲያን አስፈላጊ ነው፡፡ አዲሱን ልደት ያጣጥም ዘንድ ስለተወለደ እንዲመካ አይደለም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊመለከት ለመንግሥቱም እንደሚገባ ሊመላለስ ይገባዋል እንጂ፡፡


  ይህ ማለት አዕምሮውና ልቡ ሰማያዊ በሆነ ነገር ላይ ማተኮር አለበት ማለት ነው፡፡ ከሰማያዊ ሕግ ጋር አብሮ የሚሄድ ሕግን ያለማወላወል ሊከተል ይገባዋል፡፡ አዲስ ግብ፣ አዲስ ተስፋ አዲስ ኀይልን ገንዘብ አድርጎ፡፡


  በአዲሱ ልደት ክርስቲያን በአይነቱ የተለየ ኑሮን መኖር ይጀምራል፤ አሮጌውን የሰውነቱን ሕንፃ አፍርሶ መሠረቱ ክርስቶስ የሆነውን አዲስ ሕንፃ በማነጽ አሮጌው ሰዋችን ተወግዶ የክርስቶስን መልክ የያዘው አዲሱ ሰው ሊታይ ይገባዋል፡፡


  አስቀድመን ኀጢአት ጥንተ ተፈጥሮአችንን ስላጠፋው፣ የልባችንም ጥልቅ በኀጢአት ተይዞ ስለኖረ፣ ሥጋውያን በሥጋ ሕግና ፈቃድም የምንመራ ሆነናል፡፡ የምንመራውም የመልካም ነገር ጠላት በሆነ በዲያብሎስ ነበረ፤ ስለዚህ አዲሱ ልደት ልንሸሸው የማይገባ ጠቃሚ ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እውነት እውነት እልሃለሁ የሚለው የጌታ ቃል ለዚህ እውነት ማሣያ ነው፡፡


  የእግዚአብሔር መንግሥት ምንድነው? ከሰማያዊው መሲሕ ሌላ መመልከት እንደሌለብን የምታሳስብ መንግሥት አይደለችምን! በእኛ መካከል መንግሥቱን መሥርቶ ይኖራል፡፡ ከእርሱ ጋር አንድነትን ፈጥረን የምናየው፣ የምንኖረው ሁሉ ለዚህ ሕይወት እንደሚገባ ነው፡፡ እርሱ ቅዱስ ስለሆነ እኛም ቅዱሳን እንሆናለን፡፡ በእኛ የሚኖረው የእግዚአብሔር መንግሥት ትክክለኛ ትርጉምም ይኼው ነው፡፡ ጌታ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንሥሐ ግቡ /ማቴ.4፤17/ አለ፡፡ እንደገናም መንግሥተ ሰማያት በመካከላችሁ ናት /ሉቃ.17፡21/ ብሏል፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ያለንን ሥፍራ ሲናገር፡፡ ጌታ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ /ራዕ.1፡6/ ይላል፡፡


  ይህ መንግሥት ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረትን የምንፈጥርበት መንግሥት በመሆኑ እንዲህ ተብሏል፡-€œየእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችም€ /ሮሜ.14፡17/


  ይህ መንግሥት ለዘላለማዊ ሕይወት ዋስትና ነው፡ ወደ ሰማይ እንድንጓዝ ጌታ በጌትነቱ ሲመጣ አስደናቂውን ክብር እንድንካፈል ያደርገናል፡፡ ከምንም በላይ አሳባችንን ከፍ ከፍ አድርጎ ውስጣዊ ነፍሳችንን የመጨረሻውን ቀን እንድትመለከት ጌታ ሲመጣ ሰማያዊ ዘውድን ደፍተን ያለፍርሃት በፊቱ እንቆም ዘንድ የሚያስችለንን ጸጋ እንይዝ ዘንድ ያስችለናል፡፡


  የጌታን ቃል እንደገና በሌላ አባባል እንግለጠው ብንል ዳግመኛ ካልተወለድህ ከመንፈስ ጋር ኅብረት ካልፈጠርህ በጥምቀት ልጅነትን ካላገኘህ እኔን በተመለከተ ትክክለኛ የሆነውን አሳብ አታገኝም´የሚል ይሆናል፡፡


  €œኒቆዲሞስም ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? /ቁ.4/ በማለት ጠየቀ፡፡


  የኒቆዲሞስ ጥያቄ የእውቀት ድካሙን ይገልጣል፡፡ ጌታ የሚናገረው በመንፈሳዊ ቋንቋ ነው፡፡ የኒቆዲሞስ ልብ ነገሮችን የሚያገናኘው ቁሳዊ ዓለማዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ነው፡፡ ቁሳዊ ነገሮችን ከልቡናው ከአእምሮው ካላወጣ መንፈሳዊና ሰማያዊ የሆኑ ምስጢራትን እንደምን ሊገነዘብ ይችላል? ያኔ ነው ወደ እውነት መድረስ የሚቻለው፡፡ በእግዚአብሔር መንፈስ አዲስ መንፈሳዊ ጉልበትን ይዞ ምስጢርን መረዳት የሚቻለው፡፡


  ኒቆዲሞስ ጌታ በተናገረው አዲስ ልደት ተደንቋል፤ ልክ እንደ ሌሎች አይሁድ ዘመዶቹ የአብርሃም ዘር በመሆኑ የሚመካ ነው፡፡ ጌታ ደግሞ እንደገና ተወለድ እያለው ነው፤ አይሁድ ለእግዚአብሔር የተመረጡና የተወደዱ አድርገው ራሳቸውን ይቆጥሩ ነበር፡፡


  በነቢያትና በተስፋው ቃል ኪዳን የተቀደሱ ሕዝቦች ነን ይሉ ነበር፡፡ ከምንም በላይ እግዚአብሔር ከእነርሱ አባቶች ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር፡፡ ልዩ መቅደስና መሥዋዕትም ነበራቸው፡፡ ኒቆዲሞስ እስራኤላዊ ብቻ አልነበረም ፈሪሳዊም ጭምር እንጂ፡፡


  ምን ዓይነት ከዚህ የበለጠ ልደት ጌታ ይሰጠኛል ብሎ ሊያስብ ይችላል? አይሁድ መሲሑ ሲመጣ የእስራኤል መንግሥት እንደሚያምንበት እንደገናም እንደሚወለዱ ይገምታሉ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ በነበራቸው ኩራትና ትምክህት አንጻር ሲመዝኑት ይህ የሚሆን አይመስላቸውም ነበር፡፡ እነርሱ አሁን ከያዙት የአብርሃም ልጅነት የከበረ ልደት ያለ መስሎ አይታያቸውም ነበር፡፡ ስለ ትውልድ ሀገራቸው ይመኩ ነበር፤ ስለዚህ ሌላ ልደት መስማት የሚሆንላቸው አይደለም፡፡


  ይህ ሁሉ ነገር እያለ ኒቆዲሞስ ጀርባውን ለጌታ አልሰጠም፤ እርሱ የጎደለው አንድ ነገር እንዳለ አምኖ ትምህርቱን ቀጥሏል፡፡ በግብሩ ምንም እንኳን መምህርና አለቃ ቢሆንም በትሕትና እውነተኛ የሆነ ነገርን ለመማር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጧል፡፡ ነገር ግን ጌታ የሚለው አዲስ ልደት የማይቻል እንደሆነ ገምቷል፡፡ አስደናቂ ሰው ነው፡፡ ረጅም ዘመን የትምህርትና የአመራር ልምድ ያለው ሰው ከጌታ እግር ሥር ተንበርክኮ አዲስ ነገርን ሲማር መመልከት ያስደንቃል፡፡ ለእውነተኛ አለቃ ጌታ የሰጠው ምሳሌ አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል፡፡ አሁን ኒቆዲሞስ ስለ ትምህርትና ስለ አመራር ልምዱ ሲመካ አንመለከተውም፡፡ እስከመጨረሻው እስትንፋሱ ድረስ ሲማር እንጂ፡፡ አምብሮስ እንዲህ ይላል፡- የኒቆዲሞስ ሁኔታ የሚያሳየን መማር የማያስፈልገው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ነው ይላል፡፡


  ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ መጣ፤ ከፍ ያሉ ነገሮችን አዳመጠ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ተራ ሰው የሚገልጣቸው አይደሉም፡፡ ማንም ሰውም ከዚህ አስቀድሞ ሰምቷቸው አያውቅም፡፡ በቅፅበት ኒቆዲሞስ ወደ ከፍታ ወጣ፤ ነገር ግን መረዳቱ ጨለማ ነበር፡፡ ነገር ግን በራሱ ማስተዋል ገና የቆመ በመሆኑ ሊሸከማቸው ስላልቻለ ወደቀ፤ የጌታን ቃል እንዴት ሊሆን ይችላል? በማለት ጠየቀ፡፡ ጌታ የተናገረውን ነገር እንዲያብራራለት ሰው ከሸመገለ በኋላ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን በማለት ማብራሪያ ጠየቀ፡፡


  ኒቆዲሞስ ስለ መንፈሳዊ ልደት ሰምቷል፡፡ ነገር ግን በመንፈስ አልተለማመዳቸውም /አያውቀውም/፡፡ኒቆዲሞስ ትውክልቱን ያደረገው ቁሳዊ መረጃ ላይ ነው ፤ይህንን ትልቅ ትርጉም ለመረዳትና ለመተርጎም ምሳሌ አድርጎ ያቀረበው የሰውን የሥጋ ልደት ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል €œለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም€ /1ቆ.2·14/


  በዚህ ሁሉ ነገር ኒቆዲሞስ ክብርና ጉጉት ይታይበታል፡፡ ጌታ የነገረው ነገር አላስቆጣውም፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ የማይቻል መሆኑን አስቦ ጥያቄ ጠይቆ ዝም አለ፡፡ ሁለት ነገሮችን ተጠራጥሯል፡፡ ምን አይነት እንደገና መወለድ እና የእግዚአብሔር መንግሥት፡፡ አይሁድ በየትኛውም ጊዜ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የተናገሩት ነገር የለም፡፡ ስለ ዳግም ልደትም እንዲሁ፡፡ ስለነዚህ ነገሮች ሰምተውም አያውቁም፡፡ ኒቆዲሞስን ያስደነቀውም ነገር ይህ ነው፡፡


  ቅዱስ አውግስጢኖስ እንዲህ ይላል፡- ይህ ሰው ከአዳምና ከሔዋን የሚደረግ ልደትን ሰምቷል፤ ከእግዚአብሔርና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለሚደረገው ልደት ግን አያውቅም፡የሚያውቀው ዘርን የሚተኩ ወላጆች በሞት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ነው፡፡ ነገር ግን ሕይወትን ስለሚሰጠው ስለ አዲሱ ልደት ያለው ግንዛቤ ከመረዳት በታች ነው፡፡ ንብረታቸውን የሚወርሱ ልጆችን የሚወልዱ ቤተሰቦች ያውቃል፡፡ ነገር ግን ዘወትር የሚኖሩ ልጆችን የሚወልዱ የማይሞቱ ወላጆችን በተመለከተ እውቀት የለውም፡፡ ሁለት ዓይነት መወለድ አለ፡፡ አንደኛው በምድር የሚደረግ ሁለተኛው ሰማያዊ፡፡ የመጀመሪያው ከሥጋና ከደም ሁለተኛው ከውኃና ከመንፈስ፤ የመጀመሪያዎቹ ለሞት የተጋለጡ ናቸው የኋለኞቹ ዘላለማውያን ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የተወለዱት ከወንድና ከሴት የኋለኞቹ ከእግዚአብሔርና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ኒቆዲሞስን በተመለከተ የሚያውቀው አንድ ልደትን ብቻ ነው፡፡


  ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ /5/


  ጌታ ይህንን እውነት ዝቅ አድርጎ እንዳይመለከተው በማሰብ አስቀድሞ የተናገረውን ነገር ደገመለት ፡፡ በርግጥ የእግዚአብሔር ቃል አዎ አይደለም ከሚለው አፍአዊ ነገር በዘለለ መልስን የሚጠይቅ ነው፡፡ ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ ከመረዳት አቅሙ በላይ ቢሆንም ጌታ እንደገና መወለድ ትምህርቱ ላይ ጠንከር ብሎ ሄዷል፤ ያለዚህ ልደት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየትም ለመግባትም የሚያስችል መንገድ የለም፡፡


