{$lang.login}{$lang.site_name}
Welcome
Login / Register

Most popular


 • የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል/መዝ. 33÷7/

  ታኅሣሥ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. 

  አባ ሳሙኤል

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

  የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን
  ሊቀ ጳጳስ

  st michael13እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ቸርነቱን የሚገልጠው በመላእክት ተራዳኢነት ለሰው ልጅ በሚፈጽመው የማዳን ተግባር ነው፡፡ መላእክት የሚያገለግሉት በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ መሠረት መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል፣ እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱት፤ እወቁም (መዝ. 33÷7-11) በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደጠቀሰው ጥልቅ መልእክት እንዳለው እንረዳለን፡፡ ከታሪክ እንደምንረዳውም እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ቸርነት ቀምሰው ያወቁት በጭንቀታቸው ጊዜ መልአኩን ልኮ በፈጸመላቸው የማዳን ተግባር ነው፡፡


  መላእክት አገልግሎታቸው ብዙ ነው፡፡ መንፈሱ የተራቆተውን፣ በችግር ላይ የወደቀውን፣ በፍርሀት የተዋጠውንና ተስፋ የቆረጠውን አጽናንተዋል፣ ከክፉ ነገር ሁሉ ጠብቀዋል፡፡ በትንቢተ ዘካርያስ ምእራፍ 3÷4 ላይ “እነሆ በደልህን አስወግጄልሀለሁ አዲስ የክብር ልብስም አለብስሃለሁ” ተብሎ የተገለጸውን ማገናዘብና መረዳት ያስፈልጋል፣ ቃሉም ቃለ መልአክ እንደሆነ ተገልጿል፡፡


  መላእክት የእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ ጠብቆ ለሚማጸንባቸው ሁሉ ፈጥነው የሚደርሱና የሰውንም ወገን በማንኛውም መንገድ የሚራዱ መሆናቸው ቢታወቅም የመላእክትን እርዳታ ለማግኘት በቅድሚያ ራስን በእምነት ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ የመላእክት ተራዳኢነትን በብሉያትም ሆነ በሐዲሳት የምንረዳበት መንገድ ብዙ ቢሆንም ለግንዛቤ ያህል፡-st.rufael


  ሀ. አጋር ከሣራ በደረሰባት ግፍና በደል ምክንያት ከቤት ወጥታ በበረሃ በችግር ላይ ሳለች የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አጋር ቀርቦ እንዳጽናናትና እንዳገለገላት በዘፍ. 16÷1-16 ላይ ዝርዝር ታሪኩ ተገልጿል፡፡


  ለ. ሕዝበ እስራኤልን ወደ ምድረ ርስት በመምራት ላይ የነበረው ኢያሱ በእግዚአብሔር መልአክ እየተረዳ ጠላቶቹን ድል አድርጓል፤ ሊደረግ የሚገባውንም መልአኩ እየነገረው ይሠራ እንደነበረ በመጽሐፈ ኢያሱ 5÷13-35 ላይ ታሪኩ ተጽፏል፡፡


  ሐ. መላእክት ለመዓትም ለምሕረትም ይላካሉ፡፡ (ሮሜ 9÷22-23) በየዋህነት፣ በቅንነት፣ የሚሠሩትን፣ በእግዚአብሔር የሚያምኑትን ይረዳሉ፡፡ ከልዩ ሥቃይ ይታደጋሉ፣ በአንጻሩም በትዕቢትና በጠማምነት የሚኖሩትን፣ ለእግዚአብሔርና ለሕጉ የማይታዘዙትን ለመቅጣት ይታዘዛሉ፡፡ ለምሳሌ ሕዝበ እስራኤል ከጭቆና አገዛዝ ከግብጽ ሲወጡ ቀን በደመና፣ ሌሊት በእሳት ብርሃን እየመራ የመገባቸው፣ ባሕር ከፍሎ ያሻገራቸው የእግዚአብሔር መልአክ ነው፡፡ ለእስራኤላውያን መልአከ ምሕረት ሆኖ ባሕርን ከፍሎ ያሻገረ፤ ለግብጻውያን ደግሞ መልአከ መዓት በመሆን ስጥመት እንዲፈጸም ያደረገው መልአከ እግዚአብሔር ነው፡፡ (ዘጸ.14÷15-25)


  መ. ለሰናክሬምና ሠራዊቱ መልአከ መዓት፣ ለሕዝቅያስና ለወገኖቹ መልአከ ምሕረት ሆኖ የሕዝቅያስን እምነት፣ የሰናክሬምን ትዕቢት ተመልክቶ ተገቢውን ግዳጅ የፈጸመ መልአከ እግዚአብሔር እንደሆነ በ2 ነገሥ. 19÷35 ላይ ተመዝግቧል፡፡
  ሠ. ከእቶነ እሳት ጒድጓድ ተጥለው የነበሩትን ሦስት ወጣቶች ከሞት የታደገ መልአክ እግዚአብሔር ነው፣ (ዳን.3÷1-25)


  ረ. አናብስት ከሚጠበቁበት ሥፍራ በግፍ ተጥሎ የነበረውን ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤልን ከአፈ አናብስት የታደገ መልአከ እግዚአብሔር ነው፡፡ (ዳን. 6÷13-22) “በመንገድህ ሁሉ እንዲጠብቁህ እግዚአብሔር መላእክቱን ያዝዛል” (መዝ. 90÷1-22) እንዲል፡፡ እንዲሁም “ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ” ሲል የቅዱስ ሚካኤልን ተራዳኢነት ይገልጣል (ዳን. 10÷13)፡፡


  ሰ. እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ ፈርዖን ሲያሳድዳቸው እግዚአብሔር የሕዝቡን ችግር ተመልክቶ “በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወደ አዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ በፊትህ መልአክን እሰድልሀለሁ” ሲል ለሙሴ ቃል እንደገባለትና በኋላም በዚህ ቃል ኪዳኑ መሠረት የተላከው የእግዚአብሔር መልአክ በፊትና በኋላ እየሆነ ይመራቸውና ይጠብቃቸው እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል (ዘፀ.14÷19፤23÷20፤33÷2)፡፡


  ቤተ ክርስቲያን ስለ ተራዲኢነትና ጠባቂነት ለምእመናኖቿ የምታስተምረውም ይህንን የቅዱስ መጽሐፍ ቃል አብነት በማድረግ ነው፡፡ በዚህ ትምህርት መግቢያ ላይ የተጠቀሰው “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል” የሚለው ቃል የሚያመለክተውም የዚህ ትምህርት ትክክለኛነት ነው፡፡


  መላእክት በዕለተ እሁድ ከተፈጠሩ ፍጥረታት አንዱ ክፍል ናቸው፡፡ መላእክት አንድ ጊዜ የተፈጠሩ እና በየጊዜውም የማይባዙ ናቸው:: መላእክት በተፈጥሮአቸው ነባብያን፤ ለባውያን፣ ሕያዋን፣ ኃያላንም ናቸው፤ እንደ ደቂቀ አዳም ሕመምና ሞት የለባቸውም፡፡ የመላእክት ቁጥር በአኀዝ አይወሰንም የብዙ ብዙ ናቸው፤ መላእክት በነገድ አለቃ እና በከተማ ይከፋፈላሉ፤ በነገድ መቶ፤ በከተማ ዐሥር፡:

   
  ሀ. አገልግሎታቸው፡-
  st raguel 23ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር የቅርብ አገልጋዮች ናቸው፤ በዙፋኑ ዙሪያ ሆነው ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ እያሉ ዘወትር ያመሰግናሉ፡፡ በተልዕኮአቸውም ፈጣኖች ናቸው፤ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ለተልዕኮ ይወርዳሉ ይወጣሉ፤ የሰው ልጆችንም ይረዳሉ፡፡ (ራዕ.4÷9-11፤መዝ.103÷4፤ ዕብ.1÷4፤1÷14፤÷ዮሐ.1÷52)


  በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ለተልእኮ መፋጠናቸው፡-
  • የሰውን ጸሎት፤ ምጽዋትና መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ፣


  • የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት ወደ ሰዎች ማድረስ እንዲሁም ለቅጣት ይላካሉ፡፡ (ዳን.9÷20- 22፤ሉቃ. 1÷13፤ የሐዋ. 1÷3-5)


  • ሰዎች በሞቱ ጊዜ ነፍሳቸውን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ፡፡
  (ሉቃ. 13÷22፤ሱቱ. ዕዝ. 6÷6-20፤ ዳን. 4÷13፤ ሮሜ 9÷22)


  • በመከራና በችግር ጊዜ ለተራዳኢነት መላክ፣


  • በፍጻሜ ዘመን (ይህ ዓለም በሚያልፍበት ጊዜ) ከእግዚአብሔር ተልከው ኃጥአንን ከጻድቃን መለየት እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ቅዱሳን መላእክት በሰፊው ያስረዳል፡፡ (የሐዋ. 12÷7- 11፤ መዝ. 69÷7፤ ማቴ. 2÷31፤ ራእ. 7÷1-4)


  ለ. አማላጅነታቸው፡-
  የቅዱሳን መላእክት አማላጅነትና ተራዳኢነት፣ የሰዎችን ጸሎትና ምጽዋት ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ በተሰጣቸው ባለሟልነት ይፈጽማሉ፡፡ ከቅዱስ መጽሐፍ በሰፊው እንደምንረዳው የብዙዎችን ሰዎች ጸሎት መሥዋዕትና ምጽዋት ወደ እግዚአብሔር እያቀረቡ የሚፈልጉትን መልካም ነገር ሁሉ ያሰጣሉ፡፡ ማጽናናትና የምሥራች መንገርም ከእግዚብሔር የተሰጣቸው ልዩ ጸጋ ነው፡፡ (ዘፍ. 48÷16፤ ዳን÷16፤ ዳን.16÷10÷10-2፤ሉቃ. 1÷13፤ 10÷29-32፤ ይሁዳ.9) መመልከት ይቻላል፡፡


  የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ተጽፏል፣ በተለይም በመጽሐፈ ሄኖክ 10÷7 እና በትንቢተ ዘካርያስ 1÷12፤ በዘፀአ. 23÷20-23፤ መዝ.33÷7 የተቀመጡትን ጥቅሶች በግልጥ ያስረዳሉ፡፡ ቅዱሳን መላእክት ንስሓ ገብተው በተመለሱ ሰዎች ደስታ እንደሚያደርጉ በሉቃስ ወንጌል 15÷10 ላይ የተጻፈው ስለ ሰው ልጆች ደኅንነት ያላቸውን ፍቅርና አማላጅነት ያስገነዝባል፡፡


  ሐ. ክብራቸው፣
  st.ourael2ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ባለሟሎች ስለሆኑ ለአምላካቸው ቀናዕያን፣ ለነፍሳት ቀዋምያን ስለሆኑ፣ ለምሕረትም ለመዓትም ስለሚላኩ፣ ሰዎችን በችግራቸው ጊዜ ስለሚረዱና ስለሚያማልዱ ቤተ ክርስቲያን ታከብራቸዋለች፡፡ በስማቸው ጽላት ቀርጻ፣ ቤተ ክርስቲያን አሳንፃ፣ ድርሳናቸውን አጽፋ፣ እንዲመሰገኑ እንዲከብሩ ታደርጋለች፡፡ የጸጋና የአክብሮት ስግደትም ይሰገድላቸዋል፡፡ (ዳን.8÷15-18፤ ዘፍ. 22÷31 ዘኈ. 22÷31፤ኢያ.5÷13-15


  መላእክት ሰውን የሚራዱት በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ስለሆነ የመላእክት ተራዳኢነት የእግዚአብሔር ቸርነት መገለጫም ናቸው፡፡ ከቅዱሳት መጻሕፍት ቃል መረዳት እንደሚቻለው ዘካርያስና ኤልሳቤጥ በሐዲስ ኪዳን ዘመን መጀመሪያ ላይ የተነሡ የብሉይ ኪዳን ዘመን ባልና ሚስት ሲሆኑ ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፡፡ በእግዚአብሔር ሥርዐትና በትእዛዙም ሁሉ ያለ ነውር የሚሄዱ ነበሩ፡፡ ልጅም አልነበራቸውም፡፡ ዘመናቸውም ያለፈ ነበር፡፡ ዘካርያስ የዘመነ ኦሪት ሊቀ ካህናት እንደመሆኑ በቤተ መቅድስ በአገልግሎት ላይ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ታየው፡፡ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፡፡ ይህንንም እነግርህና አበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልኬአለሁ፡፡” (ሉቃ.1÷11-21) ሲል መልአኩ ተናገረው፡፡