  ሰው ከውኃና ከመንፈስ መወለድ አለበት ይላል፤ ስለምን ውኃን ይጠቀማል? ውስጣዊ የመንፈስ መታጠብን ለማመልከት ነው፡፡ /ቲቶ.3፡5፣ 1ቆሮ.6፡11፣ ሕዝ.36፡25/ €œ


  ይህ ውስጣዊ የመንፈስ መታጠብ በመንፈስ ቅዱስ የሚፈጸም ነው፡፡ እርሱ ብቻ ያጥባል ያነጻል ውስጣዊ ልባችንን አዲስ ያደርጋል፡፡ ጌታ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን በመቀየር በሰርጉ ቤት ለነበሩ ዕድምተኞች ደስታን እንደሰጠ በመንፈሱ የሰጠው ውጫዊ የሰውነት መታጠብ አይደለም፡፡


  ይህ ውኃ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ ይጠጣ በማለት ለሳምራዊቷ ሴት የነገራት የሕይወት ውኃ ነው፡፡ በያዕቆብ ጉድጓድ ውስጥ እንዳለው ውኃ አይነት አይደለም ያዕቆብ፣ ልጆቹና፣ ከብቶቹ የጠጡት ውኃ የሚያረካው የሥጋን ጥማት ነው፡፡ ጌታችን የሚሰጠን ውኃ ግን የነፍስን ጥማት የሚያረካ ነው፡፡


  በአዲሱ ልደት ውኃ አስፈላጊ ሆኗል፤ ጥምቀት የሚፈጸመው በመዘፈቅ ነውና፡፡ ይህም ሞትን የመቀበልና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመቀበር ምልክት ነው፡፡ ከእርሱ ጋር እንነሣ ዘንድ የግድ ያስፈልገናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡-


  እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፣ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን€


  ከውኃና ከመንፈስ መወለድ የአሮጌውን ሰው መሞትና የአዲሱን ሰው ትንሣኤ ይጠይቃል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የሆነውን አዲስ ሕይወትም መቀበል ነው፡፡ እርሱም የትንሣኤ መንፈስ ነው፡፡ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር የሚያደርገንን አዲሱን ሰው የመፍጠር ሂደት ነው፡፡ በፈጣሪያችን መልክ የተፈጠረውን አዲስ ሰው መመልከት ነው፡፡


  በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምነው መስቀሉን ሊሸከሙ የሚወዱ ወገኖች በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ አለባቸው፡፡ የጌታ ቃል ትርጉም ለኒቆዲሞስ ምንድነው ብላችሁ ብትጠይቁኝ መልሴ የሚሆነው ጌታ ከሥጋ ትውልድ ወጣ ብሎ መንፈሳዊውን ትውልድ እንዲያስብ ሳበው የሚል ይሆናል፡፡


  ጌታ እንዲህ በማለት የነገረው ይመስላል፡፡ ኒቆዲሞስ ሆይ እየተናገርሁህ ያለሁት ስለ ሌላ ልደት ነው፡፡ ስለምን ነው ንግግሬን ወደ ምድራዊ ነገር የምታወርደው፡፡ ስለምን የምነግርህ ነገር በተፈጥሮ ሕግ እንዲገዛ ታደርጋለህ? ይህ ትውልድ /ልደት/ በአይነት በሥጋ /በምጥ/ ከሚደረገው ትውልድ የተለየ ነው፡፡ አጠቃላይና የተለመደ ከሆነ ልደት ራስህን አውጣ፤ እኔ ሌላ ልደት ወደሚገኝበት መንፈሳዊ ዓለም ሾሜሃለሁና፡፡ ሰዎች ሁሉ ከዚህ አዲስ ልደት እንዲወለዱ እወዳለሁ፡፡ አዲስ ዓይነት ልደትን ይዤ ወደ ምድር መጥቻለሁ፡፡ ሰውን የፈጠርሁት ከምድር አፈርና ከውኃ ነበር፡፡ ይህ ያገለግለኛል ብዬ የፈጠርሁት ምርጥ ዕቃ የተፈጠረበትን ዓላማ ዘንግቶ አግኝቸዋለሁና እንደገና ከአፈርና ከውኃ ልሠራው አልፈቅድም እንደገና በውኃና በመንፈስ እንዲወለድ እፈቅዳለሁ እንጂ፡፡


  ምናልባት ከመካከላችሁ አንዱ እግዚአብሔር ሰውን እንዴት ከውኃ ፈጠረው ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ እኔ መልሼ እጠይቀዋለሁ፡፡ ሰውን እንዴት ከምድር አፈር አበጀው? ጭቃን እንደምን አድርጋችሁ ወደተለያየ ክፍል ትከፋፍሉታላችሁ? አጥንት፣ ነርብ፣ የደም ሥር፣ የደም ቧንቧ ከየት ተሠሩ? ቆዳ፣ ደም፣ ጉበት ከየት ተሠሩ? ይህ ታላቅ ሥራ ለምን የተከናወነ ይመስላችኋል? የተለያየውስ ቀለም? እነዚህ ሁሉ አይነቶች ውሁዶች ከየት ተገኙ? እነዚህ ሁሉ ነገሮች የምድርም የጭቃም አካል አይደሉምና፡፡


  ምድር ዘርን ስትቀበል እንዴት አድርገው ሥር ይሰድዳሉ? ነገር ግን በእኛ አካል ውስጥ ሲሆኑ እነዚህ ዘሮች ይፈጫሉ፡፡ ምድር ዘርን ምን መግባ ዘር ፍሬ እንዲያፈራ ታደርጋለች? እንደገናስ ሰውነታችን እንዴት በእነዚህ ዘሮች ይገነባል? ምድር ውኃን ትቀበላለች ወደሚያፈራ ወይንም ትቀይረዋለች፡፡ የእኛ ሰውነት ግን ወይንን ተቀብሎ ወደ ውኃ ይቀይረዋል፡፡ በአሳብ የምትሰጠው ፍሬ ሁሉ የእርሷ ውጤት መሆኑን በምን በምን በምን መንገድ ነው የሚለውን ግን ማስረዳት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ምድር በፍሬዋ ሰውነታችንን ታጠግባለች፤ በእግዚአብሔር ላይ ያለኝ እምነት ብቻ ነው እነዚህ ሁሉ ነገሮች የምድር ውጤቶች ናቸው ብዬ እንድቀበል የሚያደርገኝ፡፡


  አሁን እነዚህ ሁሉ ዓይነት ተጨባጭ ነገሮች በየቀኑ የሚከሰቱ ስለሆነ እምነት የሚይጠይቁ ስለሆነ መንፈሳዊ የሆነው ጉዳይ በቂ የሆነ ትኩረትና ቅድምና ማግኘት እንደሚኖርበት ትገነዘባላችሁ፡፡ የማይንቀሳቀሰው ምድር ለእግዚአብሔር ፈቃድ መልስ ይሰጣል ምድር የምትሸከመው ይህ ሁሉ ነገር የተገኘው ለዚህ ፈቃድ ነውና፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ከመረዳታችን በላይ የሆነ ጽንፍ የያዘ ብዙ ምልክት ይፈጠራል፤ መንፈስ ቅዱስ በውኃ ላይ በኖረ ጊዜ ምን ተከሰተ?


  ምናልባት ከመካከላችሁ አንዱ ውኃ ለዚህ ልደት ለምን ያስፈልጋል? ብሎ ቢጠይቀኝ መልሴ የሚሆነው ይህ ልደት አምላካዊ ጠቀሜታ አለው የሚል ነው፡፡ መቃብር፣ መቀበር እምነት፣ ሕይወትና፣ ትንሣኤ እነዚህ ሁሉ ምሥጢራት በጥምቀት ጊዜ የሚከናወኑ ናቸው፡፡ጭንቅላታችንን ውኃ ውስጥ እንነክራለን፤ ወደመቃብር እንደምንወርድ ሁሉ አሮጌውን ሰዋችን እንቀብር ዘንድ ጭንቅላታችንን ስናነሣ አዲሱ ሰው በተመሳሳይ ሁኔታ ይገኛል፡፡


  ከመንፈስ የሚወለድ እርሱ ማነው €œእንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዶ በአእምሮው መንፈስ ከሚታደስ ሰው በስተቀር€ /ኤፌ.4፡23/ በእርግጥ ይህ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ እንደገና የተወለደ ሰው ነው፡፡


  ይህ በዘላለማዊ ሕይወት የመተማመን ውጤት ነው፡፡ ይህም በጥምቀት አማካኝነት የሚፈጸም ነው፡፡ በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ሰው እንደምሕረቱ መጠን በአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብም በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ /ቲቶ.3፡5/ መንፈሳዊ ልጅነትን የተቀበለ ነው፡፡ በሌላ ንባብ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ይላል €œበመንፈስ ቅዱስ ስም ትጠመቃላችሁ€ /ሥራ.11፡16/፡፡ ከውኃና ከመንፈስ ከተወለደ ወገን ውጭ በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቀ ማነው? እውነት እውነት እላችኋለሁ ከውኃና ከመንፈስ ከተወለደ ወገን ውጭ በመንፈስ ቅድስ የተጠመቀ ማነው? እውነት እውነት እላችኋለሁ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለዳችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻላችሁም፡፡


  የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተጠመቀ ሰው ላይ ያደረ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረውን ምስጢር ይናገራል፡፡ ጥምቀት €œለአዲስ ልደት የሚሆን መታጠብ /ቲቶ.3፡5/ ተብሏል በመንፈስ ቅዱስ የሚሆን መታደስ ነው፡፡


  በምስጢረ ጥምቀት የኀጢአት እሥራት ይፈታል ስለዚህ ምክንያት ሕፃናት ሳይቀሩ ይጠመቃሉ፡፡€


  €œሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባ ዘንድ አይቻለውምና፡፡


  ጥምቀት ኀጢአታችን ሁሉ ያጥባል፡፡ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መቅደስ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ሰማያዊ ተፈጥሮአችንን ያድሳል ይህም በመንፈስ ቅዱስ ግብር የሚፈጸም ነው፡፡


  በቅዱስ ጥምቀት ሰው ከሰይጣን ኀይል ነጻ ይሆናል፤ እንደ አርባ ቀን ሕፃንም ይሆናል፡፡ ይህም በመንፈስ ቅዱስ የሚከናወን ነው፡፡ የተጠመቀውን ሰው የሚቀድስና የሚያነጻ መንፈስ ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሰው ላይ ሰይጣን የወደደውን ያደርግበት ዘንድ አቅሙ አይኖረውም፡፡


  ሰው በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አንድነትን ሲፈጥር እንደገና ከመወለዱ ባሻገር ክርስቶስን በሁለንተናው ይለብሰዋል /ገላ.3፡27/ ይህን በንባብ ብቻ የምንረዳው አይደለም፡፡የፍቅር መግለጫ ነውና፡፡ይህንን የምንረዳው ጌታ ሥጋችንን ተዋሕዶ በእኛ መጠን መወለዱና ስለእኛም ሲል ለአብነት በመወለዱ ነው፡፡

  መጋቢት 20 ቀን 2007 ዓ.ም.