  መልአኩም ለዘካርያስ የተገለጠው ልጅ እንደሚወልድ ለማብሠር ነበር፡፡ ዘካርያስ ግን ይህን ብሥራት የሰማው ከጥርጣሬ ጋር ነበር፡፡ ምክንያቱም እሱም ሆነ ሚስቱ ኤልሳቤጥ በዕድሜ የገፋችና የመውለጃ ጊዜያቸውም ያለፈ መሆኑን ስለሚያውቅ ነበር፡፡ ካሁኑ ዘካርያስ የተነገረውን ብሥራት በመጠራጠሩ የተነገረው ብሥራት እስከሚፈጸም ድረስ አንደበቱ እንደሚዘጋና መናገርም እንደማይችል ነገረው፡፡ ይህንም ያደረገው ለቅጣት ሳይሆን ለተነገረው ብሥራት እውነትነት ምልክት እንዲሆነው ለማድረግ ነበር፡፡


  በመልአኩ እንደ ተነገረውም ኤልሳቤጥ የመውለጃ ጊዜዋ ካለፈ በኋላ ፀነሰች፡፡ ወንድ ልጅም ወለደች፤ እሱም መጥምቁ ዮሐንስ ነበር፡፡ ዮሐንስም እንደ ተወለደ ዘካርያስ ተዘግቶ የነበረው አንደበቱ ተከፍቶ መናገር ጀመረ፡፡
  መጥምቁ ዮሐንስም አስቀድሞ በመልአኩ ቃል እንደተነገረው መንፈስ ቅዱስ የሞላበት የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥን ሁሉ የማይጠጣ ከእሰራኤል ብዙዎችን ወደ እግዚብሔር ወደ አምላካቸው የሚያቀረብ፤ የአባቶች ልብ ወደ ልጆች፤ የከሃድያንንም ሐሳብ ወደ ጻድቃን እውነት የሚመልስና ሕዝብንም ለእግዚአብሔር ማደሪያ የተዘጋጀ የሚያደርግ ካህን፤ ነቢይ፤ ሐዋርያና ሰማዕት ሆኖ ዓለምን ለማገልገል የበቃ የእግዚብሔር መልእክተኛ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት የመጀመሪያው የሐዲስ ኪዳን “ቅዱስ” ተባለ፡፡

   

  መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጣዖት አናመልክም በማለታቸው ምክንያት ወደ እቶነ እሳት የተጣሉትን ሦስት ወጣቶችን ማዳኑን በቅዱስ መጽሐፍ ከምናገኛቸው ታሪኮች አንዱ ነው፡፡ ሦስቱም ወጣቶች ወደ ባቢሎን ተማርከው ከተወሰዱት እስራኤላውያን መካከል የሚገኙ የእግዚአብሔር ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ አማንያን ወደ እሳት እንደተጣሉ የእግዚአብሔር መልአክ ከሦስቱ ሰዎች ጋር ወደሚነድደው የእሳት ምድጃ ወርዶ እሳቱን ስለመታው የእሳቱ ነበልባል እንደ ጠፋና ሦስቱም ሰዎች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከሚነድደው እሳት እንደወጡ፤ በዚህም ለእግዚአብሔር ጥልቅ ምስጋና እንዳቀረቡ በትንቢተ ዳንኤል ታሪካቸው በስፋት ተገልጧል (ዳን. 3÷26)፡፡ ይህም እግዚአብሔር በመላእክት ተራዳኢነት ለሰው ልጅ የሚያደርገውን ቸርነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም በታላቅ በዓል ታከብረዋለች፡፡


  “ከእናቴ ማኅፀን የመረጠኝና የለየኝ እግዚአብሔር በጸጋው ጠራኝ” (ገላ.1÷15-17) እንዲል ልዑል እግዚአብሔር ከማኅፀን ጀምሮ ለመልካም አገልግሎት ሰዎችን እንደሚመርጥና እንደሚያዘጋጅ በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በቅደም ተከተል ማየትና መመርመር እንዲሁም መረዳት ተገቢ ነው፡፡


  ለምሳሌ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን፡-
  ሀ. የማኑሄ ልጅ ሶምሶን በብሥራተ መልአክ እንደተፀነሰና ተወልዶ ካደገም በኋላ ምን ማድረግ እንዳለበት አስቀድሞ በልዑል እግዚአብሔር እንደታጨና እንደተመረጠ በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕራፍ 13 ከቁጥር 1-25 የተመዘገበውን፤


  ለ. ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ “ገና በእናትህ ማኅፀን እንድትፀነስ ከማድረጌ በፊት መርጬሃለሁ፤ ከመወለድህም በፊት አንተን በመለየት ለሕዝቦች ሁሉ ነቢይ አድርጌ ሾሜሃለሁ” ተብሎ እንደታጨና እንደተመረጠ በምዕራፍ 1÷4-5 የተመዘገበውን፤


  ሐ. መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በብሥራተ መልአክ “ዘካርያስ ሆይ! አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ የእርሱ መወለድ ለአንተ ተድላና ደስታ ይሆንልሃል፤ ብዙዎችም በመወለዱ ደስ ይላቸዋል (ሉቃ.1÷13-14) ተብሎ ተገልጿል፡፡


  መ. በጌታ እንደታጨና እንደተመረጠ ሁሉ ንዋይ ኅሩይ የተሰኘው ቅዱስ ጳውሎስም በመሪ ጥቅሱ እንደተገለጸው ”ከእናቴ ማኅፀን የመረጠኝና የለየኝ እግዚአብሔር በጸጋው ጠራኝ” ብሎ ምርጫውና ጥሪው ከእግዚአብሔር መሆኑን ያበሥራል፡፡


  “ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ስንኳ እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና፡፡” (ማቴ.18÷10-12) በማለት ጌታችንና መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሚያስተምርበት ወቅት ሕፃናትን ከትልልቆቹ ለይቶ አላያቸውም፡፡ በፍቅሩ ወደ እርሱ ያቀርባቸው ነበር፤ ወደ እርሱ እንዲመጡ እንዳይከለክሏቸው ደቀመዛሙርቱንም አዝዞአቸዋል፡፡ ከተአምራቱ አለያቸውም፤ በረከተ ኅብስት ተካፍለዋል፤ በአንብሮተ እድ ተባርከዋል፤ በዕለተ ሆሣዕና ዘምረዋል፤ ከሕፃናት መካከል አንዱን ሕፃን በክንዱ ታቅፎ “ተመልሳችሁ እንደዚህ ሕፃን ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት አትችሉም” በማለት የትሕትና፤ የፍቅር፤ የየዋህነትና የተመላሽነት ምሳሌ አድርጎአቸዋል፡፡


  የቅዱሳን መላእክት ዋና ተግባራቸው እግዚአብሔርን ማመስገንና ትእዛዙን መፈጸም በእርሱ የሚያምኑትንም ትንንሾቹንና ትልልቆቹን ሁሉ ማገልገል ነው፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- “መላእክት ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ያላቸውን ለማገዝ የሚላኩና የሚያገለግሉ መናፍስት አይደሉምን?” (ዕብ. 1÷14)


  st gabreilkirkosሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ክርስቲያኖች እየታደኑ በሚገደሉበት በዘመነ ሰማዕታት ቅዱስት ኢየሉጣ ከሕፃኑ ቂርቆስ ጋር በአንድ ዓላዊ መኰንን ፊት ቀርባ ስለ ክርስቶስ ተጠየቀች፡፡ እርስዋም “ይህን የሦስት ዓመት ሕፃን ጠይቀው እርሱ ይነግርሃል” አለችው፡፡ መኰንኑ ግን የሦስት ዓመት ሕፃን ምን ሊናገር ይችላል በማለት ናቀው፡፡ ይሁን እንጂ ሕፃኑ ቂርቆስ ስለ ክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት በርቱዕ አንደበት መሰከረ፡፡ የመኰንኑን ጣዖት ከንቱነትም በድፍረት ተናገረ፡፡ መኰንኑም ተቆጥቶ ሕፃኑንና እናቱን እንደ ክረምት ነጐድጓድ በሚጮህ እሳት ላይ በበርሜል በተጣደ የፈላ ውኃ ውስጥ እንዲጨምሩአቸው አዘዘ፡፡ ሕፃኑም “እናቴ ሆይ የእሳቱን ነበልባል አትፍሪ አትጠራጠሪ አናንያንና አዛርያን ሚሳኤልንም ያዳናቸው እርሱ ያድነናል በማለት ወደ እሳቱ እየመራ ይዟት ገባ፡፡ ያን ጊዜ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ የእሳቱን ነበልባል አጠፋው፤ ሕፃኑንና እናቱንም አዳናቸው፡፡


  “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸዋማል” እንደ ተባለ የእግዚአብሔር መልአክ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ሁልጊዜ ከመከራ ይጠብቃቸዋል፤ ይታደጋቸዋልም፡፡ (መዝ. 33÷7)


  አምላካችን እኛንም ከማንኛውም ፈተና ሁሉ ይጠብቀን አሜን፡፡

  Read more »

 • ምኩራብ(የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት)

  ምኩራብ(የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት) 

  የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

  ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠፆሙ ያርምሙ አንከሩ ምህሮቶ ሞገስ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዓ አፉሁ፡፡

  ትርጉም: ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው ፡፡ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል (እያለ የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፡)፡ ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።

  ምንባባት (መልዕክታት)

  (ቆላ. 2÷16-ፍጻ.) 
  እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና። አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ÷ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር፡፡ ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት÷ በሥርና በጅማትም በሚስማማበት÷ በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት በሚሞላበትም በራስ አይጸናም፡፡ ከዚህ ዓለም ኑሮ ከክርሰቶስ ጋር ከሞታችሁ እንደገና በዓለም እንደሚኖሩ ሰዎች እንዴት ትሠራላችሁ? እንዴትስ ይህን አትዳስስ÷ ይህን አትንካ÷ ይህንም አትቅመስ ይሉአችኋል? ይህ ሁሉ እንደ ሰው ትእዛዝና ትምህርት ለጥፋት ነውና፡፡ ይህም ስለ ልብ ትሕትናና እግዚአብሔርንም ስለ መፍራት÷ ለሥጋም ስለ አለማዘን ጥበብን ይመስላል፤ ነገር ግን ከሥጋ በላይ ነው እንጂ ምንም ክብር የለውም፡፡ 

  (ያዕ. 2÷14-ፍጻ.) 
  ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ÷ “በሰላም ሂዱ÷ እሳት ሙቁ÷ ትጠግባላችሁም” ቢላቸው÷ ለችግራቸውም የሚሹትን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡ነገር ግን አንድ ሰው÷ “አንተ እምነት አለህ÷ እኔም መልካም ሥራ አለኝ፤ እስቲ ሃይማኖትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ” ይላል፡፡ አንተም እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ ታምናለህ፤ መልካምም ታደርጋለህ፤ እንዲህስ አጋንንትም ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም፡፡ አንተ ሰነፍ ሰው÷ እምነት ያለ ምግባር የሞተች እንደ ሆነች ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ወደ መሠዊያው ባቀረበው ጊዜ÷ በሥራው የጸደቀ አይደለምን? እምነት ለሥራ ትረዳው እንደ ነበር÷ በሥራውም እምነቱ እንደ መላችና ፍጽምት እንደ ሆነችም ታያለህን? መጽሐፍ÷ “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት” የሚለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በሥራ እንደሚጸድቅ በእምነት ብቻም እንዳይደለ ታያለህን? እንዲሁ ዘማይቱ ረአብ ደግሞ ጒበኞችን ተቀብላ÷ በሌላ መንገድ ባወጣቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ÷ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡ 

  (የሐዋ.10÷1-8) 
  በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር፡፡ እርሱም ጻድቅና ከነቤተሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ÷ “ቆርኔሌዎስ ሆይ÷” አለው፡፡ ወደ እርሱም ተመልክቶ ፈራና÷ “አቤቱ÷ ምንድን ነው?” አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው÷ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል፡፡ አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ፡፡ እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት እንግድነት ተቀምጦአል፡፡ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡” ያነጋገረውም መልአክ ከሄደ በኋላ ከሎሌዎቹ ሁለት÷ ከማይለዩት ጭፍሮቹም አንድ ደግ ወታደር ጠራ፡፡ 

  ምስባክ 
  መዝ 68፡9
  እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
  ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
  ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡

  ትርጉም፦
  የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና
  የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና
  ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፡፡ 