  በዲ/ን ታደለ ፈንታው

  ምንጭ ፤ማኅበረ ቅዱሳን ድህረ ገጽ

       
   


  Mahibere Kidusa

  ""

  Read more »

 • ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር

  ሊቀ ልሣናት ቀሲስ ከፍያለው ጥላሁን

  ሥነ ምግባር፡- ማለት ደግነት፣ በጎነት፣ መልካም ጠባይ ማለት ሲሆን ክርስቲያን የሚለው ቃል ሲጨመርበት ደግሞ የተሟላና የተለየ ያደርገዋል፡፡ መልካም ጠባይ ማንም ሰው ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የተሟላ ዘላቂና የሁል ጊዜ ሆኖም ለሰማያዊ መንግሥት የሚያበቃው በክርስትና እምነት ሲኖሩ ነው፡፡

  ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፡- በምድር እያለን ሰማያዊ ኑሮ ኖረን ለሰማያዊ መንግሥት የምንበቃበት ሕይወት ነው፡፡ ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማስደሰት ነውና፡፡ በመሆኑም ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሚከተሉት ሕግጋት ሊለካ ይችላል፡፡

   1.    ሕገ እግዚአብሔር

  መጀመሪያውና ዋነኛው የክርስቲያን ሥነ ምግባር መለኪያው ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ አንድ ሰው ምናልባትም ሕይወቱ በሰው ፊት ሲታይ የማያስደስት በአፍአ ያለው ጠባዩ እንከን የማይወጣለት ሊሆን ይችላል፡፡ በሕገ እግዚአብሔር ተመዝኖ ካላለፈ ዋጋ የለውም በሰው ፊት መልካም ሆኖ የሚታይ ምግባር እግዚአብሔርን ሊያስደስት ያስፈልጋል፡፡ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ፡፡” ፌፌ.6፥6

   ፈሪሳውያን ከእነርሱ ውጪ የሆነውን ሁሉ የናቁ ያለእኛ ሕገ እግዚአብሔርን አክባሪ ከእኛም በላይ ጻድቅ የለም ባዮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዞችና ሥራቸው ሁሉ ከንቱ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ እንዲያውም “ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም” ማቴ.5፥20 በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስጠነቀቀ፡፡ እንዲያውም ከእነርሱ እርሾ /ትምህርት/ እንዲጠበቁ አስጠነቀቃቸው፡፡ “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” ማቴ.16፥6 አለ፡፡ ከዚህም ሌላ ብዙ ሠርተናል ሥነ ምግባራችን አስደሳች ነው እያሉ ለመወደስ በኩራት ይቀርቡ የነበሩትን ሁሉ አፍረው እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ ማቴ.19፣16-22

  የንጉሥ ሳዖል ሥራ በራሱ በንጉሡ አሳብ ሲመዘን ምክንያታዊና ትክክልም ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን ሊያስደስት አልቻለም፡፡ ቃሉን ስላላከበረ ለእርሱም ስላልታዘዘ ንቀኸኛልና ንቄሃለሁ ተባለ፡፡ ከንግሥናውም ወረደ፡፡ 1ሳሙ.15፥10-22 “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡” ዕብ.11፥6

   ክርስቲያን በጉዞው ሁሉ በጭፍን በራሱ እውቀት ብቻ አይመራም፡፡ በቃለ እግዚአብሔር ሕይወቱን እየመዘነ ሊራመድ ያስፈልጋል፡፡ “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ ራሳችሁን ፈትኑ፡፡” 2ቆሮ.13፥5 የክርስትና እምነት እያጸኑና እየጠነከሩ እየበሰሉ የሚጓዙበት ሕይወት ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ከትላንት ዛሬ ከአምና ዘንድሮ አድጐ ጠንክሮ መገኘት አለበት፡፡ “ንቁ በሃይማኖት ቁሙ ጐልምሱ ጠንክሩ” 1ቆሮ.16 በሃይማኖት መጠንከር ሲባል በጊዜውም /በተመቸ ጊዜ/ አለ ጊዜውም /ባልተመቸ ጊዜ/ መጠንከር ይገባል፡፡ “በጊዜውም አለ ጊዜውም ጽና፡፡” 2ጢሞ.4፥2 እንዲል፡፡

   ከሰው ሕግ ይልቅ የእግዚአብሔር ሕግ ቅርብ ነው፡፡ ከሰው ሕግ መደበቅ መሸሽ ይቻላል፡፡ ከእግዚአብሔር ግን ማምለጥ አይችልም፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ሥራ በእርሱ ዘንድ የተገለጠች ናት፡፡ የጲጥፋራ ሚስት ዮሴፍን ማንም አያየኝም ኀጢአት እንሥራ ብላ ለሁለት ዓመታት ባባበለችው ጊዜ ኩፋ.27፥25 እግዚአብሔር ከእርሱ እንደማይለይ እያንዳንዱም ሥራው በፊቱ የተገለጠ እንደሆነ ያመነው ኀጢአትን እንዴት እሠራለሁ በማለት መለሰለት፡፡ ዘፍ.39፥9፣ መዝ.138፥2-12

   ስለዚህ ክርስቲያናዊ አኗኗራችን መልካም ምግባራችን ትክክለኛ የሚሆነው በእግዚአብሔር ሲመዘን ብቻ ነው፡፡ ብልጣሶርን “በሚዛን ተመዝነህ ቀለህ ተገኘህ” ዳን.5፥27 የተባለው ለዚህ ነው፡፡ የሰው ልጁ ሕግ ተለዋዋጭና ጊዜያዊ ነው፡፡ ሕገ እግዚአብሔር ግን በዘመናት ብዛት የማይሻርና ቋሚ በመሆኑ ምግባራችን ከዚህ አንጻር ሊለካ ያስፈልጋል፡፡ “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ፡፡ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሠላም ነው፡፡” ሮሜ.8፥5‐6

   2.    ሕገ ልቡና

  እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ሁኔታ የሚመራመር ክፉና በጎውን ለይቶ የሚያውቅ አእምሮ ሰጥቶታል፡፡ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፡፡” መዝ.139፥10 እንዲል፡፡ በተጨማሪም “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው፡፡”መዝ.118፥105 ብሏል፡፡ ሕግ ለሙሴ ከመስጠቱ በፊት ደጋግ አባቶች በዚህ ሕግ እየተመሩ እንደሚገባ ኖረዋል፡፡

   የሰው ልጅ ማንም ባያስተምረውና ባይነግረው የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ያውቃል፡፡ “እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን እያንዳንዱም ወንድሙን እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና ይላል እግዚአብሔር፡፡” ኤር.31፥34 ምሳሌ አቤል “ከበጎቹ በኩራትና ከላቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ወደ ቃየል እና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም፡፡” ዘፍ.4፥4-5 ሄኖክ “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም እግዚአብሔር ወስዶታልና፡፡” ዘፍ.5፥24 ኖኅ “ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አገኘ በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡” ዘፍ.6፥9 እነዚህና ሌሎችም በሕገ ልቡና ተመርተው መልካም ተግባር የፈጸሙና እግዚአብሔርም ሥራቸውን የወደደላቸው ናቸው፡፡ ዕብ.11፥4-7

   የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር በራቀ ቁጥር ግብሩ ወደ እንስሳነት ይለወጥና የሚወቅሰው ኅሊና እንኳን ያጣል፡፡ “የሰው ልጅ ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ፡፡” መዝ.48፥12 ናቡከደነፆር በበደል ላይ በደል በመጨመሩ ለእግዚአብሔር ሕግ አልገዛም በማለቱ ግብሩ ሁሉ የእንስሳ ሆነ፡፡ ዳን.4፥32 ስለዚህ ክርስቲያን በመጽሐፍ ከተዳፈነው የእግዚአብሔር ሕግ በተጨማሪ በልቡናው ለተቀረጸው ሕግ ይገዛል፡፡ ራሲንም እየመረመረ ይጓዛል አጥፍቶም እንደሆነ ማንም ሳይፈርድበት በራሱ ላይ ይፈርዳል፤ ንስሐ ይገባል የጠፋው ልጅና በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ለዚህ ምስክር ይሆኑናል፡፡ ሉቃ.15፥11-19፣ ሉቃ.23፥41

   3.    የሰው ሕግ

  ይህን በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የአንድ ሀገር መንግሥት ወይም የሚያስተዳድር አካል ሕዝቡን ለማስተዳደር የሚያወጣው ሕግ ከሆነ ሁለተኛው ደግሞ ኅብረተሰቡ በባሕሉ ትክክል ነው ብሎ የተቀበለውና በወረቀት ያልተጻፈው ሕግ ነው፡፡ “በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ” 2ተሰ.2፥15 እንዲል፡፡

   ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ሕግ እንደሚገዛ ሁሉ የሰውንም ሕግ ከእግዚአብሔር ጋር እስከ አላጣላው ድረስ ሊያከብር ይገባል፡፡ አንድ ሰው ምንም ብጾም ብጸልይ፣ ለእግዚአብሔር እገዛለሁ ቢል የሚያስተዳድረውን አካልና የኅብረተሰቡን መልካም ባሕል ካፈረሰ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባሩን ጎደሎ ያደርገዋል፡፡ በሥራ ቦታ የታዘዘውን ካልፈጸመ፣ የሥራ ሰዓት ካላከበረ፣ በቤተ ክርስቲያን ያለውን ምግባሩን በሌላ ሥፍራ ካልገለጸው ዋጋ አይኖረውም፡፡ ለእግዚአብሔር እንደሚገዛ ሁሉ በሰውም ፊት ያለነቀፋ ሊኖር  ያስፈልጋል፡፡ “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ በእነርሱም መካከል የሕይወት ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ” ፊል.2፥15

   ሐዋርያው ከዚህም በተጨማሪ “ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለን” ብሏል፡፡ 2ቆሮ.8፥20 ይህ ሲባል ኀጢአትም ሲሆን የሰው ሕግ ወይም ባሕል ነውና ሁሉን መፈጸም አለበት ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ያስፈልጋል፡፡

   ለምሳሌ ከአንድ በላይ ማግባት፣ ጫት መቃም፣ ዋርሳ መያዝ፣ ባሕል በሆነበት አካባቢ የሚኖር ክርስቲያን ከሰው ጋር ለመኖር በሚል ሰበብ ይህንና ይህን የመሰለ የአረማውያኑን ኑሮ ይኑር ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ክርስቲያን በእንዲህ ዓይነት ሰዎች መካከል ሲኖር የቅድስናን ሕይወት በተግባር በመኖር ማንነቱን ሊገልጥ ያስፈልጋል፡፡ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡” ማቴ.5፥16

   ከዚህ አንጻር ብዙ ወጣቶች ሕገ እግዚአብሔርን ከኑሮአቸው ጋር አጣጥመው መጓዝ ሲከብዳቸው ይታያሉ፡፡ በእምነት የጸኑትን ሠለስቱ ደቂቅን፣ ዮሴፍን ሶስናን አይመለከቱም፡፡ እንኳን ክርስቲያን የሚለውን ስም የተሸከሙ ሲጠራም የሰሙት የማይመስሉ አሉ፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሰውና በእግዚአብሔር ፊት የምንኖረው ኑሮ እንደመሆኑ መጠን የግል መንፈሳዊ ሕይወትና ማኅበራዊ ኑሮ በማለት በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን፡፡

   ሀ. የግል መንፈሳዊ ሕይወት፡-

  የግል መንፈሳዊ ሕይወት ማለት እኛ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት የሚኖረን ሕይወት ነው፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን ግንኙነት ይመሠረታል፡፡ አንድ ሰው ፍቅሩ እግዚአብሔር ከሆነ ምግባሩ መንፈሳዊ ሕይወቱ ይህንኑ የሚገልጥ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረው ሕይወት የጠበቀ ለማድረግ ከሚያስፈልጉት ነገሮች ውስጥ ቃለ እግዚአብሔር፣ ንስሓ፣ ቅዱስ ቁርባን፣ ጸሎት ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡

   ቃለ እግዚአብሔር ለአንድ ክርስቲያን የሕይወት መስመሩን የሚያቃናለት ነው፡፡ “ቃልህ ተገኝቷል እኔም በልቸዋለሁ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ በስምህ ተጠርቼአለሁና ቃልህ ሐሴትና የልብ ደስታ ሆነኝ፡፡” ኤር.15፥16

   ንስሓ ማለት መጸጸት ማለት ነው፡፡ የክርስትና ሕይወት የንስሓ ሕይወት ነው፡፡ በንስሓ የበደለ ከበደሉ ይነዳል፡፡ ኀጢአተኛውም ጻድቅ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለግል መንፈሳዊ ሕይወት ሥራችሁን አቅኑ፡፡” ኤር.18፥11 ከንስሐ በኋላ ቅዱስ ቊርባን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡” ዮሐ.6፥53

   እንግዲህ ቃሉን ሰምተን ንስሓ ገብተን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ስንቀበል የግል መንፈሳዊ ሕይወታችን የተስተካከለ ይሆናል፡፡ የግል መንፈሳዊ ሕይወት ጽናት ደግሞ ለማኅበራዊ ኑሮአችን ወሳኝ ነውና፡፡ “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አሳብ ይህንም አዘውትር፡፡ ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፡፡ በእነዚህ ጽና ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ፡፡” 1ጢሞ.4፥15

   ለ. ማኅበራዊ ኑሮአችን

  ክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮው ከሌሎች ጋር በሠላምና በፍቅር ሊኖር እንዲሁም አልጫውን ዓለም በምግባሩ ሊያጣፍጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮ ተሳትፎ ውስጥ ሊይዝ  የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም፡-

   ዓላማ፡- ክርስቲያን እንደ ውኃ ላይ ኩበት እየተንሳፈፈ ወንዙ ወደ ሚወርድበት አቅጣጫ አይጓዝም፡፡ እንደሚወዛወዝ ዛፍም ወደ ነፈሰበት አያጋድልም፡፡ የራሱ የሆነ ውሳጣዊ ዓላማና አቋም አለው፡፡ “በምትሄድበት ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፡፡” ኢያሱ.1፥7 ከዚህ የተነሣ የሚሠራውን በጽናትና በትጋት ይሠራል፡፡ የጀመረውን ከፍጻሜ ያደርሳል፡፡ በመከራ አይናወጥም፡፡ መስሎ ለማደር እንደ ጊዜው አይለወጥም፡፡ በዓላማ ስለሚጓዝ ዓላማውን ያሳካል፡፡

   ክርስቲያን ምን ዓይነት ዓላማ ሊኖሩት ያስፈልጋል?