  ወንጌል(ዮሐ. 2÷12-ፍጻ. ) 
  ከዚህም በኋላ እርሱና እናቱ÷ ወንድሞቹና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቅፍርናሆም ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ያይደለ ጥቂት ቀን ተቀመጡ፡፡ የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን÷ ርግቦችንም የሚሸጡትን÷ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፡፡ የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን÷ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፡፡ ርግብ ሻጮችንም÷ “ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም÷ “የቤትህ ቅናት በላኝ” የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ ዐሰቡ፡፡ 
  አይሁድም መልሰው÷ “ይህን የምታደርግ ምን ምልክት ታሳያለህ?” አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም÷ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው፡፡ አይሁድም÷ “ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ተሠራ፤ አንተስ በሦስት ቀኖች ውስጥ ታነሣዋለህን?” አሉት፡፡ እርሱ ግን ይህን የተናገረው ቤተ መቅደስ ስለ ተባለ ሰውነቱ ነበር፡፡ ከሙታን በተነሣ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንደ ነገራቸው ዐሰቡ፤ በመጻሕፍት ቃልና ጌታችን ኢየሱስ በነገራቸውም ነገር አመኑ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም በፋሲካ በዓል በኢየሩሳለም ሳለ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ በስሙ አመኑ፡፡ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ግን አያምናቸውም ነበር፤ ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና፡፡ የሰውንም ግብሩን ሊነግሩት አይሻም፤ እርሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡

  Read more »

 • አላዋቂ ሳሚ . .

  ታኅሣሥ 22 ቀን 2007 ዓ.ም.

  “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ይላሉ አበው፡፡ መረጃ ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላው ከመቅጽበት በሚዛመትበት በዚህ ዘመን፤ ላይከፈት የተከደነ፤ ላይታይ የተሸፈነ ምሥጢር የለም፡፡ ሰሞኑን ከወደ አሜሪካ የሰማነው ወሬ ለዚህ አጭር ጽሑፍ መነሻ ሆኗል፡፡

   

  ወይዘሪት ዌንዲ ቤልሻር ትባላለች፣ አማሪካዊት ናት፤ ሞያዋ የአጻጻፍ ብልሃትን ማስተማር ነው፤ የሥነ ጽሑፍ ባለሞያ ናት ማለት ነው፡፡ በዚሁ ሞያዋ እንጀራዋን ስታበስል ቆይታ፤ በስተመጨረሻ ከግእዝ ቋንቋ ጋር ትተዋወቃለች፤ በምታስተምርበት ፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ በሚገኙ አንድ ግእዝ ዐዋቂ ኢትዮጵያዊ ሊቅ አማካኝነት ፊደላችንን ለማንበብ መቁጠር ጀመረች፡፡ ከእንግሊዝኛ ፊደላት በተጨማሪ አዲስ ጥንታዊ ፊደል በማወቋ፤ ከዚያም አልፎ ለማንበብ ፊደላቱን መቁጠር በመቻሏ ተደሰተች፤ ግእዝ አወቅኩ አለች፤ አስተምራለሁም በማለት ተነሣች፡፡

   

  በሂደትም መጻሕፍትን ልተርጉም ብላ ተነሣች፤ ገድለ ወለተ ጴጥሮስ ከእጇ ገባ፤ ብታገላብጠው አልሆነም፡፡ መጽሐፉ እንደ ዓለት ጠጠረባት፤ አሉ የተባሉትን የግእዝ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላትን በመሰብሰብ ጠረጴዛዋ ላይ ደረደረች፤ ትርጉሙ ግን ሊሆን አልቻለም፡፡ “የጐበዝ ያለህ” ብላ ተጣራች፡፡ ሚካኤል ክላይነር የተባለ የግእዝ ዕውቀቱ ከእሷ የተሻለ ጀርመናዊ “አቤት፤ አለሁ፤ ምን ልታዘዝ” በማለት መልስ ሰጣት፡፡ የገጠማትን ችግር አማከረችው እና ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተወያዩ፡፡ ጀርመን ሀገር ሆኖ ገድሉን ወደ እንግሊዝኛ ሊተረጉምላት፣ እሷም ለአምስት ዓመታት የወር ደመወዝ ልትቆርጥለት ተፈራ ረሙ፡፡ በስምምነቱ መሠረት ሚካኤል ክላይነር በመጽሐፉ ኅትመት ስሙ የማይጠቀስ ከመጋረጃ ጀርባ ያለ /shadow written/ መሆኑ ነው፡፡ እሱ ተርጉሞ ሲጨርስ መግቢያና ማውጫ ጽፋለት በስሟ ታሳትማለች፡፡ ከወር ባነሰ ጊዜ በሚብተው አዲሱ የእነሱ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ “የትርጉም ሥራዋ” እንደሚታተም ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ በኩራት ላገኘችው ሁሉ በመግለጽ ላይ ትገኛለች፡፡

   

  ጉዱ እንዲህ ማድረጓ አይደለም፡፡ ይህች “የግእዝ ተማራማሪ” ሚካኤል ክላይነር ተርጉሞ ከሰጣት ንባብ አንዲት ዐረፍተ ነገር መዝዛ በማውጣት “በቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ዘመን ያልተገባ የአንስት መነኮሶይያት ግንኙነት ነበር” ብላ ማንበብ የማትችለውን የግእዝ ንባብ በቀኝ እጇ፤ ሚካኤል ከጀርባዋ ተርጉሞ የሰጣትን እንግሊዝኛ ራስዋ ይዛ ብቅ አለች፡፡ ብቅ ብላም መድረኩን ላዘጋጀላት አካል ሁሉ መናገር ጀመረች፡፡ ይህን ጉድ የእኛ ቤተ ክህነት ሰማች፡፡ ወይ ድፍረት በማለት “የተሳሳተ ትርጉምሽንና ንግግርሽን አቁሚ፤ እስከ አሁን ባለማወቅ የሳትሽ የገደፍሽውንም አርሚ” በማለት ደብዳቤ ተጻፈላት፡፡ ወ/ሪት ዌንዲ ግን “እንዴት ተደርጐ” በማለት በስሕተት ጐዳናዋ አሁንም ቀጥላለች፡፡

   

  በመሠረቱ የግእዝ ቋንቋ መዐዛ ብዙዎችን መሳቡ፤ በቋንቋው ከረጢትነት የተቋጠረው ምሥጢር ሰፊ፤ ጥልቅና የደለበ ዕውቀት የያዘ በመሆኑ ቀልባቸውን መያዙ በእጅጉ ያስደስተናል፡፡ ዛሬ ዛሬ የግእዝ ቋንቋችንን ለመቀጸል የሚፈልጉ አፍርንጅ በዓለም ዙርያ እየተበራከቱ ማየት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ግእዝን የማወቅ እንቅስቃሴ ዛሬ የተጀመረ አይደለም፡፡ በ፲፯ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ከነበረው ኢዮብ ሉዶልፍ /እ.ኤ.አ ከ1624-1704 የኖረ/ ጀምሮ በወሬ ሲሰማ፤ በተግባርም ሲታይ የነበረ እውነታ ነው፡፡ ሉዶልፍ የግእዝን አገር እንኳን በእግሩ ሳይረግጥ እዚያው ባለበት ሀገረ ጀርመን ሆኖ አባ ጎርጎርዮስ ከተባሉ የመካነ ሥላሴ መነኩሴ ተምሮ ሰዋስውን በመጠንቀቅ ዛሬም ድረስ ሁሉም የሚናጠቀውን የግእዝ ሰዋስውና መዝገበ ቃላት ጽፏል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያውያንን የግእዝ ሊቃውንት ክብርና ሞገስ አግኝቷል፡፡ ነገር ግን ከኢዮብ ሉዶልፍ ሥራ ጀርባ አውሮፓውያን ብዙም ያልዘመሩለት፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ልናውቀውና ልናዘክረው የሚገባ አንድ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ የግእዝ ዐዋቂ አባ ጎርጎርዮስ መኖሩ መታወቅ አለበት፡፡

   

  የሆነው ሆኖ የአባ ጎርጎርዮስ መኖር የኢዮብ ሉዶልፍን ክብር አይከፍለውም፡፡ ሊቅን በአግባቡ የመጠቀም ችሎታውን ያጐላዋል እንጂ፡፡ ጀርመናዊው ኦገስት ዲልማንም የግእዝ መጻሕፍትን በመመርመር የታወቀ ሊቅ ስለነበር “የግእዝን ሞያ እንደ እሱ የሚያውቅ የለም” ተብሎለታል፡፡

   

  ግእዝና የሰነቀው ዕውቀት በዓለም ዙርያ ያተረፈውን ዕውቀት በማስተዋልና በማሰብ የመደሰታችንን ያህል፤ እንደ ወይዘሪት ዌንዲ ዓይነት አላዋቂ ሳሚ መጥቶ የማይሆን ቆሻሻ ሊቀባው ሲገዳደር ስንመለከት እናዝናለን፡፡ እንደነ ሉዶልፍ ዓይነት የግእዝን ብልት አውቀው በመጠቀምና ሌሎችን በመጥቀም ያለፉና አሁንም ያሉ ቢኖሩም፤ እንደ ዌንዲ ዓይነት ደፋሮች ብቅ ብቅ ብለው እንዳለፉና ዛሬም እንዳሉ ጉዳዩን በቅርብ ለሚከታተል ሁሉ እንግዳ አይደ ለም፡፡ በዚህኛው ጐራ ብቅ ያሉትን ኩሸትና ድፍረት መዘርዘር “ከሰደበኝ ስድቤን የነገረኝ” እንደሚባለው ዓይነት ስለሚሆን ተገቢ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ በዚህኛው ጐራ የሚመደቡት አፍርንጅ ብቻ አይደሉም፡፡ በግእዝ አገር የተወለዱ፤ ነገር ግን ለግእዝ ባዕድ የሆኑ ኢትዮጵያውያንም እንዳሉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

   

  በግእዝና አምቆ በያዘው ዕውቀት ላይ የሚደረጉ ምርምሮች የሚቆሙ አይደሉም፤ ነገም ይቀጥላሉ፡፡ ቤተ ክህነታችን የምስጋናም ይሁን የወቀሳ ደብዳቤ ቢጽፍም፣ ባይጽፍም፤ የግእዝ ባለቤቶች ኢትዮጵያውያን ተደሰትንም አዘንም በየትኛውም መንገድና ችሎታ በቋንቋችንና በዕውቀታችን የሚደረገው ምርምርና ኩሸት ይቀጥላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር በቋንቋችንና በዕውቀታችን ላይ በሚደረጉ ምርምሮች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚፈጠሩ ስሕተቶች እንዲቀንሱ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ብሎም የሀገሪቱን ትክክለኛ ማንነት የሚገልጹ ግኝቶች እንዲበዙ ትውልድን የሚጠቅም ተግባር መፈጸም ነው፡፡

  በመሆኑም ከላይ የጠቀስነው እንዲፈጸም ሓላፊነቱ የተጣለብን አካላት ብንፈጽማቸው የምንላቸውን በአጭሩ እናቀርባለን፡፡
   
  1. ቤተ ክህነት
   
  የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ሊቃውንቷ መጠነ ሰፊ፤ ዘርፈ ብዙ የሆነ ውን ኢትዮጵያዊና ክርስቲያናዊ ዕውቀት በጽሑፍ መዝግበው፤ በመጠበቅ ለትውልድ እንዲቆይ በማድረጋቸው የማያመሰግን ቢኖር ዕውቀትን፣ ጥበብን እንዲሁም ፍልስፍናን የሚጠላ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ዕውቀትም ፍልስፍናም የሌለው ነው፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያናችንን ዘመን ተሻጋሪና ብሔራዊ አስተዋጽኦ ሳይሸራረፍና ሳይዛነፍ የማስቀጠል ሓላፊነት ያለበት ቤተ ክህነታችን ያነሣነው ርእሰ ጉዳይ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገባና ሌሎች ስሕተቶችም እንዲቀንሱ፡-
   