  መንግሥተ ሰማያትን መውረስ፡- አንድ ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣው ለጊዜያዊ ችግሩ ብቻ መፍትሔ ለማግኘት አስቦ ሳይሆን ሰማያዊ ክብርና ዋጋ ለማግኘት ነው፡፡ “ድንኳን የሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለን፡፡ 2ቆሮ.5፥1

   የሚታወቅና ግልጽ ዓላማ፡- ክርስቲያን ያለ ዓላማ በጭፍን አይጓዝም፡፡ ሳይታሰብ በድንገት በአጋጣሚ የሚል ነገር በርሱ ዘንድ እምብዛም ቦታ አይኖረውም፡፡ የሚታወቅ ግልጽ ዓላማ ኖሮት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሳካለት ይጸልያል፡፡ “ሳታቋርጡ ጸልዩ፡፡” 1ተሰ.5፥18 ከዚህ አንጻር አንዱን ዓላማው አድርጎ ይጓዛል ጋብቻ ወይም ምንኩስና መካከል ሆኖ አያወላውልም፡፡

   ራስን መግለጽ፡- ክርስቲያን በሄደበት ሁሉ ማንነቱን መግለጥ አለበት፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ መሰወር አትችልም፡፡ ይህም ሲባል እኔ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያን ነኝ እያለ በማወጅ ወይም በማስታወቂያ ሳይሆን አኗኗሩ ማንነቱን ይገልጠዋል፡፡ ይህም ኑሮው በቤተሰብ፣ በት/ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በአካባቢው ኅብረተሰብ ዘንድ ወዘተ…… መገለጥ አለበት፡፡

   ታማኝነት፡- እውነተኛ ክርስቲያን ምሎ የማይከዳ፣ አደራ የማያጠፋ፣ የማያወላውል ለምስክርነት የሚበቃ ነው፡፡ ታማኝ ሰው መልካም የሚለውን ይናገራል፡፡ የሚናገረውን ይሠራል በሓላፊነት ቢቀመጥ ያለ አድልዎ ወገናዊነት ያስተዳድራል፡፡ “በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሀለሁ፡፡” ማቴ.25፥21 ይባልለታል፡፡ ታማኝነት ለራስ ታማኝ መሆን ለእግዚአብሔር ሰዎች በመታመን ይገለጣል፡፡ ይህም በትዳር፣ በሥራ፣ በተሰጠው ሓላፊነት መታመን አለበት፡፡ ምሳሌ ዮሴፍ ዘፍ.39፥9

   ፍቅር፡- ክርስቲያናዊ ፍቅር የያዘ ሰው በሰውና በእግዚአብሔር ፍቅር ያለነቀፋ ይኖራል፡፡ ፍቅር የክርስቲያንነታችን መገለጫ ነው፡፡ አምላክን ከዙፋኑ ያወረደው ራሱንም እስከ ሞት አሳልፎ ለሰው ልጅ እንዲሰጥ ያደረገው ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህ አንደ ሰው ፍቅር ከሌለው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የለውም ማለት ይቻላል፡፡ የምናፈቅረው ማንን ነው?

   እግዚአብሔርን፡- እግዚአብሔርን ማፍቀር ሲባል እግዚአብሔርንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ማፍቀር ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ፍቅረ እግዚአብሔርን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡

   

  1. ትእዛዙን ማክበር፡- እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን በመፈጸም ይገለጣል፡፡ “ትእዛዙ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፡፡” ዮሐ.14፥21

  2. የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ መውደድ ይህን በሦስት ከፍለን መመልከት እንችላለን

  2.1.    ቅዱሳንን መውደድና ማክበር፡- ቅዱሳን እግዚአብሔር የመረጣቸው ያከበራቸውና የወደዳቸው ናቸው፡፡ “የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኗልና አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው የጠራቸው እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው ያጸደቃቸው እነዚህን ደግሞ አከበራቸው፡፡” ሮሜ.8፥29 ፍቅረ እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑ ቅዱሳንን በማክበር እንገልጻለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የትሕትናና የኦርቶዶክሳዊነት ውጤት ነው፡፡

  2.2.   ሀገርን መውደድ፡- ሀገር የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሰጠው ሀገር ሆኖ እርሱን ሊያመሰግን ሀገሩን ሊወድ ግዴታ አለበት፡፡ ሀገር ከሌለ ሠላም ካልሆነ እግዚአብሔርን በደስታ ማመስገን አይቻልምና፡፡ “ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽ ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድ፡፡” መዝ.136፥5

  2.3.   ቤተሰብን መውደድ፡- ክርስቲያን እምነትን፣ ምግባርን፣ ሥርዓትን በመጀመሪያ የሚማረው ከቤተሰቡ ነው፡፡ ቤተሰብ የመጀመሪያዎቹ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ነቢዩ ሙሴ የእግዚአብሔርን፣ የወገንን፣ የሀገርን ፍቅር የተማረው ከእናቱ ነውና፡፡ ወልደው፣ አሳድገው፣ አስተምረው ለትልቅ ደረጃ ያበቁትን ቤተሰቡን ክርስቲያን ሊወድ ይገባዋል፡፡ “ስለ ቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢኖር ሃይማኖትን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የከፋ ነው፡፡” 1ጢሞ.5፥8

  3.   የሰው ልጆችን ሁሉ ማፍቀር፡- /ፍቅረ ቢጽ/ የሰውን ልጅ ሁሉ ማፍቀሩ ፍቅረ ቢጽ ይባላል፡፡ ይህም በሥላሴ አርአያ የተፈጠረውን ሰው ሁሉ መውደድና ማፍቀር ነው፡፡ ይህም ኀጥእ ጻድቅ፣ አማኒ መናፍቅ፣ ዘመድ ባዕድ ሳይሉና ሳይለዩ ሁሉን አስተካክሎ መውደድ ነው፡፡ ይህም ትእዛዝ ጠላትን እስከመውደድ በመድረስ ነው፡፡ “በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሟችሁን መርቁ፣ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ፡፡” ማቴ.5፥44

   በአጠቃላይ ክርስቲያን ከአለባበሱ ጀምሮ ውጫዊ አቋሙም ሆነ አጠቃላይ ሕይወቱ በማናቸውም ጊዜና ቦታ ሁሉ ክርስቲያንነቱን ሊገልጡ ይገባቸዋል፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ኖረው ለሰውም ብርሃን ሆኖ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆኑትን አስደሰተ የሚባለው ያን ጊዜ ነው፡፡ እንግዲህ ክርስቲያን በምድር ሲኖር በግል ሕይወቱም ሆነ በማኅበራዊ ኑሮው ምን መምሰል እንዳለበት ራሱን ከላይ በተገለጸው በሦስቱ ሕግጋት አንጻር እየመረመረ መጓዝ አለበት፡፡ በግል ሕይወቱ ዘወትር ንስሓ እየገባ ቅዱስ ቁርባን በመቀበል እየጾመ፣ እየጸለየ፣ እየመጸወተ ሰማያዊ መንግሥትን ተስፋ በማድረግ ይጓዛል፡፡ በማኅበራዊ ኑሮውም ደግሞ ሰዎችን በሐዘናቸው ጊዜ ማጽናናት፣ በደስታቸው ተካፋይ መሆን፣ ከቸገራቸው ለችግራቸው ደራሽ በመሆን እውነተኛ ፍቅሩን ሊገልጽ ያስፈልጋል፡፡ “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን፡፡” 2ቆሮ.4፥10

  ምንጭ፤ ማሕበረ ቅዱሳን
   
   
  Read more »

 • “ኦ ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ” ማቴ. ፳፭፥፳፫

  አንተ በጎ እና ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሀልና በብዙ እሾምሀለሁ፡፡

  የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብር ኄር ይባላል፡፡ ገብር ኄር ማለት ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ስለ ታማኝ አገልጋይ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ስንኖር ለፈጣሪያችን ያለንን ታማኝነትና የምናገኘውን ዋጋ በመዋዕለ ሥጋዌው አስተምሯል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዜማ መክፈያነት የዐቢይ ጾምን ሳምንታትን ሲከፍል ገብር ኄርን ተጠቅሟልና እኛም ስለ ገብር ኄር ጥቂት እንበል፡፡


  ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ አንደበት አድሮ፤ “እከሥት በምሳሌ አፉየ፤ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት፤ አንደበቴን /ነገሬን/ በምሳሌ እገልጣለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ ታሪክና ምሳሌ እናገራለሁ” አለ፡፡ ይህም ማለት ወንጌልን በምሳሌ አስተምራለሁ፤ በመልከ ጼዴቅ ዘመን አስቀድማ የተሠራችና ታይታ የጠፋችውን ወንጌልን እናገራለሁ፡፡ ይህን ታላቅ ምሥጢር ሐዋርያው ሲያብራራ “. . . ከመ በአሚን ያጸድቆሙ እግዚአብሔር ለአሕዛብ አቅደመ አሰፍዎቶ ለአብርሃም ከመ ቦቱ ይትባረኩ ኲሎሙ አሕዛብ፤ . . . በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ” ብሏል፡፡ /ገላ. ፫፥፰፣ መዝ. ፸፯፥፪


  በዚሁ መሠረት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ለልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ ምሳሌ አስተምሯል፤ ከላይ በተገለጠው ኃይለ ቃል መነሻነት ሁለት ምሳሌያትና አንድ ቃለ ትንቢት ቀርበዋል፡፡ ከምሳሌያቱ የመጀመሪያው በዐሥሩ ደናግል አንጻር የቀረበው ምሥጢር ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ወጥተው ወርደው ነግደው ያተርፉበት ዘንድ ገንዘቡን ስለሰጠ አንድ ነጋዴ የሚናገረው ነው፡፡


  የትንቢቱ ምሥጢራዊ ይዘት የሚያስረዳውም ስለ ኅልቀተ ዓለም አይቀሬነት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ዕትማችን ወጥተው ወርደው ነግደው እንዲያተርፉበት ከጌታቸው የተሰጣቸውን መክሊት ስለተቀበሉት አገልጋዮች ሕይወት እንመለከታለን፡፡ ፈጣሪያችን አእምሮውን ለብዎውን /ማስተዋሉን/ ያድለን፡፡


  ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ያስተማራቸው ምሳሌያዊ ትምህርቶች በቅዱስ መጽሐፋችን በሰፊው ተጽፈው እናገኛለን፡፡ የእነዚህ ትምህርታዊ ምሳሌዎች መሠረታዊ አሳብና ዓላማም የእግዚአብሔርን መንግሥት የምናገኝበትን የታማኝነትን ሥራ እንዴት መሥራት እንደሚገባንና መሥራትም እንደምንችል ማስተማር ነው፡፡


  ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመንግሥተ ሰማያት ምሥጢር ያስተማራቸው ብዙ ምሳሌዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ብዙ ምሳሌያዊ ትምህርቶች መካከልም እንዲያተርፉበት መክሊት ስለተሰጣቸውና ስለተመሰገኑት መልካም አገልጋዮች፣ እንዲሁም መክሊቱን በመቅበሩ ምክንያት በጌታው ስለተወቀሰውና ፍርድን ስለተቀበለው ሰነፍ ሰው ታሪክ፣ የታሪኩም ምሥጢር ምን እንደሚመስል የተጻፈው ትምህርት ነው፡


  ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ምሳሌ የተናገረው /ያስተማረው/ በሚከተለው መልኩ ነበር፤ ‹‹ወደ ሌላ ሀገር የሚሔድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ ሀገር ወዲያውኑ ሔደ፡፡ አምስት መክሊትም የተቀበለው ሔዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፣ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፣ አንድ የተቀበለው ግን ሔዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ፡፡


  ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፡- ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፡፡ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡


  አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሔጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ መክሊትህ አለልህ አለው፡፡ ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፡- አንተ ክፉና ሐኬተኛ ባሪያ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁበትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር:: እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር፡፡ ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት ዐሥር መክሊትም ላለው ስጡት:: ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል:: ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል የሚል ነው፡፡


  መክሊት ጥንት የክብደት መለኪያ ነበር:: አንድ መክሊት 30 ኪሎ ግራም ያህል ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸውም መክሊት የሚለው ቃል ገንዘብን ያመለክታል፡፡


  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ እርሱን የምናገለግል ሁላችን እንደየዓቅማችን ማድረግ የሚገባንን መንፈሳዊ የአገልግሎት ሥራንና በአገልግሎታችን ውጤታማ በመሆናችንም ከእርሱ የምናገኘውን ዘለዓለማዊ ክብርና ዋጋን እንዲሁም መሥራት የሚገባንን ባለማድረጋችንም ምክንያት የሚገጥመንን መለኮታዊ ቅጣትን አመልክቶናል፡፡


  በዚህ ምሳሌ ውስጥ ባለ አምስት የተባለው በቂና ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ የተካ ያወጣ ነው፡፡ በተመሳሳይም ባለ ሁለት የተባለው እንደ መጀመሪያው ሁሉ ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣ ሲሆን ባለ አንድ የተባለው ደግሞ ተምሮ ሳያስተምር የቀረ በስንፍና በቸልተኝነት በማን አለብኝነት ሕይወት ተገድቦ የቀረ ሰው ነው፡፡


  በመሆኑም የባለ አምስትና የባለ ሁለት መክሊት ባለቤቶች የሆኑት ወጥተው ወርደው ደክመው፣ መከራ መስቀልን ሳይሰቀቁና ሳይፈሩ፤ ወድደው ፈቅደው የጀመሩትን አገልግሎት በማክበር ሕይወታቸውን ለታመነው አምላክ አደራ በመስጠት የተማሩትን ፍጹም ትምህርት ለሌላው አስተምረው፣ ሠርተው ያገኙትን ለሌላው አካፍለው ወገናቸውን እንደራሳቸው አድርገው ሲመለከቱ ባለ አንድ መክሊት የተባለው ግን ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ሃይማኖቴን ሲያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡኝ ብሎ ፈርቶ ሃይማኖቱን በልቡ ከመደበቅና ከመሠወር በቀር የተማረውን ትምህርት ሠርቶ ያገኘውን ሀብት ንብረት ለሌላው ሊያካፍልና የተሰጠውን አደራም ሊወጣ አልወደደም፡፡


  በምሳሌው ውስጥ እንደተገለጠው ሁለቱ ወገኖች በተሰጣቸው መክሊት ባለሁለቱ አራት ባለአምስቱ ዐሥር ማትረፋቸውን ለጌታቸው በገለጡ ጊዜ የመክሊቱ ባለቤት እጅግ አድርጎ እንዳመሰገናቸው ከላይ አንብበናል፡፡


  ይህ የመክሊቱ ባለቤት የተባለው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የተሰጣቸውን ሓላፊነት በአግባቡና በጽንአት ለተወጡት ሁሉ እርሱ ፍጹም ዋጋን የሚሰጣቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህም ሁኔታ “አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” በሚል ታላቅ የምስጋና ቃል ተገልጧል፡፡ ይህ ቃል በሃይማኖትና በበጎ ምግባር ለእግዚአብሔር የታመኑ ሁሉ ዘለዓለማዊና ፍጹም ደስታ ወደሚገኝበት መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ለሚያደርጉት የእምነት ጉዞ እጅግ ተስፋ የሆነ ቃል ነው፡፡


  በዚህ ምንባብ ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም እርሱን የምናገለግልበትንና ለእርሱ በመታመን ዘለዓለማዊ ክብርን የምናገኝበትን ዕውቀትን፣ ማስተዋልን፣ እምነትን፣ ተስፋን፣ የሥነ ምግባር ሀብትን፣ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን እንጠቀምባቸው ዘንድ ለእኛ ለሰው ልጆች እንደየዓቅማችን መጠን ሰጥቶናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሥጋችንን ምኞት ለማስፈጸም የተሰጡ ሳይሆኑ ነፍሳችን የምትከብርበትን መልካም ሥራን የምንሠራባቸው መሣሪያዎቻችን ናቸው፡፡


  በመሆኑም እርሱ በሰጠን የአገልግሎት በር ጸጋ በታማኝነት በማገልገል በሕይወት ዘመናችን ሁሉ መንፈሳዊውን ሀብት የምናተርፍ እንሆን ዘንድ የተላለፈልን አምላካዊ ምክር ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ የተጠራነው ፍሬ ልናፈራና ሌላውንም ልናተርፍ መልካም ሥራን ልንሠራ እንጂ የሥጋችንን ፈቃድ በመከተል የኃጢአት ባሮች ልንሆን አይደለም፡፡ መጽሐፍ እንዲህ አለ “ወኲሉ ዘከመ ተጸውአ ከማሁ ለየሀሉ፤ ሁሉ እንደተጠራ እንዲሁ ይኑር” /፩ኛ ቆሮ. ፯፥፳/


  ከላይ እንደተመለከትነው በልዑል አምላክ በእግዚአብሔር አንደበት አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ መባልን የመሰለ አስደሳችና አስደናቂ ነገር የለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚገኘው ሃይማኖትን በሥራ በመግለጥ እንጂ ሃይማኖትን በልቡና በመያዝ ብቻ /ሙያ በልብ ነው/ በማለት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ከእነዚህ እንደአቅማቸው መጠን መክሊት ተሰጥቷቸው በትጋታቸውና በቅንነታቸው ሌላ መክሊት ካተረፉት በጎና ታማኝ አገልጋዮች የምንማረው እውነታም ይህ ነው፡፡ በብዙ ለመሾም ለማደግ ለመጽደቅ በጥቂቱ መታመን መፈተን መጋደል ግድ ነው፡፡


  አንድ መክሊት የተሰጠውን ሰው ስንመለከተው ጌታውን ጨካኝና ፈራጅ አድርጎ ከመቁጠር ውጪ በተሰጠው መክሊት ወጥቶ ወርዶ ሊያተርፍ አልወደደም፡፡ መክሊቱንም ባስረከበ ጊዜ በጌታው ላይ የተናገራቸው ቃላት የእርሱን አለመታዘዝና አመጸኝነት ይገልጡ ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ ሰው በጥቂቱ መታመን ያቃተውና በአስተሳሰቡ ደካማነት እጅግ የተጎሳቆለ ሰው ነው፡፡


  በዚህ ምሳሌ መሠረት ይህ ባለ አንድ መክሊት የተባለው ሰው ዓላውያን ነገሥታት እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ በማለት ሃይማኖቱን በልቡ ሸሽጎና ቀብሮ በተቀደሰ ተግባር ሳይገልጠው ከመያዙ ባሻገር በጌታ ፊት በድፍረት ቆሞ አንተ ሕግ ሳትሠራ በአእምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ፤ መምህራንንም ሳትመድብ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ በሠራችሁ ብለህ የምትፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆንክን አውቃለሁና ፈርቼ ሃይማኖቴን በልቡናዬ ይዠዋለው በአዕምሮዬ ጠብቄዋለሁ የሚል ሃይማኖቱን ግን በሥራ የማይገልጥ ሰነፍ ሰውን ያመለክታል፡፡


  ለዚህ ዓይነት ሰው የጌታ መልስ ደግሞ በምሳሌው መሠረት የሚከተለው ነው፡፡ እኔ ሕግ ሳልሠራ በአእምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ፤ መምህር ሳልሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ አውቃችሁ በሠራችሁት ብዬ የምፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆኔን ታውቃለህን? እንዲህስ ካወቅህ ሹመትክን ልትመልስልኝ ይገባኝ ነበር፡፡ ወጥቶ ወርዶ ለሚያስተምር በሰጠሁት ነበር፡፡ አሁንም የእርሱን መምህርነት ሹመት ነሥታችሁ (ወስዳችሁ) ለዚያ ለባለ ዐራቱና ለባለ ዐሥሩ ደርቡለት! እርሱን ግን አውጡት የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ከበጎ ምግባር የተለየች እምነት የሞተች እንደሆነ ተጽፏልና፡፡


  ዛሬም እያንዳንዳችን በዓቅማችን መጠን መክሊት ተሰጥቶናል፡፡ ነገር ግን መክሊቱን እንደቀበረው እንደዚያ ሰው የተሰጠንን ቀብረን ለወቀሳና ለፍርድ እንዳንሰጥ በአገልግሎታችን ልንተጋ ይገባናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ ሲገልጥ “ወዘሂ ይትለአክ በመልእክቱ፤ ወዘሂ ይሜህር በትምህርቱ. . .፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚሰጥም በልግሥና ይስጥ›› (ሮሜ. ፲፪፥፯) በማለት ተናግሯል፡፡


  ለመሆኑ አሁን ባለንበት የስግብግብነት ወቅት ዛሬ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ…›› ተብሎ በእግዚአብሔር ሊመሰገን የሚችል ሰው ማን ይሆን? በእውነት እንዲህ ተብሎ የሚመሰገን በጎና ታማኝ ካህን በጎና ታማኝ መምህር በጎና ታማኝ ምእመን ታማኝ ሰባኪና ታማኝ ዘማሪ ማግኘት ይቻል ይሆንን? ትልቅ መሠረታዊ ሊሆን የሚገባው ጥያቄ ቢኖር ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ስለታማኝነት የሁላችንንም ሕይወት የሚዳስስና ሁላችንንም የሚመለከት ነውና፡፡ ነገር ግን መቼም አምላካችን ቸር ነውና በየዘመናቱ አንዳንድ ታማኝ አባቶችን እንደማያሳጣን ተስፋ አለን፡፡


  ምክንያቱም ዛሬም ቢሆን እንደአባቶቻችን እንደቅዱሳን ሐዋርያት በእምነት፣ በትዕግሥት በፍቅር በተጋድሎ በየውሐት በትሕርምት በጸሊዓ ንዋይ በትሕትናና በትጋት በማገልገል የተሰጣቸውን መክሊት የሚያበዙ አገልጋዮች አሉ፡፡ የእነዚህ ክብራቸው በምድርም በሰማይም እጅግ የበዛና ራሳቸውን አስመስለው በትምህርት የወለዷቸው ልጆቻቸውም ለቤተ ክርስቲያን የተወደዱ የተከበሩ ልጆች ናቸው፡፡


  ለምሳሌ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ነቢየ እግዚአብሔር ኢያሱን፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ቀሌምንጦስን፣ ቅዱስ ጳውሎስም ቅዱስ ጢሞቴዎስን ለቤተ ክርስቲያን አበርክተዋል፡፡ ሌሎችም አበው ቅዱሳን በወንጌል ቃል መንፈሳውያንና ትጉሃን የሆኑ ምእመናንን በሚገባ አፍርተዋል፡፡ ያላመኑትንም አሳምነው ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመመለስ ለዘለዓለማዊ ክብር የበቁ እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል፡፡ በተሰጣቸው ጸጋም አትርፈው አትረፍርፈው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሀብተ መንፈስ ቅዱስ እንድትጎበኝ አድርገዋል፡፡ የእነርሱም በረከታቸው ረድኤታቸው ቃል ኪዳናቸው ለሌሎች እንዲተርፍ ሆኖላቸዋል፡፡