  ሀ. ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላትን ሀብት መርምሮ ቢያጣራ
   
  የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ሀብት በቁጥሩም ይሁን በይዘቱ ሰፊና ጥልቅ ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በዘርፉ የተካሔዱ ጥናቶችን ከማየት ባሻገር፤ ሀብቱን ለዘመናት ይዘው ያቆዩ ገዳማትንና አድባራትን ዕቃ ቤቶች መጐብኘት ይበቃል፡፡ ይህ የሥነ ጽሑፍ ሀብት ለዘመናት ወደ ግእዝ ቋት የገባበትን ሒደት ስንመለከት፤ በየጊዜው በቤተ ክርስቲያኗ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐተ እምነትና ታሪክ እንዲሁም ትውፊት ሚዛንነት እየተመዘነ አልነበረም ማለት የሚያስችሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ በሥነ ጽሑፍ ውስጥ የሊቃውንት የግል ፍልስፍናና ዐቋሞች፣ የገልባጮች /copysts/ “ማብራሪያዎች” /explanations/ እና ተጨማሪ አሳቦች /additions/ እንዲሁም “ክለሳዎች” /revisions/ ይገኛሉ፡፡ በግል የሚደረጉ ኩሸቶች ደግሞ ብዙኃኑን ወይም ትልቁን ሥዕል ላይገልጹ ወይም ላይወክሉ ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎም ከቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ በአንጻር የሚቆሙ ሐተታዎችም ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሥነ ጽሑፎች ከመንፈሳዊ ውጭ ለሚደረግ ጥናትና ምርምር ጠቀሜታቸው የጐላ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያኗን ግን አይወክሉም፡፡

   

  በቅዱሳን የገድል መጻሕፍትም ላይ ቢሆን ገልባጩ /ሁለተኛው ጸሐፊው/ በማወቅም ይሁን በስሕተት የሚጨምራቸው የግል ሐተታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ በሰፊው ምርት ላይ እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁሉ በትልቁ የሥነ ጽሑፍ ሀብታችንም ላይ በማወቅም ባለማወቅም ተዘርተው የበቀሉ እንክርዳዶች አይጠፉም፡፡ ይህ ደግሞ በየትኛውም የሥነ ጽሑፍ ሀብት ባላቸው ሀገራት የነበረና የሚኖር ነው፡፡ ምናልባት እኛን ከሌሎች ልዩ የሚያደርገን፤ ይህ ችግር በሥነ ጽሑፍ አዝመራችን ሊኖር እንደሚችል በማመን የማጣራት ሥራ ካለመሥራታችን ላይ ነው፡፡

   

  ከ300 በላይ የልዩ ልዩ ቅዱሳንና ቅዱሳት ገድላት እንዳሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተመሳሳይም በርካታ የነገረ ሃይማኖትና ሥርዐተ እምነት መጻሕፍትም አሉን፡፡ እነዚህ ሁሉ በግእዝ ልሳናችን ተጽፈው የቆዩን ናቸው፡፡ ታድያ በየዘርፉ ተጽፈውና በየዘመናቱ እየተባዙ /እየተገለበጡ/ የቆዩንን እነዚህን ሥነ ጽሑፎች መርምሮ ፍሬውን ከገለባ በመለየት ቤተ ክርስቲያኗን የሚገልጹትን ቅጂዎች በቀኖና ማሳወቅ ከቤተ ክህነታችን የሚጠበቅ አንገብጋቢ ተግባር ነው፡፡
   
  ለ. ለጥናትና ምርምር ማዘጋጀት
   
  ዕውቀትን ከቅድስና ጋር የያዙ አባቶቻችን አንጀታቸውን አጥፈው፤ ብራና ፍቀውና አለስልሰው፤ ቀለም በጥብጠው፣ ብዕር ቀርጸው ጀርባቸውን አጐብጠው ጽፈውልን ያለፉት ትውልድ እንዲማርባቸው ነው እንጂ በየዕቃ ቤቱ ታፍነው በምስጥ እንዲበሉ፣ በእሳት እንዲቃጠሉ እንዲሁም በሌሎች ተፈጥሮአዊ አደጋዎች እንዲወድሙ አይደለም፡፡ ዛሬ በየዕቃ ቤቱ የሚገኙትን መጻሕፍት የሚጐበኝ አካል ሳያዝን አይወጣም፡፡ ምንም ያህል ጥረት ቢደረግ ዳግም ሊገኙ የማይችሉ፣ የዕውቀት ምንጭ የሆኑ የብራና መጻሕፍት እንደተቀበሩ ይጠፋሉ፤ ይህ መሆን የለበትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ባለሞያዎችን አሰማርታ መጻሕፍት ባሉበት እንዲጠበቁ ማድረግ ይገባታል፡፡ ለጥናትና ምርምር እንዲውሉም በልዩ ልዩ መንገድ ገልብጦ ማእከላዊ በሆነ ቦታ ማስቀመጥ ይጠበቅባታል፡፡
   
  ሐ. መጻሕፍቱን ቀድሞ መተርጐ ምና መተንተን
   
  ዛሬ ይህንን ጽሑፍ እንድንጽፍ ያነሣሣን የወ/ሪት ዌንዲ የተሳሳተና ዕውቀት የጐደለው ትርጉምና ሐተታ ነው፡፡ ወ/ሪት ዌንዲ አጣማ የተረጐመችው መጽሐፍ ቀድሞ በራሳችን ሊቃውንት መልቶና ሰፍቶ ቢተረጐም ኖሮ የወ/ሪት ዌንዲ ስሕተት አይፈጠርም ነበር፡፡ በመሆኑም የግእዝ መጻሕፍትና ሊቃውንት ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍቱን ከበቂ ማብራሪያና ትንተና ጋር እንግሊዝኛንና አማርኛን ጨምሮ ወደ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች እየተረጐመች ለተጠቃሚዎች ብታደርስ ቢያንስ ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ስሕተቶችን መቀነስ ይቻላል፡፡
   
  2. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን
   
  በቀደሙት አበው ተጽፈው ትውልድን በመሻገር ለእኛ የደረሱንን መጻሕፍት የመጠበቅና የማስጠበቅ እንዲሁም የመተርጐምና የማብራራት ቀዳሚ ሓላፊ ነት የሚወድቀው በሊቀውንተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ነው፡፡ በመሆኑም የአበውን ወንበር ተረክበው የሚያስተምሩ ሊቃውንት ቅዱሳት መጻሕፍትን የመመርመሩንና የማስተካከሉን ሥራ አጠናክረው ቢቀጥሉ አላዋቂዎች የሚያ ደርሱትን ጥፋት መቀነስ ይቻላል፡፡ እንደ ወይዘሪት ዌንድ ዓይነት የአላዋቂ ትርጉም ሲከሠትም ፈጥነው በተገኘው መንገድ ሁሉ መልስ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

   