  በመሆኑም ክርስቶስ በደሙ የከፈለውን ወደር የሌለውን ዋጋ ዓለም አምኖና አውቆ ተቀብሎ በክርስትና ሃይማኖት እንዲድንበትና እንዲጠቀምበት በማድረግ እንዲሁም በታማኝነትና በበጎነት አገልግሎታቸው ጥንትም ዛሬም ላለችዋና ወደፊትም ለምትኖረዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ድምቀትም ውበትም የሆኑት ቅዱሳን አበው ሊገኙ የቻሉት ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን ደስ ለማሰኘት በመድከማቸው ሳይሆን የተጠሩበትን ዓላማና የጠራቸውን እርሱን በሚገባ አውቀውና ከልብ ተረድተው ለዘለዓለማዊ ሕይወት ተግተው በመሥራታቸው ነው፡፡ (ገላ. ፩፥፲)


  “ወይእዜሰ ለሰብእኑ ነአምን ወአኮ ለእግዚአብሔር ወእምሰኬ እፈቅድ ለሰብእ አድሉ ኢኮንኩ ገብሮ ለክርስቶስ፤ አሁንስ ለእግዚአብሔር ያይደለ ለሰው ብለን እናመናለን፤ ለሰው የማደላ ከሆንኩስ፣ የክርስቶስ ባሪያ /አገልጋይ/ አይደለሁም” /ገላ. ፩፥፲/ በማለት ያስተማረው ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ ቃል በመነሣት በተለይ ደግሞ በክህነት አገልግሎት ውስጥ ያለ ሰው ከምንም በላይ በከፍተኛ መንፈሳዊ ሓላፊነት ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን በሃይማኖትም በሥነ ምግባርም ለሌላው አርአያ በመሆን እንደ እርሱ ሃይማኖትን ከምግባር ጋር አስተባብረው የያዙ ምእመናንን ማፍራት ማብዛት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ልንባል የምንችለው፡፡


  አሁን ባለንበት ወቅት በጎና ታማኝ አገልጋይ መሆን እንዳንችል ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ የችግሮቹም መሠረታዊ ምንጭ በተጠሩበት ጸንቶ መቆም ፈጽሞ አለመቻልና ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ በማድላት ሓላፊነትን መዘንጋት ናቸው፡፡ በሥጋዊ አምሮት ፍላጎትና ምርጫ ውስጥ ደግሞ መንፈሳዊ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት የሚያስችለንን የታማኝነት ሥራን መሥራት አይቻልምና በታማኝነት ከምናድነው ሰው ይልቅ መክሊታችንን በመቅበር ባለመታመን መሰናክል የምንሆንበት ሰው ሊበዛ እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡


  በመሆኑም ከእርሱ ዘንድ እንደ ዓቅማችን የተሰጠንን መንፈሳዊ ዕውቀት ሀብትና አገልግሎት ለሌላው በማድረስ መክሊታችንን ልናበዛ የምንችለውና አገልግሎታችን ወይም ክርስትናችን ውጤታማ የሚሆነው ምርጫችንን አውቀን እንደቃሉ ሆነንና ጸንተን ስንገኝ ብቻ ነው፡፡ ይህ ባለመሆኑ ነው ዛሬ ብዙዎቻችን በሕይወታችን ሌላውን ማትረፍ አቅቶን በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ በሚያስወቅስ የስንፍና መንገድ ላይ ቆመን የምንገኘው፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ‹‹ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ›› (ማቴ. ፳፬፥፵፪) ብሎናል፡፡


  ቃሉን የሰማንና የምናውቅ ሁላችን በሞቱ ላዳነን፣ በልጅነት ጸጋም ላከበረን፣ በትንሣኤውም ላረጋጋን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ከራሱ ጋር ላስታረቀን፣ በውኂዘ ደሙም ሕይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በረከትንና ዘለዓለማዊ ደስታን ለሰጠን አምላካችን በመታዘዝ አቅማችን በሚፈቅደው አገልግሎት ጸንቶ መገኘት ተገቢ ነው፡፡ በአገልግሎት የመጽናት ምልክቱ ደግሞ አትራፊነት ነው፡፡ ቅዱሳን ነቢያት፣ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ በአትራፊነት ይታወቃሉ፡፡ ለማትረፍ ግን ራሳቸውን ለእውነት ለአገልግሎት ለመከራ አሳልፈው በመስጠት ነው፤ በትንሹ መታመን ሲባል የእኛ አገልግሎት ከፈጣሪ ቸርነት ጋር ስለማይመጣጠን ነው፤ በብዙ እሾምሃለሁ ማለቱም በመንግሥተ ሰማያት ለዘለዓለም ከብሮ መኖርን ነው፡፡


  ከቅዱሳን ነቢያትም ሐዋርያትም ሰብአ አርድእትም ሊቃውንትም የሰማነውና ያየነው እውነት ምንጊዜም ትጉህ ሠራተኛ የሚሠራው መልካም ሥራ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዘመን ልዑል እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን፤ ምእመናንን፤ ሀገርንና ሕዝብን ለመምራት የጠራንና የመረጠን፤ በአገልግሎት ዐደባባይ ያስቀመጠን ሰዎች እጅግ ዕድለኞች ነን፤ ምክንያቱም የሕዝብን ችግርና አቤቱታ ሰምቶ ተቀብሎ መፍትሔ መስጠት ትርፋማነት ነውና፤ ትርፋማነት ደግሞ ወደ ትልቁ የሹመት መሰላል መውጣት ነው፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አገልግሎታችን ተደናቅፎ የሕዝባችን ችግር ሳይፈታ ቀርቶ የአገልግሎታችን ተቆጣጣሪ አምላካችን ቢጎበኘን “አንተ ሰነፍ አገልጋይ” ተብለን ወደ ውርደት አዘቅት እንዳንላክ መጠንቀቁ አይከፋም፡፡ የመሾም የመሻር የማሳደግና የማውረድ ሥልጣን የእግዚአብሔር ነውና፡፡ “ከእናንተ መካከል አንዱን እንኳ እንዳናስቸግር ቀንም ሌሊትም እንሠራ ነበር” /፩ኛ ተሰ. ፪፥፱/ በጎና ታማኝ አገልጋዮች ሆነን እንድንገኝ ጠንክረን ልንሠራ ይገባናል፡፡


  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  Read more »

 • የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ተግባር በዘመናችን

  ዓለማችን ለከንቱ ነገር የምትሮጥበት ጉዳይ እየበዛ መጥቷል፡፡ የአንዳንዶቹ ሩጫዎች ደግሞ ጭፍንና እግዚአብሔርን ያልተመረኮዙ በመሆናቸው የገዛ አእምሮን ለማይረባ ነገር አሳልፈው እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ኀጢአት በዓለም ነግሦ ፣ ክፋት እንደ ቅድስና ተቆጥሮ እየተዘወተረ ነው፡፡ በጨለማ ሥራ ከማፈር ይልቅ የሚመኩ ሰዎች ማየት ከጀመርን ሰነበትን፡፡ እያደር ጆሮ አይሰማው የለ! ብዙዎች በገሀድ ለዝሙት ሽር ጉድ ከማለት አልፈው ራሳቸውን የሰዶም ማኅበርተኛ አድርገው መብታችን ተረገጠ ማለት ጀምረዋል፡፡

   ሐዋርያው “እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤” (ሮሜ ፩፥ ፯ - ፳፰) ሲል የተናገረው ቃል እየተፈጸመባቸው ይገኛል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ገሞራውያን በሚል የሚጠሩት የግብረ ሰዶም ጉዳይ ነው፡፡

  ሰዶምና ገሞራ በዮርዳኖስ ሸለቆ ተቆርቁረው የነበሩ ከተሞች ሲሆኑ አብርሃምና ሎጥ በአገልጋዮቻቸው ምክንያት ተለያይተው ለመኖር ሲወስኑ ሎጥ የሰዶምን ከተማ በመምረጥ ኑሮውን መሥርቶ ነበር፡፡ (ዘፍ ፲፫)፡፡ በሰዶምና በገሞራ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ግን በዝሙት ሥራ የታወቁ ነበሩ፡፡ ከተፈጥሮ ሥርዐት ውጭ በሆነ መንገድ ወንድ ከወንድ ጋር በመገናኘት ከዝሙት የከፋ ተግባርን ስለሚያከናውኑ ለግብረ ሰዶም ስያሜ መነሻ ሆኑ፡፡ በረከሰ ሥራቸው ምክንያት እግዚአብሔር በዲን እሳት አጥፍቷቸዋል፡፡ (ዘፍ. ፲፰፥፳ ፤ ፲፱፥፳፬)

   ግብረ ሰዶም ሲባል የቃሉ ትርጓሜ እንደሚነግረን የሰዶም ሰዎች የሥራ ውጤት ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በ፩ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ምዕ. ፮ ቁጥር ፱ ላይ ግብረ ሰዶማውያንን ቀላጮች እያለ ይጠራቸዋል፡፡ ወንድ አገረድ፣ ለጾታው የማይገባውን ዝሙትን ለመፈጸም እንደ ሴት ሆኖ ከወንድ ዘርን ሲቀበል፤ እንዲሁም ሴት ከወንዳወንድ ሴት ጋር ዝሙትን ስትፈጽም ቀላጭ ትባላለች፡፡ በእንግሊዝኛው ቋንቋ ወንድና ሴት ግብረ ሰዶማውያን የተለያየ ስያሜ አላቸው፡፡ ወንድ ግብረ ሰዶማውያን GAY የሚባሉ ሲሆን ሴት ግብረ ሰዶማውያን ደግሞ LESBIAN ተብለው ይጠራሉ፡፡

   በብሉይ ኪዳን ዘመን በአሕዛብ ዘንድ በጣዖት የአምልኮ ሥርዐት ውስጥ ልቅ ዝሙትና ሰዶማዊ ግብረ አምልኮ ይፈጸም ነበር፡፡ በሙሴ ሕግ መሠረት ይህን የረከሰ ተግባር የሚፈጽሙ ሁሉ ይገደሉ ነበር፡፡ (ዘሌ. ፳፥፲፫)፡፡ ምክንያቱም ወንድ ከወንድ (ተባዕት አምሣያ ፈቃደ ሥጋ) ሴትም ከሴት ጋር (አንስት አምሣያ ፈቃደ ሥጋ) የሚፈጽም ማንኛውም ዓይነት ሩካቤ ሥጋ አጸያፊ በመሆኑ ነው፡፡ (ዘዳ. ፳፫፥፲፯፣ ፩ኛ ነገ. ፲፬፥ ፳፬፤ ፲፭፥፲፪፣ ፳፪፥፵፮)

   ግብረ ሰዶማዊነት የተጠቀሰውን ዓይነት ቅጣት ቢያስከትልም ሰዎች ግን ከድርጊቱ ሳይቆጠቡ ዛሬ ድረስ እየፈጸሙት ይገኛሉ፡፡ ነውርነቱ እንደመልካም ግብር ተቆጥሮ በዐራቱም መአዝነ ዓለም እየተተገበረ ነው፡፡ በተለይ ምዕራባውያንና አሜሪካውያን እየደገፉት መምጣታቸው በመአዝነ ዓለም ለመስፋፋት ምቹ አጋጣሚ ሆኖል፡፡ እነዚህ ሀገራት ከ1980 አጋማሽ ጀምረው በምሥጢርና በድብቅ መፈጸሙን ትተው በሥልጣኔ ሰበብ ወደ አደባባይ አውጥተውታል፡፡ ከራሳቸው ሀገር አልፈው በሌሎች ሀገራት ላይ ጫና በማሳደር ግብረ ሰዶም እንዲስፋፋም እየጣሩ ነው፡፡

   ለምሳሌ፡- አሜሪካ ለሌሎች ተቋማትም ሆነ ሀገራት በምትሰጠው ርዳታ ውስጥ ለግብረ ሰዶማውያን የሚደረገውን መብት ግምት ውስጥ አስገብታለች፡፡ ከሰው ልጆች የመብት ጥያቄዎች እንደ አንዱ ቆጥራዋለች፡፡ “Same have suggested that gay rights and human rights are separate and distinct,” Mrs, Clinton Said at the united Nations Human rights councils in Geneva, “but in fact they are one and the same” (www.nytimes.com)

   ብዙ ሀገራት ግን ግብረ ሰዶምን በመቃወም እያወገዙት ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ሀገረ እግዚአብሔር እንደመሆኗ መጠን ግብረ ሰዶም ኃጢአት መሆኑን በሃይማኖት አባቶች በኩል እየሰበከች ነው፡፡ ህዝቦቿም በከፍተኛ ሁኔታ ግብረ ሰዶምን ይቃወማሉ፡፡ መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው “Pew Research Center” እ.አ.ኤ በ2007 በሰበሰበው ዓለም አቀፍ የአመለካከት ቅኝት /Global Attitudes Survey/ 97 በመቶ ኢትዮጵያውያን ግብረ ሰዶምን እንደሚቃወሙ ነው፡፡ (http://www.pewglobal.org) በአንጻሩ ግብረ ሰዶምን ለማስፋፋት የሚሯሯጡ ጥቂት አካላትም ቢሆኑ በሀገራችን ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡

   በሀገራቸን ኢትዮጵያ ግብረ ሰዶም ለማስፋፋት ላይ ታች በማለት ከሚደክሙት መካከል ከውጭ ሀገር የሚመጡ የውጭ ዜጎችና ለረዥም ዓመታት በውጭ ሀገር ኖረው ይህን ተግባር የተለማመዱ ሰዎች ይጠቀሳሉ፡፡ እንደሌላው ሀገር በአደባባይ “I am a Gay” ብለው የሚፎክሩ ባይኖሩም በስብሰባ አዳራሽ ግን መታየት ጀምረዋል፡፡ ራሳቸውን ደብቀው ውስጥ ውስጡን መስፋፋታቸው የዐደባባይ ምሥጢር ሆኗል፡፡ በውጭ ሀገር የሚገኙ ግብረ ሰዶማውያን በሀገራችን የሚገኙ ጥቂት ግብረ ሰዶማውያንን ለ”መብታቸው” ሰልፍ እንዲወጡና በሕግ እዲፈቀድ እየቀሰቀሱ ይገኛሉ፡፡ የትምህርት ተቋማትንም ከመዳረሻቸው እንደ አንዱ አድርገዋቸዋል፡፡

   በትምህርት ቤቶች ወጣቶችን በማለማመድና በመመልመል ግብረ ሰዶምን ለማስፋፋት የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡ (ግብረ ሰዶማዊነት በዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ ገጽ ፵፰) እኒህ ሰዎች ለክፉ ለሥራቸው ይረዳቸው ዘንድ የመገናኛ መሥመር ዘርግተው ትውልዱን በረከሰው ተግባራቸው እየበረዙት ይገኛሉ፡፡

   ይህ የሚያሳየው ዓለማችን የሰዶምን ሥራ ከምንጊዜውም በላይ ለመቀበል የተዘጋጀች መሆኗንና ሥነ ምግባር እየመነመነ መምጣቱን ነው፡፡ ጸሐፍት እንደሚናገሩት በሐሳዌ መሢህ ዘመን ከሚፈጸሙ ሰባት ዋና ዋና ኃጢአቶች መካከል ግብረ ሰዶም አንዱ እንደሆነ ነው፡፡ (ኆኅተ ሃይማኖት ከመምህር ብርሃኑ ጎበና ገጽ ፻፲፪)

   የግብረ ሰዶምና የዓለማችን አነዋወር እንዲህ ከሆነ፤ ይህን ሰይጣናዊ ግብር ወይም የኃጢአቶች ሁሉ አውራ የሆነውን ግብረ ሰዶም ለመከላከል ወይም እንዳይስፋፋ ለማድረግ ከኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችና ከግቢ ጉባኤያት ማከናወን የሚጠበቁ ተግባራትን እንመልከት፡፡ ተማሪዎች፡-

   ፩. የክፉ መንፈስ ውጤት እንደሆነ መረዳት

   ግብረ ሰዶማውያን ድርጊቱን “የሥነ ፍጥረት ልዩ መገለጫ ነው” በማለት ለመስበክ ይሞክራሉ፡፡ “የሥነ ፍጥረት ልዩ መገለጫን” ለማጎልበት ግብረ ሰዶማዊ እንዲሆኑ ተደርገው እንደተወለዱ ይናገራሉ፡፡ ባሕርያቸው ወይም ዘረመል ለግብረ ሰዶም የተመቸ እንደሆነም አሳብ ይሰጣሉ፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ የተሳሳተ አሳብ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥር በዚህ ሒደት ውስጥ እንዲያልፉ አድርጎ አይደለምና፡፡ (ዘፍ ፪፥፳፯)፡፡ ግብረ ሰዶማዊነት የተፈጥሮ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ባልፈጠረ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ወንድን ለሴት፣ ሴትን ለወንድ ፈጠረ፡፡ በዚህም ሰዎች ከዝሙት ሥራ ይጠበቁበታል፡፡ (፩ኛ ቆሮ ፯፥፪)፡፡

   እግዚአብሔር በተመሳሳይ ጾታ መካከል ተፈጥሮአዊ መሳሳብን አላኖረም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ ለአዳም የምትመቸውን ረዳት ሆና ሔዋን ባልተፈጠረች፤ ሌሎች ፍጥረታት በሙሉ ወንድና ሴት ባልሆኑ ነበር፡፡ ይህ የተቀደሰ የእግዚአብሔር ሥራ ይከናወን ዘንድ አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር መገናኘት አለባቸው፡፡ የትዳር ዓላማዎችም ዘር ለመተካት፣ ለመረዳዳትና ከዝሙት ለመጠበቅ ስለሆነ ግብረ ሰዶም በተመሳሳይ ጾታ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡

   አንድም ሰው በባሕሪው ግብረ ሰዶማዊ ሆኖ ተፈጠረ ልንለው አንችልም፡፡ ይልቁንም በብርቱ የኀጢአት ልምምድ የተከሰተ ነው፡፡ ተግባሩ ቀስ በቀስ ወይም በመለማመድ ሰውን የሚጸናወት የክፉ መንፈስ ውጤት እንጂ ተፈጥሯአዊ ጉዳይ አይደለም፡፡ “ሳይንስ፡- የግብረ ሰዶማዊነት ስሜትና ባሕርይ መነሻ የማኅበራዊ ሕይወትና የአካባቢ ተፅዕኖ ውጤት ወይም አዲስ ነገር ለማድረግ የሚሹ ሰዎች ልምምድ እንጂ በፍፁም ተፈጥሮ ወይም በጅን (በዘረመል) ውስጥ ያለ ነገር አይደለም ይላል” (ግብረ ሰዶማዊነት በዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ ገጽ ፳፮)፡፡ ይህ ሰዎች ከመንፈሳዊ ተግባር በራቁ ቁጥር ወደዚህ ክፉ ድርጊት የሚመራ ክፉ መንፈስ ያገኛቸዋል፡፡ ስለሆነም ተማሪዎች ሁል ጊዜ ራሳቸውን ከተቀደሰው ከእግዚአብሔር ቤት ማኖር ይጠበቅባቸዋል፡፡

   ፪. የጤና ጠንቅ መሆኑን መገንዘብ

   ግብረ ሰዶማውያን ወፈፌነት፣ ስሜታዊነት፣ ባይተዋርነት፣ ያጠቃቸዋል፤ አእምሮታዊና አካላዊ ጤናቸው ይቃወሳል፡፡ ለዚህ ነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሊቃውንት ጉባኤ “ከሰዶማውያን ርኩሰት ተጠበቁ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው መጸሐፍ “አእምሮታዊው እብደት ሲሆን አካላዊው በሽታ ደግሞ ኤድስ፤ የፊንጢጣና የአንጀት መቁሰል እንደሆነ የሕክምና ባለሞያዎች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው” በማለት ለይቶ ያስቀመጠው፡፡ (ከሰዶማውያን ርኩሰት ተጠበቁ ገጽ ፵፩)
  በግብረ ሰዶማዊነት ምክንያት ሰዶማውያን በሆኑ ሰዎች ላይ ስለሚከሰቱ በሽታዎች ደግሞ በመለከት መጽሔት የተዘረዘሩት እንዲህ ይነበባሉ፡፡ “፩. የፊጢጣ ነቀርሳ (ካንሰር)፣ ፪. የአንጀት ነቀርሳ (ካንሰር)፣ ፫. ፌስቱላ፣ ፬. ኪንታሮት፣ ፭. የጡት ነቀርሳ (ካንሰር)፣ ፮. የጉሮሮ ቂጥኝ፣ ፯. የፊንጢጣ ቂጢኝ፣ ፰. መኻንነት፣ ፱. ኤች.አይ.ቪ ኤድስና ራስን ማጥፋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

   ከላይ ከተጠቀሱት ሌላ ግብረ ሰዶማውያን ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል የዘር ሐረግ መቋረጥ (ስለማይወልዱ) የዕድሜ ማጠር (ግብረ ሰዶማዊነት ከ፲ እስከ ፴ ዕድሜ ይቀንሳል) ይህ ግብር በተፈጥሮ ከተፈቀደው ሥርዓት ውጭ የሚፈጸም በመሆኑ መቀመጫቸው (ፊንጢጣቸው) የላላ ነው፤ በዚህም ምክንያት ሰገራቸውን መቆጣጠር አይቻላቸውም፡፡ ለዚህም መከላከያ እንዲሆናቸው በማሰብ እንደ ሕፃን ልጅ በየሰዓቱ የሚቀያየር ዳይፐር (ላስቲክ) ለመጠቀም ይገደዳሉ” (መለከት መጽሔት ፳ኛ ዓመት ቁጥር ፪ ገጽ ፳፱)

   ከተመለከትናቸው በሽታዎች በተጨማሪ ይህን ተግባር ልምድ ያደረጉ ሰዎች ወደ ቅዱስ ጋብቻ አይገቡም፡፡ ወደ ትዳር ሕይወት ቢገቡ እንኳ ያለፈ ሕይወታቸው ቤተሰባዊ ሕይወታቸው ላይ ጭንቀት ይፈጥርባቸዋል፡፡ ዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ በበኩሉ “My Genes Made Me Do It” በሚል ርእስ ኤን ኢ ዋይት ሄድ በተባሉ ተመራማሪ ከተዘጋጀ መጽሐፍ ጠቅሶ፣ ግብረ ሰዶም ስለሚያስከትለው የማኅበራዊ ቀውስ ሲያትት “ራስን የማጥፋት፣ ግራ የመጋባት፣ የባሕርይ ተለዋዋጭነት፣ ማኅበራዊ ሕይወትን የመፃረርና የመሳሰሉት ብዙ ችግሮች በግብረ ሰዶማውያን ዘንድ እንዳሉ እናያለን” ብሏል፡፡ (ግብረ ሰዶማዊነት በዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ ገጽ ፲፱)

   አባቶቻችንም ሰዎች በክፉ ሥራቸው ጤናቸውን እንደሚያጡ ይናገራሉ፡፡ “በአሁኑ ጊዜ ጌታ እግዚአብሔር ኤድስን በሚያህል ክፉ ደዌ ዓለምን እያስጠነቀቀ ነው፡፡ ማስጠንቀቂያውም ሥጋቸውን ግብረ ሰዶማዊነትን ለመሰለ ለርኩሰት ለሰጡ ወጎኖች ነው” (ግብረ ሰዶማዊነት እና የሴቶች ክህነት በቤተ ክርስቲያን ዕይታ ገጽ ፲፪)፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኤች.አይ.ቪ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች መካከል በተቃራኒ ጾታዎች ፳፯ % በሚደረግ ወሲብ ሲሆን ፷፩ % ግን በግብረ ሰዶማውያን ነው፡፡ (መለከት መጽሔት ፳ኛ ዓመት ቁጥር ፪ ገጽ ፳፱) ግብረ ሰዶማውያን በሱሶች የተያዙ ናቸው፡፡ በሱሶች የተያዙ ሰዎች ደግሞ በአብዛኛው ለትምህርት ያላቸው ፍላጎት እምብዛም ነው፣ በትምህርት ገበታቸውም ፍሬ አልባ ናቸው፡፡

   ፫. ራስን ከኅቡዕ ድርጅት መጠበቅ

   ግብረ ሰዶማውያን በሚፈጽሙት ድርጊታቸው ለየት ያለ ጠባይ ይታይባቸዋል፡፡ በአለባበሳቸው ሁል ጊዜ ቁምጣ ሱሪ ማዘውተር፣ “ስኪኒ” በመባል የሚጠራውን ጠባብ ሱሪ እና እምብርታቸውን የሚያሳዩ “ቦዲ ቲሸርት” መልበስ፣ ጫማ ያለ ካልሲ ማድረግ፣ ጆሯቸውን በተለያየ ቦታ በመበሳት ጌጣ ጌጥ ማስገባት፣ ሎቲ ማንጠልጠልን ያዘወትራሉ፡፡