  ትውልዱ የአባቶቹን ዕውቀት ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን በቀጥታ እንዳያገኘው የቋንቋ አለማወቅ አጥር ይሆንበታል፡፡ በመሆኑም የዛሬዎቹ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትውልዱን በሚማርከው መልኩ ቋንቋውን ሊያስተምሩትና የቋንቋውን ገደል አሻግረው ወደ አባቶቹ የዕውቀት አዝመራ ሊያደርሱት ይገባል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን ተግቶ ለመማር ለማይችለው መጻሕፍቱን ወደሚያውቀው ቋንቋ በመመለስ ዕውቀትን የማሸጋገር ሥራ ቢሠሩ ወጣቱ በሚያውቀው የአፍርንጅ ቋንቋ ስሕተት የሚፈጽሙ እንደ ዌንዲ ዓይነቶቹን ተከራክሮ መርታትና ማሳመን ይችላል፡፡
   
  3. ምእመናን
   
  ምእመናን እንደ ሰሞኑ ያሉ ድፍረቶች በቅዱሳን ላይ ሲነገር ሲሰሙ ሊደናገጡ አይገባም፡፡ ይልቁንም ቅዱሳን አባቶችና እናቶች ስለተጠሩበት መንፈሳዊ ሕይወት ሲሉ ራሳቸውን ለሰማዕ ትነት አሳልፈው እየሰጡ እምነታቸውን በተግባር ገልጸው እንዳለፉ መገንዘብ ይገባቸዋል፡፡ በመሆኑም ሳይደናገጡ ከቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ጋር ያላቸውን የጸሎት ግንኙነት ሊያጠናክሩ ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወጣቶች ጥያቄ ሲፈጠርባቸው ወደ ሊቃውንት አባቶቻቸው በመቅረብ ትክክለኛውን ሊረዱና ሊይዙ ይገባል፡፡ ቅዱሳንን የመረጠ፤ መርጦም በተጋድሎ ያጸናቸውና የድል አክሊልም ያቀዳጃቸው አምላከ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን ከከሳሾችና ከወቃሾች ይጠብቅልን፤ እኛንም በመንፈሳዊ ቅንዓት ቀስቅሶ በቅዱሳን ላይ የስድብ አፋቸውን ለሚከፍቱ ተገቢ መልስ ለመስጠትና በእምነታችን ለመጽናናት ያብቃን አሜን፡፡

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ከታኅሣሥ 1-15 ቀን 2007 ዓ.ም.

  Read more »

 • ገብር ኄር (የዐቢይ ጾም 6ኛ ሳምንት)

  መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፡፡

  ትርጉም: ጌታው በመልካም ሥራ የሚያገኘው በሐብቱ ኹሉ ላይ የሚሾመው፤የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር አንተ የታመንክ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለዋል፡፡

  መልዕክታት
  2ኛ ጢሞ.2÷1-15 ልጄ ሆይ÷ አንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በርታ፡፡ በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ትምህርት ለሌሎች ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች እርሱን አስተምራቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል፡፡ 

  1ኛ ጴጥ.5÷1-11 እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ÷ የክርስቶስም መከራ ምስክር÷ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግለዎችን እማልዳቸዋለሁ፡፡ በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን፡፡

  ግብረ ሐዋርያት
  የሐዋ.1÷6-8 እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ÷ "ጌታ ሆይ÷ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም፡፡ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኅይልን ትቀበላላችሁ፤በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፣በሰማሪያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቸ ትሆኑኛላችሁ።"
  ምስባክ
   መዝ. 39÷8 "ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡"
   ትርጉም፦ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራ
  ወንጌል
  ማቴ. 25÷14-30 “መንገድ እንደሚሄድ÷ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደ ሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት÷ ለአንዱ ሁለት÷ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ፡፡ 
  ቅዳሴ
  ዘባስልዮስ

  ምንጭ፤ ማሕበረ ቅዱሳን 

  Read more »

 • የደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን ዘንድ ዛሬ ይከበራል!!!

  የደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን ዘንድ ዛሬ ይከበራል

  አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደመራ በአል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን ዘንድ ዛሬ በድምቀት ይከበራል።

  በተለይም በዓሉ በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ የቤተክርስትያኒቱን ፓትሪያርክ ጨምሮ ብጹአን ሊቃነ ጵጵሳት፣ ካህናት፣ የእምነቱ ተከታዮችና የተለያዩ የውጭ ሃገራት ጎብኝዎች በተገኙበት ነው የሚከበረው።

  በደመራው በአል ቀን ጥንግ ድርብ የለበሱ ካህናቶችና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተለያዩ ዝማሬዎችን ያቀርባሉ።

  ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች መልእክቶችን ያስተላልፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከቤተክርስቲያኒቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

  ማምሻውንም የደመራ መለኮስ ተካሄዶ የደመራው በዓል የሚፈጸም ሲሆን፥ በነገው እለትም የመስቀል በዓል የሚከበር ይሆናል።

  በተያያዘ ዜና ዛሬ በሚከናወነው የደመራ በአል ላይ የእሳት አደጋ እንዳይደርስ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል ብሏል የአዲስ አበባ የእሳትና የድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን።

  በዓሉ በተለይም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ ደመራ በመትከል የሚከበር በመሆኑ ለእሳት አደጋ መከሰት ምክንያት ሊሆን ስለሚችል፥ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ከተቀጣጣይ ነገሮች ጠብቆ ማካሄድ ይጠበቅበታል ነው ያሉት የባለስልጣኑ የኮሚኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ ።

  ደመራው ሲተከል ከኤሌትሪክ መስመሮች፣ ከነዳጅ ማደያዎች፣ ከጋራዦችና ከሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች ርቆ መሆን እንደሚኖርበትም ጠቁመው፥ የደመራው ስነ ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላም እሳቱን ሙሉ በሙሉ በውሃ ማጥፋት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል ።

  ከአቅም በላይ ሁኔታ የእሳት አደጋ ከተከሰተም ለባለስልጣኑ በስልክ ቁጥሮች 011 1555300 ወይም 011 156 86 01 ወይም በነጻ የስልክ መስመር 939 በመደወል በአፋጣኝ ማሳወቅ እንደሚገባ መግለጹን ትዕግስት ስለሺ ዘግባለች።

  Source:Fana Broadcasting

   

   

  Read more »

RSS