   ይህ በግልጽ የሚታየው አካሄዳቸው ሲሆን በግልጽ ሊሄዱባቸው የሚችሉባቸው መንገዶች የተዘጉ ከመሰሏቸው ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም ሰውን ወደ እነርሱ ማኅበር ሊስቡ ይሞክራሉ፡፡ በኢንተርኔት፣ በፌስ ቡክ፣ ውስጥ ለውስጥ በሚደራጁ ቡድኖችና በውጭ ሀገራት የእነርሱ አባል በመሆን በሚገኝ ጥገኝነትና የውጭ ሀገር ዕድሎችን ማመቻቸት፣ ሆነ ተብሎ ግብረ ሰዶምን ለማስፋፋት የሚዘጋጁና በከፍተኛ ሁኔታ ባህልንና ሥነ ልቡናን የሚጎዱ ፊልሞችን፣ ዘፈኖችን፣ የኅትመት ውጤቶችን አዘጋጅቶ ተግባራቸውን ማስፋፋት ተጠቃሽ መንገዶች ናቸው፡፡ በዚህ መንገድ የምናደርጋቸው ግንኙነቶችን ቆም ብሎ መመርመር ተገቢ ነው፡፡

   ሌላው ሰውን ወደ እነርሱ ማኅበር አስገድደው በመድፈር ወይም በመደለል ይቀላቅላሉ፡፡ አንዳንዶች ባለማወቅ በእነዚህ ሰዎች የተደፈሩበት አጋጣሚዎች መኖራቸውን ጠቋሚዎች አልጠፉም፡፡ በተለይ ሕፃናትን በመደለል የጥቃታቸው ሰለባ አድርጎቸዋል፡፡ ወጣቶችንም ቢሆን በግዳጃ ከመድፈር አልተመለሱም፡፡ “… የተለያዩ ጥናቶች እንዳመለከቱት በዚህ ሕይወት ያሉ ብዙዎች በልጅነታቸው በተለያዩ ግለሰቦች ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ አንዳንዶች ከቅርብ ዘመድ ጥቃቱ ሲደርስባቸው ሌሎች በጎረቤት፣ በጓደኞች ወ.ዘ.ተ ተጠቅተዋል፡፡ ወንድ ልጅ በግብረ ሰዶማዊ ከተደፈረ ብዙውን ጊዜ ሰዶማዊ የመሆን አዝማሚያው ከፍ ያለ ነው፡፡ እርሱ እንደተጠቃ ሌሎችን ለማጥቃት ይፈልጋል፡፡ … እንዲሁም ሴት ልጅ በለጋነት ዕድሜዋ በወንድ ከተደፈረች ድርጊቱ በጣም ስለሚጎዳት የወንድን ወሲባዊ ስሜት ማርኪያ መንገድ ይጠፋባታል፡፡ ስለዚህ እንደ አማራጭ ተመሳሳይ ፆታ ወዳላት ሴት ጋር ትሄዳለች፡፡ ከዚህ የተነሣ ግብረ ሰዶማዊ ልምድ ታዳብራለች” (ግብረ ሰዶማዊነት በዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ ገጽ ፳፩)

   ዛሬ ዛሬ በመዝናኛ ቦታዎች እነዚህ አካላት ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ የጨለማ ሥራቸው እስኪገለጥ ድረስ ራሳቸውን እንደጥሩ ሰው በማቅረብ እና ወጣቶችን በመተዋወቅ የጨለማ ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡ በመሆኑም ውሎንና ጓደኛን በትኩረት መመርመር መለየት ከሚገባበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡

   ፬. በቅዱሳት መጻሕፍት ስም እንዳያስቱን መጠንቀቅ

   “ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” እንዲሉ ግብረ ሰዶማውያን ደጋፊ ሲያጡ ተግባራቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ለማስደገፍ ይሞክራሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ሰዎችም ጋር ለማስተሳሰር ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ “ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበረ፤ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ” (፪ኛ ሳሙ. ፩፥፳፮) በማለት ንጉሥ ዳዊት ስለዮናታን የተናገረውን የሙሾ ቃል በመውሰድ ግብረ ሰዶማዊነት የተፈቀደ ተግባር እንደሆነ አድርገው ያወራሉ፡፡ በእነሱ አተያይ ተግባራቸው ሰውን የመውደድ ምልክት ነው፡፡

   ቅዱስ ዳዊት “ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ” ሲል ከዮናታን ጋር ስለነበረው ጥብቅ መተሳሰርና የወዳጅነት ፍቅር ለመግለጽ ነው እንጂ የክፉ ሥራ ተባባሪ ሆኖ አይደለም፡፡ ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር እንደልቤ የሆነ በማለት የተናገረለት ሰው ነው፡፡ በእግዚብሔር ዘንድ ሞገስ ያለው ሰው ነው፡፡ ሴቶችን አግብቶ ልጆችን እንደወለደ፤ ዮናታንም ልጅ እንደነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ (፩ኛ ሳሙ. ፳፭፥፵፫፣ ፪ኛ ሳሙ ፱፥፩)

   በመሆኑም ግብረ ሰዶማዊያን ቅዱስ ጴጥሮስ “በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።” (፪ኛ ጴጥ. ፫፥፲፮) እንዳለ ሰውን ለማሳት የመጻሕፍት ቃል ለመጥቀስ ይሞክራሉ፡፡ ግብረ ሰዶማዊነት በሥጋ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ እንጂ የፍቅር መገለጫ አይደለም፡፡ በሥጋ ፍላጎት እና በፍቅር መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ ለግብረ ሰዶም ፍቅር የሚለው ቃል ፈጽሞ አይስማማውም፡፡ ሰው የሚወድ ሰው እንዴት ወንድሙን በረከሰ ተግባር ያጠፋዋል? ለዘለዓለም ቅጣትስ እንዴት ይዳርገዋል? ምክንያቱም የሰዶም ሥራ ለሰዶማውያን አልጠቀመምና፡፡

   ግብረ ሰዶም የሰዶምንና የገሞራን ሰዎች በዲን እሳት አጥፍቶ ዕፀዋትና እንስሳት የማይኖሩበት፣ ዓሦች የማይርመሰመሱበትን የጨው ባሕርን የፈጠረ የኀጢአት ውጤት ነው፡፡ ይህ ባሕር እስከዛሬ ድረስ ለሰው ልጆች የማስተማሪያ ምልክት ይሆን ዘንድ በውስጡ ሕይወት ያለው ነገር እንኳ አይታይበትም፡፡ በዓለም ካርታ ላይም “የሙት ባሕር” የሚል መጠሪያ ተሰጥቷታል፡፡ ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች በሰዶምና ገሞራ ከደረሰው ጥፋት ውጭ የሚያተርፉት አንዳች ነገር የለም፡፡

   በረከሰ ተግባር የሚኖሩ ሰዎች የረከሰውን ተግባራቸውን ካልተው በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገቡም፡፡ አመንዝሮችና ሰዶማውያን ከእግዚአብሔር መንግሥት ዕድል ፈንታ የላቸውም፡፡ በሐዲስ ኪዳን በሰዶማውያን ላይ እንደ ብሉይ ኪዳን የሥጋ ሞት ቅጣት ባይበየንም፣ በአፀደ ነፍስ ግን ዘለዓለማዊ ሞት እንደሚጠብቃቸው ተጽፏል፡፡ (ዘሌ. ፳፥፲፫፣ ፩ኛ ቆሮ. ፮፥፱) የቤተ ክርስቲያን ቀኖና በበኩሉ ወደዚህ ተግባር በገቡ ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ያዛል፡፡ “ግብረ ሰዶም የሚሠሩ ሰዎች ለአድራጊውና ለተደራጊው ቅጣት ሰይፍ ነው፡፡ ተደራጊው ከዐሥራ ሁለት ዓመት ያልሞላው ቢሆን የዘመኑ ማነስ ከቅጣት ያድነዋል” (ፍትሐ ነገሥት አን. ፵፰)፡፡ በመሆኑም ለሰዶማውያን ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ወይም መብት ሕይወታቸውን ወደ ንስሓ መመለስ ነው፡፡ “ሰዶማውያንና ሰዶማውያት ሁሉ ከዚህ አስነዋሪና አስጸያፊ ተግባር በንስሓ እንዲመለሱና ከአእምሮዊና አካላዊ በሽታ እንዲፈወሱ፣ ከርኩሰታቸው እንዲቀደሱ ቤተ ክርስቲያን ትመክራለች፤ የማይመለሱትንና እንቢተኞችን ግን በጽኑዕ ታወግዛለች፣ ከአንድነትዋም ትለያለች” (ከሰዶማውያን ርኩሰት ተጠበቁ ገጽ ፵፩)

   ምእመናን ግብረ ሰዶም አስከፊ ተግባር መሆኑን አውቀው ለሁሉም በመምከርና በማስተማር፣ የችግሩ ተጠቂም እንዳይሆኑና የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባቸዋል፡፡ ይህን ችግር ከመቅረፍ አንጻር ለተማሪዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን በመመልከት ማሳሰብ፣ በጤና ላይ የሚያስከትለውን ችግር፣ ባህልንና ማኅበራዊ ሕይወትን እንደሚጎዳ ማስተማር፣ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት የችግሩን አሳሳቢነት ማስረዳት፤ በተግባሩ የተጠቁትን ደግሞ በቶሎ ወደ ንስሓ እንዲመጡ መርዳት ግብረ ሰዶም እንዳይስፋፋ ያግዛል፡፡
  በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንመለከተው በሕገ እግዚአብሔር ከመኖራቸው በፊት አመንዝሮች የነበሩ፡፡ ኋላም በንስሓ ተመልሰው ለክብር የበቁ ብዙ ቅዱሳን አሉ፡፡ ስለዚህ የሰው ልጆች ሁሉ በንስሓ ሕይወታቸውን ማስተካከል እንደሚችሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጥቀስ ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

   በእርግጥ ሰዎች በኀጢአት ወጥመድ ሲያዙ ጸጋ እግዚአብሔር ስለሚርቃቸውና ኅሊናቸው ስለሚቆሽሽባቸው ድርጊቶቻቸውን ለመመዘን ይከብደቸዋል፡፡ ኀጢአቱ ጽድቅ፣ ጽድቁ ኀጢአት ይሆንባቸዋል፡፡ በመሆኑም ተመለሱ ሲባሉ እንደ ሰዶምና ገሞራ የማይገነዘቡ ይሆናሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ሕይወታቸውን የሚያስተካክሉበትን መንገድ በነቀፌታ ሳይሆን ርኅራኄ በማሳየት ማስገንዘብ ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
  ሓላፊነት የሚሰማቸው ሁሉ ሲመክሩና ሲያሰስተምሩ ለራሳቸው መጠንቀቅና አደገኛነቱን ግምት ውስጥ ማስገባት ተቀዳሚነት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ አስቀድሞ ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሌሎችን ለመታደግ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የችግሩ ሰለባ መሆን የለባቸውምና፡፡

   በአጠቃላይ የሰው ልጅ ክብሩ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ በመሆን የሚገለጽ ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሔር ትእዛዘ ሲያከብር በቅድስና ይኖራል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ክርስቲያን ሰውነቱ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነውና፡፡ (፩ኛ ቆሮ ፮፥፲፱)፡፡ ነገር ግን በርኩስ ሥራ ሰውነታችንን ስናሳድፈው መንፈሰ እግዚአብሔር ይርቀናል፡፡ ከእግዚአብሔር መንግሥትም እንለያለን፡፡ ከእግዚአብሔር መንግሥት ከሚለዩ የክፋት ሥራዎች አንዱና ዋነኛው ግብረ ሰዶም ነው፡፡ በመሆኑም ግብረ ሰዶም እንዳይስፋፋና ሀገረ እግዚአብሔር የሆነችውን ሀገራችንን እንዳይበክል የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንናበርክት፡፡

   ክቡራን አንባብያን ስለ ግብረ ሰዶም ምን ትላላችሁ? ከእያንዳንዱ ሰው የሚጠበቀው ተግባርና ኃላፊነት ምን ይሁን? ጥያቄ አስተያየት ካላችሁ www Eotc mk.org ላኩልን እናስተናግዳለን፡

  ምንጭ ጉባኤ ቃና 2006 ዓ.ም.

  Read more »

RSS